በ11ኛው ሳምንት ሊካሄድ የነበረውና በርካታ የአክሱም ተጫዋቾች ታመዋል በሚል ምክንያት ተላልፎ ዛሬ የተደረገው የለገጣፎ ከተማ እና አክሱም ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል። የአወዳዳሪው አካል በርካታ የስራ ኃላፊዎች የተከታተሉት ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ እና የጎል ሙከራ ድርቅ የመታው ነበር።
በእንቅሳቃሴ የተሻሉ የነበሩት አክሱም ከተማዎች ሙሉጌታ ብርሃኑ በሞከረውና የግቡ በመለሰበት ሙከራ የግብ እድል ፈጥረዋል። በ32ኛው እና 41ኛው ደቂቃ ላይ ሀፍቶም ገብረ እግዚአብሔር እና ልዑልሰገድ አስፋው ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገውም ነበር። በአንፃሩ ለገጣፎች በሚታወቁበት ዘይቤ ኳስን መስርተው መጫወት ተስኗቸው ተስተውለዋል።
ከዕረፍት መልስ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ የነበሩት ለገጣፎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልክ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። በተለይም በ47ኛው እና 68ኛው ድቂቃ ላይ ፋሲል አስማማው ለግብ የቀረበ ሙከራ ያደረገ ሲሆን ከሳጥን ውጭ በተደጋጋሚ በመሞከር አደጋ ሲፈጥር የነበረው ዳዊት ቀለመወርቅ በ73ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ሞክሮ ግብ ጠባቂው አድኖበታል።
በተቃራኒው መከላከልን አዘንብሎ መጫወት የመረጠው አክሱም ከተማ በረጃጅም ኳስ የተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ሲደርስ የተስተዋለ ቢሆንም የጠራ የጎል እድል ለመፍጠር ተቸግሯል። በ81ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ላይ ወደ ግብ ክልል የተሻገረውን ሀዱሽ ፀጋዬ በነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ቢያገኘውም ወደ ግብነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ በግቡ አግዳሚ ታካ የወጣችበት አጋጣሚ በአክሱም በኩል የታየው ንፁህ የግብ እድል ነበር። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው 5 ደቂቃ ግብ ፍለጋ ተጭነው የነበሩት ለገጣፎች ሳይሳካላቸው ያለምንም ግብ ጨዋታው ተጠናቋል።