የካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ድልድል ዛሬ በካይሮ ወጥቷል፡፡ በካርል ሪትዝ ሆቴል በተደረገው የእጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ላይ ካፍ ሃዘም ኢማም፣ ጂልቤርቶ እና ማርክ ፊሽ ተጋባዥ የነበሩ ሲሆን የቀድሞ የአንጎላ እና አል አህሊ የመስመር ተጨዋች ጂልቤርቶ ነበር እጣውን ያወጣው፡፡
አራት ክለቦች ለመጀመሪያ ግዜ በቻምፒየንስ ሊጉ ምድብ ሲሳተፉ ቀሪ 12 ክለቦች ለምድብ ጨዋታዎች አዲስ አይደሉም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጥሎ ወደ ምድብ ያለፈው የዩጋንዳው ኬሲሲኤ ከስምንት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ አል አህሊ እና ኤስራንስ ጋር ተደልድሏል፡፡ አል አህሊ እና ኤስፔራንስ የ2017 ቻምፒየንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ጨዋታን ላይ ተገናኝተው ነበር፡፡
ምድብ ሁለት የሞት ምድብ ነው፡፡ ቲፒ ማዜምቤ እና ሶስት የሰሜን አፍሪካ ክለቦችን የያዘውን ይህ ምድብ ከሌሎቹ በተለየ ጠንካራውን ምድብ ነው፡፡ የሞሮኮው ኤል ጃዲዳ የአልጄሪያዎቹ ኤምሲ አልጀር እና ሴቲፍ ይገኙበታል፡፡ በ2015 ሶስት የአልጄሪያ ክለቦች (ሴቲፍ፣ ኤምሲ ኤል ኡልማ እና ዩኤስኤም አልጀር) በአንድ ምድብ ከተገኙ በኃላ አሁን ላይ ሁለት የአልጄሪያ ክለቦች ዳግም በአንድ ምድብ ተገኝተዋል፡፡
የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮን ዋይዳድ ካዛብላንካ አምና ከውድድር ያስወጣውን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ አሁንም አግኝቷል፡፡ ሁለቱ የምዕራብ አፍሪካ ክለቦች ፖርት ቶጎ እና ሆሮያም በምድብ ሶስት ተገኝተዋል፡፡
የ2016 የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ የዛምቢያው ዜስኮ ዩናይትድ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኃላ ወደ ቻምፒየንስ ሊጉ ሲመለስ ከኤትዋል ደ ሳህል እና ከ2013 ወዲህ ወደ ምድብ በመግባት የመጀመሪያው የአንጎላ ክለብ ከሆነው ፕሪሜሮ አጉስቶ እና የመጀመሪያው ግዜ ተሳታፊ የሆነው ምባባኔ ስዋሎስ ጋር ተደልድሏል፡፡
ሙሉ ድልድል
ምድብ ሀ
አል አህሊ (ግብፅ)
ታውንሺፕ ሮለርስ (ቦትስዋና)
ኬሲሲኤ (ዩጋንዳ)
ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ (ቱኒዚያ)
ምድብ ለ
ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)
ኤምሲ አልጀር (አልጄሪያ)
ዲፋ ኤል ጃዲዳ (ሞሮኮ)
ኢኤስ ሴቲፍ (አልጄሪያ)
ምድብ ሐ
ኤኤስ ፖርት ቶጎ (ቶጎ)
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ)
ዋይዳድ ካዛብላንካ (ሞሮኮ)
ሆሮያ (ጊኒ)
ምድብ መ
ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ)
ፕሪሜሮ አጉስቶ (አንጎላ)
ኤትዋል ደ ሳህል (ቱኒዚያ)
ምባባኔ ስዋሎስ (ስዋዚላንድ)