በእግር ኳስ አስፈላጊ የሚባሉ እና በልምምድ ወቅት ትኩረት የሚሰጣቸው መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህን በአግባቡ ማከናወንም ለውጤታማነት እንደሚያበቃ ግልጽ ነው፡፡ በቴክኒክ የላቁ ፣ በታክቲኩ የሰለጠኑ እና በአካል ብቃት የዳበሩ ተጫዋቾች ለአንድ ቡድን ወሳኝ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ባሻገር ግን ብዙም ትኩረት ሲሰጠው እና ሲወራለት የማናስተውለው ስነ-ልቦና እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡
የስነልቦናን ጥቅም ለመረዳት ርቀን መሄድ አይጠበቅብንም፡፡ በቅርቡ ወላይታ ድቻ በዛማሌክ ላይ ያስመዘገበውን ድል መመልከት በቂ ነው፡፡ ከጨዋታው በፊት አነስተኛ በአንዳንድ አካላት ደግሞ ምንም ግምት ያልተሰጣቸው ድቻዎች ከእነርሱ በብዙ ደረጃ ልቆ የሚገኘውን ዛማሌክን ከኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር ማሰናበት ችለዋል፡፡ እግር ኳስ እንደዚህ ነው፤ እችላለሁ ብሎ የተነሳ ቡድን ውጤትን ሊያስመዘግብ ይችላል፡፡ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃም ከግብጽ መልስ እንደተናገሩት ሳይፈሩ እና ሳይሸበሩ መጫወታቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡ ገና ጨዋታ ሳይጀመር የቡድንን ታላቅነት ተመልክቶ መሸበር የኛ ሀገር ክለቦች ችግር ቢሆንም ይህንን ግን በዚህ ቡድን ላይ አላስተዋልንም፡፡
የዓለማችን ውጤታማ አሰልጣኞች የሆኑት ሰር አልክስ ፈርጉሰን እና ካርሎ አንቸሎቲ በስነ-ልቦናው ረገድ ያላቸው አሰራር ለውጤታማነታቸው ዋናው ምክንያት ተደርጎ ይነሳል፡፡ ተጫዋቾችን የሚያነሳሱበት መንገድ ለረጅም ዘመናት ፉክክር በበዛበት እና ተቀያያሪ በሆነው የአውሮፓ ውድድር ውጤታማ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡ ሰር አሌክስ እስከ መጨረሻ ደቂቃ በሚታገለው እናም ከመመራት በመነሳት ውጤት በሚያስመዘግበው ቡድናቸው ይታወቃሉ፡፡ አንቸሎቲ በበኩላቸው በባህሪ አስቸጋሪ የሚባሉ ተጫዋቾችን በመልካም ሁኔታ መያዝ እና ማነሳሳት መቻላቸው መለያቸው ነው፡፡
ወደ ሀገራችን መለስ ስንል ደግሞ በ2005 ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ እና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ምዕራፍ ድረስ መጓዝ የቻለውን የሰውነት ቢሻውን ስብስብ እናስታውሳለን፡፡ የቡድኑ የተነሳሽነት መንፈስ እና የማሸነፍ ፍላጎት በዛን ጊዜ ለተመዘገቡ ዉጤቶች ዋንኛ ምክንያት ነው፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት ምሳሌዎች ማየት እንደምንችለው ስነ-ልቦና ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው፡፡
በአርሰናል ክለብ ውስጥ የስነልቦና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ቲም ኦብራየን በ2016 ከጎል ድረገፅ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህን ብለው ነበር። “ስነ-ልቦናዊ ዝግጅት የሚያደርጉ ተጫዋቾች ከማያደርጉ በተሻለ የተለያዩ ፈተናዎችን የመወጣት አቅም አላቸው፡፡ ቡድንን መምራት እና ማነሳሳት የአምበሎች ተግባር ብቻ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ተጫዋቾች በተለያየ መንገድ የቡድናቸው መንፈስ እንዳይረበሽ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ፡፡ ልክ ሰዎች የተለያየ አመለካከት እንዳላቸው ሁሉ ቡድኖችም የራሳቸው የሆነ መገለጫ አላቸው፡፡ ስራ በጀመርኩበት ወቅት የተሳሳቱ አመለካከቶችን አስተውያለሁ፡፡ አንዳንድ ተጫዋቾች አእምሮአዊ ጥንካሬ አላቸው፤ ሌሎች ደግሞ የላቸውም የሚል፡፡ ነገር ግን እከሌ ደካማ ነው ለማለት የሚያስችል መሰረታዊ መረጃ የለም፡፡”
በ2016 ማንም ሳይጠብቃቸው የእንግሊዝ ፒሪሚየር ሊግን በማሸነፍ ታሪክ የሰሩት ሌስተር ሲቲዎች በስነ-ልቦናው ረገድ ጠንክረው መስራታቸው ለውጤታማነታቸው አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡ የክለቡ የስነ-ልቦና ባለሞያ ብራዲሊ ቡስሽ ይህንን አስመልክተው ከታይምስ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዲህ ብለዋል። “ስለ ስነ-ልቦና ያለው አመለካከት እየተቀየረ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም በሚዲያው የሚሰጠው ሽፋን በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የነርቭ ህክምና እና ዘመናዊ አሰራር እየጎለበተ መምጣት በዘርፉ ላይ ያለን እውቀት እንዲጨምር ረድቷል፡፡ ውሳኔን ለመወሰን እና ነገሮችን ለማውጠንጠን የምንጠቀምበት የፊተኛው የአንጎል ክፍል አለ፡፡ ይህ ክፍል ከጫና ነጻ ሲሆን ነገሮችን በአግባቡ እና በጥራት ማከናወን ይችላል፡፡ ዶፓሚን የምንለው ሆርሞን ጉልበትን ሲሰጠን የጭንቀት ሆርሞን የሆነው ኮርቲሶል አቅማችንን በአግባቡ እንዳንጠቀም እከል ይፈጥርብናል፡፡”
ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ከጭንቀት ነፃ የሆነ እና የአሸናፊነት ዝግጅት ያለው አዕምሮ የውጤታማነት መሰረት እንደሆነ ነው፡፡ አሰልጣኞችም ይህን ስለሚረዱ በተቻለ መጠን ተጫዋቾቻቸው ከተጽዕኖ ነጻ ሆነው እንዲጫወቱ ይጥራሉ፡፡ ደጋፊም ሆነ ሚዲያ ከፍተኛ ወቀሳ እና ትችት በሚያደርስበት ወቅት ያንን ለመወጣት ተጫዋቾች የተለያዩ የስነ-ልቦና ዘዴዎችን መጠቀም ይችላሉ፡፡
በእግርኳሱም ሆነ በሌሎች ስፖርቶች ውስጥ የሚሠሩ የስነ-ልቦና ባለሞያዎች ተጫዋቾቹ እንደማንም ሰው ሊያጋጥማቸው ከሚችል የአዕምሮ ጤና መታወክ በተጨማሪ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ እና አቋም ጋር በተያያዘ የሚኖሩ ችግሮች መሠረትን በማጥናት መፍትሄ የመስጠት ሃላፊነት አለባቸው።
በልምምድ ክፍለጊዜ ጥሩ ብቃትን አሳይተው በጨዋታዎች ላይ ግን ይህንን ለመድገም የማይችሉ ተጫዋቾች ጉዳይ በዋንኛነት በቡድኖቹ የስፖርት ሳይኮሎጂስቶች መፍትሄ የሚያገኝ ነው። ተጫዋቾች ጉዳት ሲያጋጥማቸው የሚፈራረቁባቸው እንደ ንዴት (Anger)፣ ሁኔታውን አለመቀበል (Denial)፣ ማመቻመች (Bargaining)፣ ከፍተኛ የሆነ የድብርት ስሜት (Depression) ያሉ አሉታዊ ስሜቶች ከስፖርተኞቹ ጋር በቅርበት በሚሰሩ ባለሞያዎች መልስ ያገኛል።
የራስ መተማመን ስሜት መውረድ፣ የትኩረት ማጣት፣ ተስፋ መቁረጥ እና መሠልቸት፣ ዝቅተኛ ተነሳሽነት እንዲሁም የአላስፈላጊ ሱስ እና የአመጋገብ ችግሮች በስፖርት ስነ-ልቦና ውስጥ በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ችግሮች ሲሆኑ በአግባቡ በሰለጠኑ የዘርፉ ባለሞያዎች እና በስፖርተኞቹ ጥረት በበቂ ሁኔታ ሊስተካከሉ ይችላሉ። ተጫዋቾች እንደ ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በሚኖራቸው የፍቅር፣ የጓደኝነት እና ሌላ አይነት ትስስር ውስጥ የሚያጋጥማቸው ችግሮች በሜዳ ላይ ለሚያሳዩት አቋም በጥሩም ሆነ በመጥፎ ጎን ተፅዕኖ የሚያሳርፍ እንደመሆኑም በባለሞያዎቹ ትኩረት ይደረግበታል።
የስፖርት ስነ-ልቦና ሚና በእግርኳሱ እየገዘፈ መምጣቱን ተከትሎ በተለይ በአውሮፓውያኑ ትልቅ ስፍራ ተሠጥቶታል፤ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር (FA) የስፖርት ስነ-ልቦና አሰጣጥ እና አተገባበር ስርአት (Manual) እያዘጋጀ መሆኑ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ በሃገራችን በሚገኙ ክለቦችም ሆነ በሁለቱም ፆታ በየዕድሜ እርከኑ በሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች በዘርፉ በቂ ዕውቀት እና የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ባለሞያዎች ማሠራት በአጭር ጊዜ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ የሚረዳ በመሆኑ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው። በጉዳዩ ዙሪያም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በስፋት ሊመክሩ እና ሊወያዩ ይገባል፡፡