በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የግብፁ ኃያል ክለብ ዛማሌክን ከውድድር ውጭ በማድረግ ታሪክ መስራት የቻሉት ወላይታ ድቻዎች ሁለት ተጫዋቾቻቸው የግብፅ ክለቦች አይን ማረፊያ ሆነዋል።
ፈላጊ ክለቦቻቸው ስማቸው ባይገለፅም በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚወዳደሩ እንደሆኑ ሲታወቅ ተጫዋቾቹ ደርሶ መልሱ ጨዋታ ላይ ጥሩ አቋም ማሳየት የቻሉት ጃኮ አራፋት እና በዛብህ መለዮ እንደሆኑ አረጋግጠናል። በተለይ ጃኮ አራፋት ይህ የውድድር ዘመን ሲያበቃ በቀጥታ አሁን ስሙ ይፋ ወዳልተደረገው ክለብ ለማምራት ከስምምነት መድረሳቸውን ሰምተናል ።
ከበዛብህ መለዮ ጋር በተያያዘው የዝውውር ዜና ክለቡ ተጫዋቹን በቀጥታ ከማስፈረም ይልቅ ከሦስት ወር በኋላ ወደ ግብፅ ሄዶ የሙከራ ዕድል ሊሰጡት እንደሚፈልጉ ገልፀው ሙከራውን በበቂ ሁኔታ መፈፀም ከቻለ ሊያስፈርሙት እንደሚችሉ መነጋገራቸውን ሶከር ኢትዮዽያ አረጋግጣለች ።
ባለፉት ጊዜያት ሽመልስ በቀለ (ፔትሮጄት) እና ኡመድ ኡክሪ (ኤንታግ ኤል ሀርቢ ፣ ኤንፒፒአይ እና ኢቲሀድ አሌሳንድሪያ) እንዲሁም ሳላህዲን ሰዒድ (አል አህሊ እና ዋዲ ደግላ) በግብፅ ቡድኖች የተጫወቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው።