የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 14ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥሉ ሽረ እንዳስላሴ እና የካ ክፍለከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
አውስኮድ 0-3 ሽረ እንዳስላሴ
በአዲስ አበባ ስታድየም ረፍድ 04:00 ላይ የተደረገው ይህ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል መልካም እንቅስቃሴ ታይቶበት በሽረ የበላይነት ተጠናቋል። የጨዋታውን ክብደት እና ውጥረት ያህል ማራኪ የኳስ ፍሰት በተመለከትነበት በዛሬው ጨዋታ አውስኮድ በተሻለ ሁኔታ ኳሱን ይዞ ለመጫወት ጥረት ቢያደርግም ሽረዎች ከፍተኛ የጨዋታ ፍላጎት እና የህብረት እንቅስቃሴ ውጤታማ አድርጓቸው አሸንፈው ወጥተዋል።
በ19ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት ከብሩክ ገብ የተሰጠውን ቅጣት ምት ሰዒድ ሁሴን በግንባሩ ገጭቶ ጎል በማስቆጠር ሽረዎችን ቀዳሚ ማደረግ ችሏል ። የሽረ የማጥቃት ምንጭ የሆኑት ሁለቱ የእግራ እግር ተጨዋቾች ጅላሎ ሻፊ እና ሳሙኤል ተስፋዬ መሀል ሜዳውን በሚገባ ተቆጣጥረው የሚያደራጁት ኳስ ለአውስኮድ አማካዮች ፈታኝ ሲሆን ለሽሬ አጥቂዎች የተሻሉ የማግባት አጋጣሚዎችን ይፈጥር ነበር። 29ኛው ደቂቃ ላይ የአውስኮዱ ግብ ጠባቂ ሙሉጌታ አሰፋ ኳሱን በቶሎ ለማስጀመር በግራ መስመር ለሚገኘው ተከላካይ የሰጠውን ኳስ በፍጥነት ቀምቶ የግብ ጠባቂውን ከግብ ክልሉ መራቅ የተመለከተው ሰዒድ ሁሴን ከርቀት በጥሩ አጨራረስ ለቡድኑም ለራሱም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ግራ መስመራቸው ላይ በነበረ ክፍተት የተነሳ በተደጋጋሚ ጫና ይደረግባቸው የነበሩት አውስኮዶች አብደላ እሸቱ ወደ ፊት በመሄድ በግሉ ከሚያደርገው ጥረት ውጭ ኳሳቸው ይቆራረጥባቸው ነበር ።
ከእረፍት መልስ የሁለት ተጨዋቾች ቅያሪ በማድረግ ወደ ሜዳ የገቡት አውስኮዶች ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርገም በቡድኑ ውስጥ በተሻለ ኳስን ለአጥቂዎች የሚያደርስ አማካይ አለመኖሩ እና በሦስት የተከላካይ አማካኝ መጫወቱ ለአጥቂዎች በተገቢ ሁኔታ ኳስ አለመድረሱ ጠንካራ የጎል እድል መፍጠር ሳይቻላቸው ቀርተዋል ። ያም ቢሆን በበድሩ ሁሴን በሁለት አጋጣሚ ያገኘውን የጎል አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ። ሽረዎች በሁለተኛው አጋማሽ ተዳክመው የቀረቡበት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቢሆንም አውስኮዶች ጎል ፍለጋ የግብ ክልላቸውን ነቅለው በሚሄዱበት አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከባድ ነበር። ልደቱ ለማ ተቀይሮ ገብቶ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ግብ ጠባቂው ያዳነበት የሽሬዎች ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲሆን ጨዋታው ማብቂ ላይ ከመአዘን ምት የተሻገረውን ካሜሩናዊው ፓገን ሮድሪክ በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሮ ጨዋታው በሽረ 3 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ 14 ጨዋታ ያደረገው ሽረ በ27 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ሲቀመጥ አውስኮድ በተከታታይ ጨዋታ በመሸነፉ በ17 ነጥብ በዘጠነኛ ደረጃው ላይ ረግቷል።
የካ 2-1 ኢትዮጵያ መድን
በኦሜድላ ሜዳ በተደረገው ጨዋታ በየካ ክ/ከተማ 2-1 አሸንፎ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚያደርገውን ፉክክር አጠናክሯል። በመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተመለከትን ቢሆንም በ15 ደቂቃ ውስጥ ግን ኢትዮዽያ መድኖች ወደ ፊት በመሄድ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። በተለይ በሦስት አጋጣሚዎች ሳጥን ውስጥ ገብተው ጋናዊው አጥቂ አዳም ሳሙኤል ፣ ሀብታሙ መንገሻ ፣ ስኡድ ኑር ያባከኗቸው ኳሶች በኋላ ላይ ወ.ዋጋ አስከፍሏቸዋል።
የጨዋታው ደቁቂቃ እየገፈ ሲሄድ ወደ እንቅስቃሴ የገቡት የካዎች በመድኖች ላይ ጫና ማሳደራቸው አይሎ በ27ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተጣለውን ኳስ የመድን ተከላካዮች ከግብ ክልላቸው ለማራቅ በፈጠሩት ትርምስ ኢዮብ ዘይኑ በመቀስ ምት ጎል ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ጨዋታው በመሀል ሜዳ ላይ ብቻ ተገድቦ ብዙም የጎል ሙከራ ሳይደረግበት ቀጥሎ 43ኛው ደቂቃ ላይ በየካዎች በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው አማካዩ በረከት አምባዬ ከመሀል ሜዳ ወደፊት የጣለውን ኳስ ከተከላካዮች መሀል ሾልኮ የወጣው አጥቂው ታምሩ ባልቻ ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥሮ ወደ ሳጥኑ ይዞ በመግባት የበረኛውን አቋቋም በማየት ሁለተኛ ጎል ለየካዎች በማስቆጠር መሪነታቸውን አሰፎቶ ለእረፍት ወጥተዋል ።
ከእረፍት መልስ መድኖች በተሻለ ሁኔታ መንቀሳቀስ ቢችሉም ከአማካዮቹ በኩል ወደ አጥቂዎቹ ይሻገር የነበረው ኳስ ለአጥቂዎቹ ከመድረስ ይልቅ ለየካ ተከላካዮች ሲሳይ ከመሆን ባለፈ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም ። የካዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ በመፈለጋቸው በሁለተኛው አጋማሽ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ወደፊት የሚሄዱበት መንገድ አነስተኛ ነበር ። ጨዋታው 20 ደቂቃ ሲቀረው በተወሰነ መልኩ አሰልጣኝ ደረጄ በላይ ወጣት አጥቂዎችን ቀይሮ በማስገባት ያደረጉት የጨዋታ ለውጥ ተሳክቶላቸው 70ኛው ደቂቃ ላይ ሚካኤል በየነ አስቆጥሮ የጎል ልዩነቱን ቢያጠብም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በየካ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቀቀል።
ውጤቱን ተከትሎ የካዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ባይችሉም ከላያቸው የሚገኙ ክለቦችን ለመጠጋት የዛሬው ሦስት ነጥብ ሲያግዛቸው በአንፃሩ መድኖች መሸነፋቸውን ተከትሎ ወደ መሪዎቹ ጎራ ለመቀላቀል የነበራቸውን እድል አምክነዋል።