በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ወደ ምድብ ለማለፍ የሚደረጉ ጨዋታዎች ረቡዕ በተደረገ ስነ-ስርዓት ታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ክለቦች የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻም ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የኮንጎ ሪፐብሊኩን ካራ ብራዛቪልን ሲገጥም ወላይታ ድቻ ከታንዛኒው ያንግ አፍሪካንስ ጋር ይፋለማል፡፡
ፈረሰኞቹ ዳግም ወደ ኮንጎ የመሄድ እጣ ደርሷቸዋል፡፡ አምና በቻምፒየንስ ሊጉ ወደ ዶሊሲ አቅንተው ኤሲ ሊዮፓርድስን ሲገጥሙ አሁን ደግሞ የመዲናዋ ክለብ የሆነውን የካራ ብራዚቪልን አግኝተዋል፡፡ የኮንጎ ብሄራዊ ቡድን እና የፈረሰኞቹ ዳግም ወደ ኮንጎ የመሄድ እጣ ደርሷቸዋል፡፡ የኮንጎ ብሄራዊ ቡድን እና የdrcpf.net የእግርኳስ ዘጋቢ የሆነው ፓቼል ምፓን ድልድሉ ለካራ ብራዚቪል የተሻለ ነው ሲል ለሶከር ኢትዮጵያ ሃሳቡን አካፍሏል፡፡ “ካራ በመጪዎቹ ሁለት ወሳኝ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች መልካም ውጤት ማስመዝገብ ይችላል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚከበር ቡድን ቢሆንም ካራ በአሁን ወቅት በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህም ማሳያው በኮንፌድሬሽን ዋንጫው የቱኒዚያ ክለብ ከውድድር ማስወጣቱ ነው፡፡” ብሏል፡፡
ካራ በሁለቱም ዙሮች ከውድድር ያስወጣቸው ክለቦች ጠንካራ ነበሩ፡፡ ለዚህም ይመስላል ፓቻል ካራ ወደ ምድብ የማምራት ከፈረሰኞቹ የተሻለ እድል እንዳለው የሚያብራራው፡፡ “ከሜዳ ውጪ መጫወት ቀላል አይደለም፡፡ ቢሆንም ካራ በሁለቱ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች እድል አለው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጥንካሬ እና በየትኛውም ወቅት አደገኛ ነገሮችን መፍጠር እንደሚችሉ እገነዘባለው፡፡” ሲል ሃሳቡን አጠቃሏል፡፡
ወላይታ ድቻ ወደ ዳሬ ሰላም አቅንቶ ያንግ አፍሪካንስ የሚገጥምበት ሌላኛው ጨዋታ ነው፡፡ ለታንዛኒያው ጋርዲያን የሚሰራው ሚካኤል ሙዌቤ ድልድሉ ለያንጋ መልካም ነው ይላል፡፡ “እንደእኔ ሃሳብ ከብዙ ነገሮች አንፃር ድልድሉ ለያንጋ መልካም የሚባል ነው፡፡ ያንጋን ብዙ ግዜ የሚያስቸግሩት የሰሜን እና የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት ክለቦች በመሆናቸው ይህ የተሻለ ነው ማለት ነው የምችለው፡፡”
ሚካኤል ሲቀጥል ጠንካራ የአፍሪካ ክለቦችን አለማግኘት ለያንጋ አዎንታዊ ጎን እንዳለው ያስረዳል፡፡ “እንደኢኒየምባ፣ ዩኤስኤም አልጀር፣ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ፣ አል መስሪ እና ሲአር ቤሎዝዳድ ያሉትን ክለቦች ሳያገኙ ከድቻ ጋር በመጫወታቸው ያንጋዎች ፈፅሞ ደስተኛ ናቸው፡፡ ድቻ በብዙዎች ስለማይታወቅ የተወሰኑ ደጋፊዎች እንዲሁም ሚዲያዎች ከሚገባው በላይ ለያንጋ ቀላል ጨዋታ እንደሚሆን እየተናገሩ ነው፡፡”
የሚካኤልን ሃሳብ የሚያንፀባርቁ የታንዛኒያ እለታዊ ጋዜጦችም በዛሬው ቀን የፊት ገፆቻቸውን ከያንጋ እና ድቻ ጨዋታ ጋር ፅሁፎችን ይዘው ወጥተዋል፡፡
“ያንጋ ወደ አስቸጋሪዎቹ የሰሜን አፍሪካ ሜዳዎች መሄድ ባይጠበቅበትም ወደ ምድብ ለማግባት ቀላል የማይባል ፈተና መወጣት ይጠበቅበታል፡፡” ጋዜጣው ስለወላይታ ድቻ ዛማሌክን ከውድድር ማስወጣት በፅሁፉ ላይ አትቷል፡፡ (ቢንግዋ)
“ያንጋ ደካማ ተጋጣሚ ደረሰው፡፡” ጋዜጣው ወላይታ ድቻን ደካማ ቡድን ብሎታል (ምዋናናቺ)
“ካፍ ያንጋን ወደ ገንዘብ ቅንጫቱ ዙር ወሰደ፡፡ ድልድሉ ሲበዛ መልካም ነው፡፡” (ምዋናስፖቲ)