ሪፖርት | ወላይታ ድቻ በጥንካሬው ገፍቶበታል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት የዛሬ ብቸኛ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ሶዶ ላይ መሪው ደደቢትን አስተናግዶ በአምረላ ደልታታ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ሁለተኛውን ዙር በድል ጀምሯል፡፡

ከማለዳው ሁለት ሰአት ጀምሮ ወደ ስታድየሙ መትመም የጀመረው የከተማዋ ነዋሪ ረጃጅም ሰልፎችን በመስራት ሰባት ሰዐት ከመሆኑ በፊት ስታድየሙን ሞልቶታል። እድሉን ያላገኘው ቀሪ ደጋፊም በዛፎች ፣ ዳገቶች እና ህንፃወች ላይ በመንጠላጠል ጨዋታውን ለመከታተል ተገዷል። ሁኔታው በስታድየሙ ውስጥ በፈጠረው መጨናነቅ ምክንያትም የተወሰኑ ደጋፊዎች ተረጋግጠው በደረሰባቸው ጉዳት ወደ ሆስፒታል እስከማምራት ደርሰዋል። ይህ ሁሉ እንዲሆን ያደረገው የወላይታ ድቻ የአፍሪካ መድረክ የመጀመሪያ ተሳትፎ የተገኘው ውጤት ነበር። በዛማሌክ ላይ የተመዘገበው ድል የሳምንት ዕድሜ ቢያስቆጥርም በከተማዋ እና በዛሬው ጨዋታ ላይ የተለየ ስሜት መፍጠሩ አልቀረም። እንዲህ ባለ የደጋፊ ድባብ የደመቀው ጨዋታ 8፡30 ላይ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ማህበር ደደቢቶችን በተቀበለበት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አዘል ባነር እንዲሁም ደደቢቶች ባሰሩት ደስታችሁ ደስታችን ነው የሚል ባነር ስጦታ ልውውጥ ተደርጎ ቡድኖቹ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ ወላይታ ድቻዎች ጌታነህ ከበደ ቅጣቱን አላጠናቀቀም በማለት ክስ ያስመዘገቡ ሲሆን ከሲዳማ ቡና በውሰት ያመጡትን የመስመር ተጫዋች ፀጋዬ ባልቻን አካተው በ4-5-1 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል። ደደቢቶች በአንፃሩ የአራት ጨዋታ ቅጣት ሰለባ የነበረውን ጌታነህ ከበደን ፌድሬሽኑን ክለቡ በጠየቀው ይግባኝ መሰረት ቅጣቱን ቀንሶለታል በሚል በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካተው በ4-3-3 አደራደር ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ መሪነት ከተያዘለት ሰአት አስር ደቂቃ ዘግይቶ በጀመረው ጨዋታ ገና የዳኛው ፊሽካ ከተሰማበት ሰዓት አንስቶ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል በመድረሱ ረገድ የጦና ንቦች የተሻሉ ሲሆኑ ደደቢቶች የጨዋታውን እንቅስቃሴ ለመረዳት እስከ 15ኛው ደቂቃ ድረስ ጥንቃቄን መርጠው ሲጫወቱ ታይተዋል፡፡ በፈጠሩት ጫና በ3ኛው ደቂቃ ላይ ወላይታ ድቻዎች ያገኙት የማዕዘን ምት ተከላካዩ እሸቱ መና ሲያሻማ ከመሀል ሾልኮ በመውጣት አምረላህ ደልታታ በግንባሩ ገጭቶ ግብ በማስቆጠር በስታዲየሙ የታደሙ ደጋፊዎችን በሙሉ በአንድ ድምፅ ጮቤ አስረግጧል፡፡ 


ድቻዎች በመስመር በኩል ለማጥቃት ያሰቡ በሚመስል መልኩ ፀጋዬ ባልቻ በመስመር ላይ እና እያጠበበ ወደ ሳጥን በመግባት ለቡድን አጋሮቹ በሚፈጥራቸው እድሎች ጫና መፍጠር ችለዋል። በዚህም 12ኛው ደቂቃ ላይ ጃኮ አራፋት በግራ የደደቢት የግብ ክልል ካሻገራትን ኳስ ፀጋዬ ባልቻ በግንባሩ ቢሞክርም አማራ ክሊመንት ይዞበታል።  24ኛው ደቂቃ ላይ መሀል ሜዳ ላይ በጨዋታው ኮከብ ሆኖ የዋለው በዛብህ መለዮ የሰጠውን ኳስ አምረላህ ደልታታ ከግብ ጠባቂው ክሌመንት ጋር ተገናኝቶ አስቆጠረ ሲባል ክሌመንት በሚገርም ሁኔታ አውጥቶበታል፡፡
 የመጀመሪያ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሰላሳ ደቂቃ ያህል መጠበቅ ግድ ካላቸው ደደቢቶች በኩል በተደረገ ሙከራ ፋሲካ አስፋው በረጅሙ የላካትን ኳስ ጌታነህ ከበደ በግንባሩ ገጭቶ ወንድወሰን ገረመው በቀላሉ ይዞበታል። አብዛኛውን የጨዋታ እንቅስቃሴ ወላይታ ድቻች በመስመር ያጋደለ አጨዋወትን በመተግበር እና አልፎ አልፎ በበዛብህ መለዮ ድንቅ ብቃት ታግዘው በመሀል ሜዳ ላይ በተሻለ መልኩ ሲንቀሳቀሱ ደደቢቶች ደግሞ በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች እና በሁለቱ መስመሮች በኤፍሬም አሻሞ እና ሽመክት ጉግሳ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡ አሁንም የተጨማሪ ግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉት የጦና ንቦቹ በ35ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ ከአምረላህ ደልታታ ጋር ባደረጉት የአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ ክልል ገብተው ለጃኮ አራፋት ሰጥተውት ጃኮ ወደ ግብ ቢሞክርም ኢላማዋን ሳይጠብቅ ቀርቷል። 

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃዎች ሲቀሩ ደደቢቶች ያገኙትን ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ አክርሮ መቶት ወንደሰን ገረመው በእግሩ አወጣለው ሲል ኳሷ ባለመራቋ ሽመክት ጉግሳ አግኝቷት ግብ ቢያስቆጥርሞ ከጨዋታ ውጭ ተብላ በረዳት ዳኛው ተሽራለች፡፡ ግቧ በመሻሯ ምክንያት የደደቢት ተጫዋቾች ከፍተኛ ተቃውሞን በረዳት ዳኛው ላይ አሰምተዋል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 1-0 መሪነት ወደ እረፍት አምርቷል፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ድቻዎች ከማጥቃቱ ይልቅ ያስቆጠሩት ግብ አስጠብቆ ለመውጣት በአመዛኙ የኃላ ክልላቸውን ሸፍነው የተጫወቱበት ደደቢቶች ደግሞ የአቻነት ግብ ፍለጋ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አስቆጥሮ አቻ ለመሆን ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉበት ነበር። ገና ጨወታው እንደተጀመረ ጃኮ አራፋት እና በዛብህ መለዮ በፈጠሩት የአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ደደቢት የግብ ክልል በመግባት የሞከሩት ኳስ በተከላካዮች ተጨርፎ ወደ ውጭ ወጥቶባቸዋል፡፡ የወላይታ ድቻን የተከላካይ መስመር ሰብሮ ለመግባት ቢቸገሩም የግብ እድሎችን በመፍጠሩ በኩል ደደቢቶች ተሽለው ታይዋል። በየአብስራ ተስፋዬ ሽመክት ጉግሳ እና ኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት ተደጋጋሚ የማጥቃት እድልን ቢፈጥሩም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ግን አልቻሉም፡፡ በተለይ 57ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረገው ጌታነህ ከበደ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ የመታውን ቅጣት ምት ወንድወሰን ገረመው ሲያወጣበት ብርሀኑ ቦጋለ አግኝቶ ለሽመክት ጉግሳ ሰቶት ሸመክት ወደ ግብ ሞክሮ በግቡ የውስጥ ብረት ተመልሶበታል። 

መልሶ ማጥቃትን አማራጭ አድርገው ከ60ኛው ደቂቃ በኃላ መንቀሳቀስ በቻሉት ወላይታ ድቻዎች በኩል 61ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ በደደቢት ተከላካዮች መሀል ለመሀል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ጃኮ አራፋት ወደ ሳጥን እየገፋ ገብቶ ያደረገው ሙከራ ወደ ላይ ተነስቶበታል፡፡ የደደቢቱ ተከላካይ ጋናዊው አንዶህ ኩዌኩ በተደጋጋሚ ከዳኛ እና ከተጨዋቾች ጋር በሚፈጥረው አስጣ ገባ ምክንያት አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ ቀይረው አስወጥተውታል፡፡ አጥቂው ጌታነህ ከበደም በቡድን ጎደኞቹ ላይ የሚያሳየው ብስጭት እና በአሰልጣኞቹ ላይ የሚያሳየው ስሜታዊ ንግግር በጉልህ የታየ ነበር። በወላይታ ዲቻ በኩልም ግብ ጠባቂው ወንደሰን ገረመው በዳኛው ላይ ያልተገባ ባህሪ ሲያሳይ እና በጨዋታውም ትኩረት የማጣት ችግር ሲታይበት ተመልክተናል። ጨዋታው ግን ከአመረላ ድልታታ ግብ ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በወላይታ ድቻ አሸናፊነት ተገባዷል።

የአሰልጣኞች አሰተያየት

አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ – ወላይታ ድቻ

ጨዋታው ከሞላ ጎደል ጥሩ ነበር። ትኩረት የሚጠይቅ ጨዋታ ነበር። ጭንቀትም ነበረው። ደደቢት ትልቅ ቡድን በመሆኑ ጫናው ከባድ ነበር። እኛም ጥሩ ነበርን። በቀጣይ መሻሻል ያለበት ነገር እንዳለ ተመልክቻለው። ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ አይደለንም። በቀጣይ በስነልቦና ረገድ ማሸነፍ  ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ወደ ላይ በደረጃው መጠጋታችን እና ከታችኛው ደረጃ በሚገባ መውጣት መቻላችን በቀጣይ ከመከላከያ ላለብን ጨዋታ ትልቅ ስንቅ ነው። በዚሁ ከቀጠልን ለሻምፒዮንነት መፎካከራችንም አይቀርም፡፡

ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ – ደደቢት

ጨዋታው ጥሩ ነበር። በመጀመሪያ ደቂቃ የተቆጠረብን ግብ  እንዳሰብነው መሆን አላስቻለንም። በዘጠና ደቂቃም ኳስን ተቆጣጥረን ለመጫወት ችለናል። ኳስ ጨዋታ ላይ ያለ ነው። ተጫውተን ተሸንፈናል። በቀጣይ የተሻለ ሆኖ መቅረብ አለብን። የዛሬው ሽንፈት ለኛ የማንቅያ ደወል ነው። በቀጣይ የተሻለ ሰርቶ መቅረብ ነው። አሁንም ከሻምፒዮንነቱ አልራቅንም። አሁንም መሪ ነን። ጌታነህ ከሜዳ ርቆ ነበር አሁን ግን ተመልሷል በቀጣይም ያለብንን ክፍተት ይደፍልናል ብዬ አስባለው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *