በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ ወልዲያን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 3-1 በመርታት በወቅታዊ ምርጥ አቋሙ ገፍቶበታል፡፡ ጨዋታው አወዛጋቢ ውሳኔዎች እና አስደንጋጭ ጉዳት የታየበት ሆኖም አልፏል፡፡
ጉሸሚያ የበዛበት እና እምብዛም ማራኪ እንቅስቃሴ ባልታየበት የመጀመርያ አጋማሽ ኢላማቸውን ያልጠበቁ በርካታ ሙከራዎች የተስተዋሉበት ሲሆን በኳስ ቁጥጥር አዳማዎች የተሸሉ ነበሩ፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ ትኩረት ከሳቡት ጉዳዮች መካከል ከአንድ ወር ጉዳት በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሰው ሱራፌል ዳኛቸው በ9ኛው ደቂቃ ሱሌይማን ያሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ በቀኝ መስመር ወደ ወልድያ የግብ ክልል በሚገፋበት ወቅት ብርሀኔ አንለይ ከኃላው ደርሶ ኳሱን ሲያወጣበት ቢወድቅም የዕለቱ ዳኛ ፊሽካ ሳያሰሙ ጨዋታው ቀጥሏል፡፡ ሆኖም ሱራፊል ከወደቀበት መነሳት ባለመቻሉ በቀጥታ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ በምትኩ ኤፍሬም ዘካርያስ ወደ ሜዳ ገብቷል።
የወልዲያ የመከላከል እንቅስቃሴ ተጭነው የመጫወት ዕድል የከፈተላቸው አዳማዎች በዳዋ ሆቴሳ እና ቡልቻ ሹራ በርካታ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። በ16ኛው ደቂቃ ቡልቻ በግንባሩ የገጫት ኳስ ተከላካዩ ቢያድግልኝ ሲያወጣበት በ24ኛው ደቂቃ በግራ መስመር በረከት ደስታ በሁለት ተከላካዮች መሀል ያሳለፍለትን ኳስ ቡልቻ ወደግብነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ በአግባቡ ኳሱን ሳይቆጣጠር የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ታኮ ወጥቶበታል። በረከት ደስታ በ30ኛው ደቂቃ ላይ የመታው ኳስ በተከላካዮች ተደርቦ ወደ ውጪ ሲወጣ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ በግንባሩ ገጭቶ ወደግብነት ቢለውጠውም ከጨዋታ ውጭ አቋቋም ላይ ነው በሚል ግቡ ሳይፀድቅ ቀርቷል። በ42ኛው ደቂቃ ላይም ዳዋ የሞከረው ኳስ በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥታበታለች። በ45ኛው ደቂቃ ከነዓን ማርክነህ ከዳዋ የተሰጠውን ኳስ በአግባቡ በመቆጣጠር ሁለት ተጫዋቹችን አልፎ ወደ 16 የግብ ክልል ውስጥ ሲገባ በወልዲያ ተከላካይ ጥፋት ተፈፅሞብኛል በሚል ቢውድቅም የዕለቱ ዳኛ ሚካኤል አርአያ ጨዋታው እንዲቀጥል በመፍቀዳቸው በስፖርት ቤተሰቡ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
በጨዋታው ብዙም ወደፊት አትቅተው መጫወት ያልቻሉት ወልዲያዋች በ3ኛው ደቂቃ ላይ አማራ በቀለ ከርቀት መትቶ ብዙም አደጋ ሳይፍጥር በግቡ አናት ላይ ከወጣችበት አጋጣሚ በኋላ ሌላ የግብ እድል ለመፍጠር 32 ደቂቃዎች አስፈልጓቸዋል፡፡ በ35ኛው ደቂቃ ላይ አማረ በቀለ እና አንዱዓለም ንጉሴ አንድ ሁለት ተቀባብለው ወደ ግብ የመቱት ኳስ ግብ ጠባቂውን ቢያልፈውም ምኞት ደበበ ደርሶ ያወጣው እንዲሁም በ40ኛው እና በ42ኛው ደቂቃዎች ተስፋዬ አለባቸው እና ያሬድ ሀሰን ከርቀት የሞከሯቸው ሙከራዎች በወልዲያ በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ የታዩ ነበሩ። የመጀመሪያው አጋማሽ በዚህ መልኩ ያለግብ ሲጠናቀቅ ዳኞቹ ወደመልበሻ ክፍል በሚያመሩበት ጊዜ ከደጋፊው ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
ከዕረፍት መልስ ጎል ፍለጋ ተጭነው የተጫወቱት አዳማ ከተማዎች አሸናፊ የሆኑባቸውን ጎሎች ያስቆጠሩት ቢህኛው አጋማሽ ነበር፡፡ በ48ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ ተጎትቶ ወድቋል በሚል የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ዳዋ ሆቴሳ ወደ ግብነት ለውጦ አዳማ ከተማን መሪ አድርጓል።
በፍፁም ቅጣት ምቱ መሰጠት ያልተስማሙት ወልድያዎች ክስ አስመዝግበወው ጨዋታው የቀጠለ ሲሆን የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ ሆኖም በ56ኛው ደቂቃ ተስፋዬ አለባቸው የሞከረውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ጃፋር ተቆጣጥሮ ለከነዓን ማርክነህ በፍጥነት ያሻገረውን ኳስ ከነዓን በረጅሙ ወደፊት ሲያሻግረው ግብ ጠባቂው ደረጄ አለሙ ኳሱን ለማራቅ ከግብ ክልሉ ቢወጣም በፍጥነቱ የሚታወቀው ዳዋ ሆቴሳ ቀድሞ ኳሷን በማግኘት የአዳማ ከተማን መሪነት መሪነት ወደ 2-0 ከፍ ያደረገች ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ ወልዲያዎች መረጋጋት የተሳናቸው ሲሆን በ61ኛው ደቂቃ በመሀል ሜዳ በሰሩትን የቅብብል ስህተት በመጠቀም አዳማዎች በዳዋ እና በረከት አማካኝነት በፍጥነት ወደ ወልዲያ የግብ ክልል ደርሰው በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ቡልቻ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ የተሰለፈው ደረጄ አለሙ በድጋሚ የክብ ክልሉን ለቆ የመውጣቱ በቀላሉ የቡድኑን ሶስተኛ ጎል አስቆጥሯል።
ከግቡ መቋጠር በኃላ አጥቅተው መጫወት የመረጡት ወልዲያዋች በአንዱዓለም እና አማረ አማካኝነት አስደንጋጭ የማባሉ ሙከራዎች አድርገው በመጨረሻም በ78ኛው ደቂቃ ላይ ቢያድግልኝ ኤልያስ ከቅጣት ምት በቀጥታ ግብ አስቆጥሮ ወልዲያን ከመሸንፍ ያላዳነች ግብ አስቆጥሯል። በ85ኛው ደቂቃ በግማሽ አመቱ አዳማን የተቀላቀለው ጫላ ተሽታ የግብ ልዩነቱን ወደ ሊያሰፋ የሚችልበትን ዕድል ሳይጠቀምበት የቀረ ሲሆን ጨዋታውም በአዳማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በውጤቱ መሰረት ለ28ኛ ጊዜ በተከታታይ በሜዳው ያልተሸነፈው አዳማ ከተማ ነጥቡን 26 በማድረስ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ወልዲያ በ18 ነጥቦች ወደ 11ኛ ዝቅ ብሏል።