በ2019 ኒጀር ላይ ለሚስተናገደው ከ20 አመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ማጣርያ ጨዋታውን ከብሩንዲን ጋር የሚያደርገው ብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አትናፉ አለሙን በዋና አሰልጣኝነት መሾሙ ይታወሳል። ቡድኑ በዕድሜ ተገቢነት እና በሌሎች ጉዳዮች ጊዜ ቢወስድበትም በዝግጅቱ ተካፋይ ከነበሩ በርካታ ተጨዋቾች መሀል የመጨረሻ 25ቱን ለብሩንዲው ጨዋታ መምረጡን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
በምርጫው አሰልጣኝ አጥናፉ በ2017 ከ17 አመት በታች ቡድንን በያዙበት ወቅት ከተጠቀሙባቸው ተጨዋቾች መሀከል የኢትዮጵያ ቡናዋቹ አቡበከር ነስሩ እና ሚኪያስ መኮንን ፣ የወላይታ ድቻው እዮብ አለማየሁ እና በቅርቡ አዳማ ከተማን የተቀላቀለው ጫላ ተሺታን በአሁኑ ቡድናቸው ውስጥ አካተዋል። በፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ውስጥ ስንመለከታቸው ከነበሩ ሌሎች ተጨዋቾች መሀል ደግሞ የሀዋሳ ከተማው የመሀል ተከላካይ መሳይ ጳውሎስ ፣ የወልዋሎ ዓዲግራቱ ግብ ጠባቂ በረከት አማረ ፣ በአርባምንጭ ከተማ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ መካተት የጀመረው ግብ ጠባቂ ጽዮን መርዕድ እንዲሁም ከሀዋሳ ጋር የU20 ሻምፒዮን በመሆን ዘንድሮ በዋናው ቡድን ጥሩ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ጸጋአብ ዮሴፍ ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪም በቀድሞው የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ በሚሰለጥነው የሉቲንያው ኤፍ ሲ ስተምብራስ የሚጫወተው ሶፎንያስ መኮንንም የቡድኑ አካል ሆኗል። እነዚህን ጨምሮ 25 ተጨዋቾችን ያካተተው የቡድኑ አባላት ስም ዝርዝርም ይሄን ይመስላል።
ፂዮን መርዕድ (አርባምንጭ ከተማ) ፣ በረከት አማረ (ወልዋሎ ዓ.ዩ) ፣ ፖልክ ቾል (ቡራዩ ከተማ) ፣ ሳሙኤል ተስፋዬ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ሸዊት ዮሀንስ (ሽረ እንደስላሴ) ፣ መሣይ ጳውሎስ (ሀዋሳ ከተማ) ፣ እዮብ ዓለማየሁ (ወላይታ ድቻ) ፣ ሙጃሂድ መሀመድ (ሲዳማ ቡና) ፣ ዮናታን ገዙ (ሀዋሳ ከተማ) ፣ ዮሀንስ ሴጌቦ (ሀዋሳ ከተማ) ፣ ዮናታን ፍሰሀ (ሲዳማ ቡና) ፣ ፀጋአብ ዮሴፍ (ሀዋሳ ከተማ) ፣ አቤል እንዳለ (ደደቢት) ፣ አቡበከር ነስሩ (ኢትዮጵያ ቡና) ፣ ጫላ ተሺታ (አዳማ ከተማ) ፣ ገብረመስቀል ዱባለ (ስልጤ ወራቤ) ፣ ሚኪያስ መኮንን (ኢትዮጵያ ቡና) ፣ ተስፋዬ በቀለ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ እስራኤል ሸጎል (አርባምንጭ ከተማ) ፣ ስንታየሁ ዋለጨ (ኢትዮ ኤሌክትሪክ) ፣ እሱባለው ሙሉጌታ (አዲስ አበባ ከተማ) ፣ ሚካኤል ሐሲሶ (ሲዳማ ቡና) ፣ ቃልኪዳን ዘላለም (ኢትዮጵያ ቡና) ፣ ሶፎንያስ መኳንንት ( ኤፍ ሲ ስተምብራስ) ፣ ሰለሞን ወዴሳ (ስልጤ ወራቤ)
የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከ2001 በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውድድሩ ለመመለስ በማጣሪያው የመጀመሪያ ጨዋታ ብሩንዲን ሜዳው ላይ ሲያስተናግድ በደርሶ መልስ አሸናፊ ከሆነ በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ሱዳንን የሚያገኝ ይሆናል።