የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ሲጀመር ወደ ይርጋለም የተጓዘው ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን 1-0 አሸንፏል፡፡ ድሬዳዋ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ከባለሜዳው በተሻለ የተንቀሳቀሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ59ኛው ደቂቃ አቡበከር የመታውን ኳስ መሳይ አያኖ ሲመልሰው በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሳሙኤል ሳኑሚ ባስቆጠረው ጎል መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኋላ በደጋፊዎች በተነሳ ረብሻ የተቋረጠ ሲሆን ከ15 ደቂቃ መቋረጥ በኋላ በቀጠለው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና መሪነቱን አስጠብቆ በመውጣት በውድድር ዘመኑ ሁለተኛ የሜዳ ውጪ ድሉን አስመዝግቧል፡፡
ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
ጨዋታው ዛሬ ጥሩ ነበር ፤ ሆኖም ተሸንፈናል፡፡ ለዛሬው ሽንፈት ደጋፊውን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ላይ ቡድኑን የማስተካከል ስራ እየሰራን ነው፡፡ በቀጣይ ቡድኑን ወደቀደመ ውጤታማነቱ እንመልሰዋለን፡፡
ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና
ያሳካነው ጥሩ ውጤት ነው፡፡ ውጤቱ እንዲሁ ሳይሆን በጥሩ ስራ የተገኘ ነው፡፡ ስህተታችንን ማረም እና ጠንክሮ መስራት ለድል ያበቃናል፡፡ አሁንም ይሄ ድል ይቀጥላል፡፡
በጥሩ አቋም ላይ የማይገኙ ሁለት ቡድኖችን ያገናኘው የድሬዳዋ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ መሪዎቹ የሚጠጋበት ፤ ድሬዳዋ ከተማም ላለመውረድ በሚደረገው ትግል የሚያግዛቸውን እድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ድሬዋች በአትራም ኩዋሜ እና በረከት ይስሃቅ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመሐሪ መና አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል፡፡
ስምኦን አባይ
ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በርካታ የግብ እድልን በተጋጣሚያችን ላይ ብንወስድም ማስቀጠር አልቻልንም፡፡ ተጫዋቾቼ ከመጓጓት አንፃር ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ እነሱን መውቀስ አልፈልግም፡፡ ከፊታችን በርካታ ጨዋታወች ስላሉ በዛ ላይ ትኩረት እናደርጋለን ፡፡
ቫስ ፒንቶ
ዛሬ ሁለታችንም ያሳየነው እንቅስቃሴ ተመጣጣኝ ነው፡፡ እኛ ግን ባሰብነው ልክ ለመጫወት ብናስብም የተጎዱ ተጫዋቾች መኖራቸው አሁንም ክፍተታችንን እያጎላው መጥቷል ፡፡ የሳላሀዲን ሰይድ ፣ ሮበርት እና ናትናኤል ያለመኖር ምን ያህል ቡድኑን እንደጎዳው ማየት ይቻላል፡፡ ጊዮርጊስ አሸናፊ ቡድን ነው ፤ ወደ አሸናፊነት አንመለሳለን፡፡