የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እና የ14ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሀ ግብር በዛሬው እለት በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተካሂደዋል። ሽረ እንዳስላሴ በድል የመጀመርያ ዙሩን ሲያገባድድ አዲስ አበባ ከተማ እና ቡራዩ ከተማም ከመሪው ያላቸውን ልዩነት ያጠበቡበት ድል አስመዝግበዋል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሽረ እንዳስላሴ በሜዳው ፌዴራል ፖሊስን አስተናግዶ 5-2 በማሸነፍ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ባህርዳር ከተማ ጋር የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ማጥበብ ችሏል። በጊዜ ግብ ማስተናገድ በጀመረው ጨዋታ 5ኛው ደቂቃ ላይ ሊቁ አልታየ ፌደራል ፖሊስን መሪ ቢያደርግም በ11ኛው ደቂቃ ላይ በድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው ሰዒድ ሁሴን ሽረን አቻ አድርጓል። በ24ኛው ደቂቃ ልደቱ ለማ ባለሜዳዎቹን ወደ መሪነት ሲያሸጋግር በ38ኛው ደቂቃ ጌድዮን መላኩ ሶስተኛውን አክሎ የመጀመርያው አጋማሽ በሽረ 3-1 መሪነት ተጠናቋል። ከእረፍት መልስ ተጠናክረው የገቡት ሽረዎች በ54ኛው ደቂቃ የሙሉጌታ አንዶም ጎል ልዩነታቸውን ሲያሰፉ ባህሩ ለፌዴራል ፖሊስ ሁለተኛ ግብ ቢያስቆጥርም በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ጌድዮን መላኩ ለራሱ ሀለተኛውን ለቡድኑ የማሳረጊያውን ኳስ ከመረብ አዋህዷል።
ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ሁለተኛ ተከታታይ የሜዳ ውጪ ድል በማስመዝገብ ወደ ጥንካሬው ተመልሷለል። ነቀምት ከተማን የገጠመው አአ ከተማ 3-1 ሲያሸንፍ የጎል መንገዱ የሰመረለት ፍቃዱ አለሙ ፣ አምበሉ ሙሀጅር መኪ እና ተከላካዩ ሚልዮን ብሬ የመዲናዋ ክለብ ጎሎችን አስቆጥረዋል። ድሉ አአ ከተማን ከመሪው በ2 ነጥቦች አንሶ 3ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ የረዳው ሲሆን በ15ኛ ሳምንት ባህርዳር ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ከወዲሁ እንዲጠበቅ አድርጎታል።
ቡራዩ ላይ ወሎ ኮምቦልቻን የገጠመው ቡራዩ ከተማ በቀላሉ 3-0 አሸንፎ መሪዎቹን በቅርብ ርቀት መከተሉን ቀጥሏል። በ5ኛው ደቂቃ አምበሉ አቡበከር በሁለት ተጫዋችች መሀል አሳልፎ ያቀበለውን ኳስ ኢሳይያስ ታደሰ ወደ ግብነት ለውጦ ቡራዩን ቀዳሚ ሲያደርግ በ14ኛው ደቂቃ አቡበከር ከሳጥን ውጭ የመታው ኳስ በወሎ ኮምቦልቻ ተካላካይ ተደርቦ ሲመለስ ደበላ ሮባ አግኝቶት በአጎባቡ በመጠቀም ቡራዩ 2-0 እነዲመራ አስችሏል። በ53ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኢሳይያስ ታደሰ ከቅጣት ምት ለግሉ ሁለተኛውን ለቡድኑ ሶስተኛውን ጎል ማስቆጠር ችሏል። ቡራዩ ይበልጥ ወደ መሪነት ለመጠጋት የሚረዳው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከለገጣፎ ጋር ይቀረዋል።
በተከታታይ ሽንፈቶች የተንሸራተተው ሰበታ ከተማ በሜዳው ሱሉልታ ከተማን ገጥሞ በጌዲዮን ታደሰ ጎል 1-0 ማሸነፍ ችሏል። በሱሉልታው ያያ ቪሌጅ የሜዳውን ጨዋታ እያደረገ የሚገኘው ኢኮስኮ የካ ክፍለ ከተማን ጋብዞ በተመሳሳይ 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ 7ኛ ከፍ አድርጓል። የኢኮስኮን ብቸኛ የድል ጎል በ81ኛ ደቁቃ ያስቆጠረው የኋላሸት ሰለሞን ነው።
ትላንት በመድን ሜዳ በተደረገ የምድብ ሀ አንድ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ከ አማራ ውሃ ስራ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።