በያዝነው አመት በርካታ የአስተዳደራዊ እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ለውጥ ያደረገው አርባምንጭ ከተማ አሁኝ ደግሞ ነባር ተጫዋቾችን ከክለቡ እያሰናበተ ሌሎች አዳዲስ ተጨዋቾችን ከከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ክለቦች እያስፈረመ እና በሙከራ ላይ እያየ ይገኛል። በዚህም ሂደት ውስጥ ክለቡ በቡድኑ ውስጥ ደካማ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ካላቸው ሶስት ተጨዋቾች ጋር በስምምነት መለያየቱ ተሰምቷል።
በክለቡ ያለፍትን ሁለት አመታት ድንቅ እንቅስቃሴ በማድረግ ስኬታማ የውድድር ጊዜያትን እያሳለፈ የነበረው የቀድሞው የኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ መከላከያ እና ሀዋሳ ከተማ የመሀል ሜዳ ተጨዋች ወንድሜነህ ዘሪሁን በውድድር ዘመኑ ጅማሮ መልካም የሚባል ጊዜ ያሳለፈ ቢሆንም በጉዳት ምክንያት ክለቡን እየጠቀመ አይደለም በሚል ቀሪ ውል እያለው ከክለቡ ጋር በስምምነት እንዲለያይ ሆኗል። ሌላኛው ከክለቡ የተለያየው ተጨዋች ደግሞ አጥቂው ገ/ሚካኤል ያዕቆብ ነው። የቀድሞው የሲዳማ ቡና አጥቂ ከሁለት አመት በፊት ሀዋሳ ከተማን ለቆ አርባምንጭ ከተማን ከተቀላቀለ በኃላ በክለቡ መልካም የውድድር ጊዜያት አሳልፎ ውሉ ቢጠናቀቅም ዘንድሮ በአዲስ መልክ የአንድ አመት ኮንትራት እንደፈረመ ይታወሳል። ሆኖም በጉዳት የተወሰኑ ጨዋታዎች ያመለጡት አጥቂው በክለቡ የተጠበቀውን ያህል መሆን አልቻለም በሚል ምክንያት ሁለተኛው ተሰናባች ተጨዋች ሆኗል። በክረምቱ አዳማ ከተማን ለቆ ወደ አርባምንጭ ያመራው የ2003 የኢትዮጵያ ኮከብ ግብ ጠባቂው ሲሳይ ባንጫ የመሰናበት ዕጣ ፈንታ የገጠመው ሶስተኛው ተጫዋች ሆኗል። በሲዳማ ቡና እና ደደቢት እንዲሁም ከ31 አመት በኃላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ በቻለው ስብስብ ውስጥ የነበረው ግብ ጠባቂው ዘንድሮ ወደ አርባምንጭ ባመራበት አመት ከተጠበቀው በታች አቋምን በማሳየቱ በደጋፊው እና በክለቡ እንደማይፈለግ ተነገሮት በስምምነት ተለያይቷል። ተጨዋቹ በወጣቱ ግብ ጠባቂ ፂሆን መርዕድ እና ጃክሰን ፊጣ ተበልጦ የቋሚነት እድልንም ማጣቱ ይታወሳል፡፡
ሶስቱም ተጨዋቾች ከትናንት ጀምሮ ልምምድ ያቆሙ ሲሆን በ16ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀግብር አርባምንጭ ለሚጠብቀው የመጀመሪያ ጨዋታም ወደ መቐለ ሳይጓዙ ቀርተዋል። አሁን ላይ ተጫዋቾቹ ቀሪ የውል ስምምነት ከክለቡ ጋር ስላላቸው በክፍያ ጉዳይ እየተነጋገሩ እንደሆነም ተሰምቷል። አርባምንጭ ከተማ ከነዚህ ተጫዋቾች አስቀድሞ ከታዲዮስ ወልዴ እና ዮናታን ከበደ ጋር መላየያቱ እንዲሁም ፍቃዱ መኮንን ፣ ዘካሪያስ ፍቅሬ እና በረከት አዲሱን ወደ ክለቡ ማምጣቱ የሚታወስ ሲሆን ሌሎች አዳዲስ ተጫዋቾችንም ከታችኛው ሊግ አምጥቶ የሙከራ እድል እንደሰጠ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጨመሳ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡