ኢትዮጵያዊው አጥቂ ፍቅሩ ተፈራ ለህንዱ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለብ መሃመዳን ስፖርቲግ ክለብ ለመጫወት መስማማቱ ይታወሳል፡፡ መሃመዳን ፍቅሩን የግሉ ያደረገበትን ዝውውር ካጠናቀቀ በኃላ በይፋ ተጫዋቹን አስተዋውቋል፡፡
ፍቅሩ ማክሰኞ ከመሃመዳን ጋር ልምምድ የጀመረ ሲሆን ወደ ክለቡ በመምጣቱ ደስተኛ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ “እንደመሃመዳን ላለ ክለብ የመጫወት እድል ልተወው የማልችለው ነበር፡፡ መሃመዳን የማሸነፍ ባህል ያለበት ቡድን ነው፡፡ ወደ መሃመዳን የመጣሁት እጣ ፋንቴ ስለነበር ብዬ አስባለው፡፡ እዚህ በእግርኳስ መደስትን እና መሃመዳን የሰጠኝ እድል በአግባቡ መጠቀም እፈልጋለው፡፡”
ፍቅሩ በ2017 መጨረሻ ከደቡብ አፍሪካው ሃይላንድስ ፓርክ ጋር የነበረው ውል ከተጠናቀቀ በኃላ ከተለያዩ የህንድ ክለቦች ጋር ስሙ ለዝውውር ተያይዞ ነበር፡፡ በህንድ የመጫወት ልምድ ያለው ፍቅሩ በኮልካታው ክለብ ለመላመድ እንደማይቸገርም በአስተያየቱ ገልጿል፡፡ “እዚህ ለመደላደል እምብዛም ግዜ አያስፈልገኝም፡፡ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ምቾት እየተሰማኝ ነው፡፡ እዚህ የተገኘሁት ለማሸነፍ ነው፡፡” ብሏል።
የመሃመዳን ክለብ ዋና ፀሃፊ ጋዛል ዛፋር በበኩላቸው ፍቅሩ የካበተ ልምዱን ለቡድኑ ወጣት ተጫዋቾች እንደሚያጋራ በማመን በዝውውሩ ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ “ፍቅሩ በቅርብ አመታት በህንድ ካየናቸው ምርጥ የፊት መስመር ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡ የእሱ መምጣት ወጣት እና ባለተሰጥኦው የሆነውን የቡድናችን የፊት መስመር ያሟላል፡፡ ልምድ ያለው ተጫዋች በቡድናችን መኖሩ ጥሩ ነው ምክንያቱም ወጣት የሆነው የቡድናችን ስብስብ ከፍቅሩ የሚወስዱት ነገር ይኖራል፡፡” ብለዋል።
ፍቅሩ በመሃመዳን 10 ቁጥር መለያ የሚለብስ የሆናል፡፡ ለ16 የተለያዩ ክለቦች በሶስት አህጉሮች የተጫወተው ፍቅሩ ለ12 አመታት ከኢትዮጵያ ውጪ የእግርኳስ ህይወቱን መርቷል፡፡