በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት በሜዳው ሀዋሳ ከተማ ስታድየም ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ 1-0 በማሸነፍ ሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽን በድል አሟሽቷል፡፡
እንደተለመደው በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ታጅቦ በተጀመረው ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ በኩል ዳንኤል ደርቤን ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ሲካተት ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር በዝግጅት ላይ የነበረው መሳይ ጳውሎስን አካተው በማሰለፍ በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገቡ ጅማ አባ ጅፋር አዲስ ፈራሚው አሮን አሞሃን ለመጀመርያ ጊዜ የመሰለፍ እድል በመስጠት በ4-4-2 አደራደር ለጨዋው ቀርቧል፡፡
በጨዋታው ሀዋሳ ከተማዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን የጅማን በር ማንኳኳት የጀመሩትም ገና ጨዋታው በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ በኩል ደስታ ዮሀንስ ያሻማትን ኳስ እስራኤል እሸቱ በግንባሩ ገጭቶ ዳንኤል አጄይ በያዘበት ሙከራ ነበር፡፡ በተደራጀ ሁኔታ በሁለቱም መስመሮች በሚገኙት የመስመር ተከላካዮች (ዳንኤል ደርቤ እና ደስታ ዮሀንስ) በመታገዝ የአባጅፋር የተከላካይ መስመርን መፈተናቸውን የቀጠሉት ሀዋሳዎች በቶሎ መሪ ሊሆኑ የሚችሉባቸው እድሎች መፍጠር ችለው የነበረ ቢሆንም በእለቱ ድንቅ የነበረው ጋናዊው ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጄይ ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል፡፡ በ12ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከታፈሰ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጅማ የግብ ክልል በመግባት የሞከረው ፣ በ14ኛው ደቂቃ ደስታ ዮሀንስ ከርቀት ወደ ግብ አክርሮ የመታው እንዲሁም በ16ው ደቂቃ ላይ ጅብሪል አህመድ ከዳንኤል ደርቤ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ የሞሯቸው ኳሶች የጋናዊው ግብ ጠባቂ ሲሳይ የሆኑ ናቸው፡፡ ጅማ አባጅፋሮች በመጀመሪያው አጋማሽ የፈጠሩት አንድ የግብ አጋጣሚ ሲሆን 28ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል አጄይ በረጅሙ ከራሱ የግብ ክልል የላካትን ኳስ ኦኪኪ ጋር ደርሳ ናይጄርያዊው በነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ተመስገን ገ/ኪዳን ቢያመቻችለትም ተመስገን የሞከረውን ሙከራ ሶሆሆ ሜንሳህ በቀላሉ አድኖበታል፡፡
32ኛው ደቂቃ ላይ የጅማው ተከላካይ አዳማ ሲሶኮ በግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ ነክቷል በሚል የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች ቅሬታቸውን በፌድራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ላይ አሰምተዋል፡፡ ከዚህ ክስተት በኋላም የተሸሉ የነበሩት ሀዋሳዎች ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን አምክነዋል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ አምበሉ ደስታ ዮሀንስ ከራሱ የግብ ክልል እየገፋ ወደ ጅማ የግብ ክልል በመግባት ለሙሉዓለም ያሸገረለትን ኳስ አንጋፋው አማካይ በምርጥ ሁኔታ ዳንኤል አጄይን የመመለስ እድል ሳይሰጠው በማስቆጠር ሀዋሳን ቀዳሚ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ጅማ አባ ጅፋሮች ከመጀመርያው አጋማሽ ተሻሽለው በቀረቡበት ሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ የአቻነት ጎልን ፍለጋ ሁለት አጥቂዎችን ቀይረው በማስገባት በማጥቃት ወረዳው የተጫዋች ቁጥር ለማብዛት ጥረት ቢያደርጉም የጠራ የግብ አጋጣሚን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ይልቁንም ሀዋሳ ከተማዎች የግብ ሙከራዎች በማድረጉ ረገድ የተሸሉ ነበሩ፡፡ ለአብነትም እስራኤል እሸቱ በ52ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ታፈሰ ሰለሞን አሻግሮለት ሳይጠቀምበት የቀረው ፤ በ70ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ፍቃዱ ከግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄይ ጋር አንድ ለአንድ አገናኝቶት ያመከነው ፤ እንዲሁም ከስድስት ደቂቃዎች በኃላ በድጋሚ ዳዊት አሻግሮለት ሳይጠቀምባቸው የቀራቸው ኳሶች የሀዋሳን ሪነት አስተማማኝ የሚያደርጉ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡
በጅማ አባ ጅፋር በኩል በሁለተኛው አጋማሽ ልትጠቀስ የምትችለው ብቸኛ አጋጣሚ በጭማሪ ደቂቃ ላይ እንዳለ ደባልቄ በጭንቅላቱ ገጭቶ ሶሆሆ ሜንሳህ እንደምንም ያወጣበት ሙከራ ሲሆን ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ውጤቱ ሁለተኛ ተከታታይ ድል ያስመዘገበው ሀዋሳ ከተማን በ21 ነጥቦች ደረጃውን ወደ 8ኛ ከፍ እንዲል ሲረዳው ከ5 ጨዋታ በኋላ ሽንፈት የገጠመው ጅማ አባ ጅፋር 25 ነጥቦች ላይ ረግቶ ወደ 4ኛ ተንሸራቷል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ
ሁለተኛውን ዙር በጥሩ ሁኔታ መጀመራችን ለኛ አንድ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ማሸነፋችንም ጥሩ ነው፡፡ ከዛ ባለፈ እያሸነፍን በመጣን ቁጥር ለቀጣይ ጨዋታዎች ስንቅ ይሆነናል፡፡ ለዋንጫ ነው የምንፎካከረው ለማለት ግን ይከብደኛል፡፡ ይህን ለመናገር ገና ብዙ ጨዋታዎች አሉ፡፡
እኔ ለሙሉዓለም ረጋሳ እድሉን ብቻ ነው ያመቻቸሁለት፡፡ እሱም በውስጡ ያለውን ነገር ሜዳ ላይ እያሳየ ያለ ጥሩ ተጫዋች ነው፡፡
ገ/መድህን ሀይሌ – ጅማ አባጅፋር
በመጀመሪያው አርባ አምሰት እነሱ ብልጫ ነበራቸው፡፡ በሁለተኛ አጋማሽ ግን ያን ለመቀልበስ ጥረት አድርገናል፡፡ ሜዳው ተጫዋቾቼን እንደፈለጉ እንዲንቀሳቀሱ አላደረጋቸውም፡፡ ሽንፈት ያጋጥማል ፤ የተጫወትነውም ከሜዳ ውጪ ከመሆኑ አንጻር ሽንፈቱ የሚያጋጥም ነው፡፡ በቀጣይ ተሸሽለን እንቀርባለን፡፡