የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ደጋፊ ካላቸው ክለቦች መሀከል አንዱ ነው። ክለቡ ከተመሰረተበት 2001 ጀምሮ በሶዶ እና ቦዲቲ ከተማ ባሉት ስታድየሞች የሊግ ጨዋታዎቹን ሲያከናውን ቆይቷል። አሁን ላይ ክለቡ የሶዶ ስታድየምን በቋሚነት እየተገለገለበት ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣው የደጋፊው ቁጥር ከስታድየሙ የመያዝ አቅም ጋር የተመጣጠነ ባለመሆኑ ተመልካቹ ከስታድየሙ ቅጥር ግቢ ውጪ በዛፎች እና ከፍታ ቦታዎች ላይ ሆኖ ጨዋታዎችን ሲከታተል ይታያል። ክለቡ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባትም ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ማቀዱ ተሰምቷል።
ክለቡ ከአንድ የቻይና ድርጅት ጋር ጥናት አድርጎ ከመፈራረሙ ባሻገር በፋይናንስ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እየተነጋገረ እንደሆነ እና ከክልሉ መንግስት ጋር መጨረስ ያለባቸውን ጉዳዮች ቋጭተው ወደስራ በሚገባበት ሰአት የስራው ሙሉ ሂደት ለህዝቡ ይፋ እንደሚደረግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ክለቡ ስታድየሙ ምን ያህል ተመልካች እንደሚይዝ ይፋ ባያደርግም ከ40 እስከ 50 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ተነግሯል። በርካታ ደጋፊዎች ያሉት ወላይታ ድቻ መቼ ግንባታውን እንደሚጀመር ያልተነገረለት ስታዲየም የክለቡን ታሪክ ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚያሻግር እንደሚሆን ይጠበቃል።