ብሄራዊ ሊግ ፡ የምድብ 3 እና 4 ጨዋታዎች እሁድ ይካሄዳሉ

 

የውድድር እና ስነስርአት ኮሚቴው የየምድቦቹ ጨዋታዎች በየቀኑ በተከታታይ እንደሚደረጉ ትላንት ቢያስታውቅም አሁን ደግሞ የምድብ 3 እና 4 ጨዋታዎች እሁድ እንደሚደረጉ አስታውቋል፡፡ በዚህም መሰረት የምድብ 4 ጨዋታዎች በተመሳሳይ 2፡00 ላይ በሶስቱ ስታድየሞች ሲደረጉ የምድ 3 ጨዋታዎች በተመሳሳይ 4፡00 ላይ ይደረጋሉ፡፡

በዚህም መሰረት:-

የምድብ 3 ጨዋታዎች (ሁሉም በ2፡00 ይካሄዳሉ )

ወሎ ኮምቦልቻ ከ ሆሳእና ከነማ – ድሬዳዋ ስታድየም

አውስኮድ ከ ደቡብ ፖሊስ – ሳቢያን ሜዳ

ኢትዮጵያ መድን ከውሃ ስፖርት – መከላከያ

 

የምድብ 4 ጨዋታዎች (ሁሉም 4 ሰአት ይደረጋሉ)

ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከ ሰበታ ከነማ – ድሬዳዋ ስታድየም

ጅማ ከነማ ከ ሼር ኢትዮጵያ – ሳቢያን

መቐለ ከነማ ከ ሀላባ ከነማ – መከላከያ

Federal Police 2

ድሬዳዋ ከነማ እና ፌዴራል ፖሊስ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ጀምረዋል፡፡ ጠዋት በተደረጉት ጨዋታዎችም ድሬዳዋ ከነማ እና ፌዴራል ፖሊስ ወደ ሩብ ፍፃሜው ያለፉ ቡድኖች ሆነዋል፡፡

ዛሬ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የድሬዳዋ ከነማ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ የተጠበቀው ፉክክር ሳይታይበት በመሰረት ማኒ ቡድን 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ከድሬዳዋ የድል ግቦች ውስጥ በላይ አባይነህ 2 ግቦችን አስቆጥሮ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን በ4 ግብ ከጅላሎ ሻፊ ጋር እኩል መምራት ጀምሯል፡፡ ድሬዳዋ በማለፉና ፋሲል ከነማ ከውድድሩ በመሰናበቱ በላይ አባይነህ ተጨማሪ ግቦችን በማስቆጠር በከፍተኛ ግብ አግቢነት የማጠናቀቅ እድል አለው፡፡

ከድሉ በኋላ የድሬዳዋ ከነማዋ አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ደጋፊያቸው ለውጤት እንዳበቋቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ደጋፊ ውጤት መለወጥ የሚያስችል ኃይል እንዳለው በኛ ደጋፊዎች ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ ›› ሲሉ በውድድሩ ብቸኛዋ ሴት አሰልጣኝ የሆኑት መሰረት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ አጨዋወታችን በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ለዚህም ያስቆጠርናች ግቦች ብዛት ማሳያ ናቸው፡፡ አላማችን በቀጣይ ጨዋታዎች ጠንክረን በመቅረብ በድጋሚ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደግና ድሬዳዋም ተወካይ ክለብ እንዲኖራት ማድረግ ነው፡፡ ›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ፋሲል ከነማ በውድድሩ የመጀመርያ 3 ጨዋታዎች ሙሉ 9 ነጥቦች ሰብስቦ አስደናቂ አጀማመር ቢያደርግም ከሁለቱ ጨዋታዎች 1 ነጥብ ብቻ ማሳካት ተስኖት በአሳዛኝ ሁኔታ ከምድቡ ተሰናብቷል፡፡

በሳቢያን ሜዳ በተመሳሳይ ሰአት ጨዋታውን ያደረገው ፌዴራል ፖሊስ አርሲ ነገሌን 3-2 በማሸነፍ በ11 ነጥቦች በድሬዳዋ በግብ ልዩነት ተበልጦ ወደ ተከታዩ ዙር አልፏል፡፡ ኦሜድላ በሚለው ቀደምት ስሙ በርካቶች የሚያስታውሱት አንጋፋው ፌዴራል ፖሊስ 1 የውድድር ዘመን ወዳሳለፈበት ፕሪሚየር ሊግ ለመመለስ 180 ደቂቃዎች ብቻ ቀርተውታል፡፡

ከምድባቸው አስቀድመው መውደቃቸውን ያረጋገጡት ወልዋሎ እና ቡራዩ ከነማ 5፡00 ላይ ተገናኝተው ወልዋሎ 3-1 አሸንፏል፡፡ በጨዋታው ሲሊቶ አለሙ የወልዋሎን 3 ግቦች ከመረብ አሳርፎ ሐት-ትሪክ በመስራት በውድድሩ የመጀመርያው መሆን ችሏል፡፡

 

ነገ የምድብ 2 ሁለተኛው ሀላፊ ቡድን ይለያል

ውድድሩ ነገ ሲቀጥል ሶስቱም የምድብ 2 ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰአት ይካሄዳሉ፡፡ ጅማ አባ ቡና ከወዲሁ ወደ ሩብ ፍፃሜው ማለፉን በማረጋገጡ ነገ የሚጠበቀው አባ ቡናን ተከትሎ የሚያልፈው ቡድን ነው፡፡

የነገ ጨዋታዎች የሚከተሉት ናቸው (ሁሉም በተመሳሳይ 03፡00 ይካሄዳሉ)

ባቱ ከነማ ከ ሱሉልታ ከነማ – ድሬዳዋ ስታድየም

አዲስ አበባ ከማ ከ ጅማ አባ ቡና – መከላከያ ሜዳ

ናሽናል ሴሜንት ከ ሻሸመኔ ከነማ – ሳቢያን ሜዳ

የዚህን ምድብ የደረጃ ሰንጠረዥ አስቀድሞ ማለፉን ያረጋገጠው ጅማ አባ ቡና በ10 ነጥቦች ሲመራ አዲስ አበባ ከነማ በ7 ይከተላል፡፡ ባቱ ከነማ 6 ነጥቦች ሲሰበስብ ናሽናል ሴሜንት እና ሻሸመኔ ከነማ 4 ነጥብ አላቸው፡፡ ሱሉልታ በ3 ነጥብ መውደቁን አረጋግጦ ከግርጌ ተቀምጧል፡፡

——- የየምድቦቹን የደረጃ ሰንጠረዥ ፣ ውጤቶች ፣ ቀጣይ ጨዋታዎች እና ከፍተኛ ግብ አግቢዎች ደረጃ ለማወቅ ሜኑ ላይ Competiotions ላይ ከሚመጡት አማራጮች Ethiopian National League ቀጥሎም Tables ይጫኑ ——–

 

ፎቶ – ከምድብ 1 ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀሉት ድሬዳዋ ከነማ (ከላይ) እና ፌዴራል ፖሊስ (ከታች)

ያጋሩ