በዘንድሮ የውድድር አመት ከተስፋ ቡድን ባደጉ ተጫዋቾቹ ውጤታማ ጉዞ እያደረገ የሚገኘው አዳማ ከተማ የወርሀዊ ደሞዝ መጠናቸው ላይ ማሻሻያ አድርጓል። በዚህም መሰረት ከተስፋ ቡድኑ አድገው የሶሰት አመት ኮንትራታቸውን ያላገባደዱት ቡልቻ ሹራ ፣ በረከት ደስታ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ሱሌይማን ሰሚድ አሁን ከሚያገኙት ወርሃዊ ደሞዝ በእጥፍ ማሳደጉ ታውቋል። ከአራቱ በተጨማሪም ዘንድሮ ክለቡን ተቀላቅሎ ጥሩ ግልጋሎት እየሰጠ የሚገኘው አይቮሪኮስታዊው ኢስማኤል ሳንጋሪም የደሞዝ ማሻሻያው አካል ሆኗል።
ክለቡ ለተጫዋቾቹ ማሻሻያ ለማድረግ ያነሳሳው በዝቅተኛ ደሞዝ ክለቡን እያገለገሉ የሚገኙት ተጨዋቾቹን ተነሳሽነት ለማሳደግ እና እየሰጡት ያለውን አገልግሎት ከግምት በማስገባት እንዲሁም በቀጣይም ለክለቡ የተሻለ አገልግሎት ይሰጣሉ ብሎ በማመን እንደሆነ ገልጿል። በተጨማሪም ክለቡ ይህ የደሞዝ ማሻሻያ በቂ ነው ብሎ እንደማያምን እና በቀጣይም እንደ አስፈላጊነቱ የደሞዝ ጭማሪው ሊቀጥል እንደሚችል የክለቡ ኃላፊዎች ለሶከር ኢትዮዽያ ተናግረዋል ።
ክለቡ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ተጫዋቾችን ከማስፈርም ይልቅ ዘንድሮ በወጣት ተጫዋቾቹ እያገኘ ያለው የተሻለ አገልግሎት ብዙ ትምህርት እንደሰጠው እና በቀጣይም በወጣቶች ላይ ያለውን እምነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቋል።
አዳማ ከተማ በሊጉ 26 ነጥብ በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ ከደደቢት በሶስት ነጥብ ፣ ከመቐለ ከተማ በሁለት ነጥብ አንሶ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።