ብሄራዊ ሊግ ፡ አዲስ አበባ ከነማ ጅማ አባ ቡናን ተከትሎ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ምድብ 2 ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ አስቀድሞ ወደ ሩብ ፍፃሜው የተቀላቀለው ጅማ አባ ቡናን ተከትሎ የሚያልፈው ቡድንም ተለይቷል፡፡ ጅማ አባ ቡና የሚጫወትበትን ሜዳ በመሳሳቱና ወደ ሜዳው ተመልሶ ጨዋታው እስኪጀመር ድረስ ሁሉም ጨዋታዎች መጀመር ከነበረባቸው ሰአት 25 ደቂ ዘግይተው መጀመራቸውም በርካቶችን ፈገግ አሰኝቷል፡፡

በመከላከያ ሜዳ በ7 ነጥብ የተሻለ የማለፍ ተስፋ ይዞ የገባው አዲስ አበባ ከነማ የምድቡ መሪ ጅማ አባ ቡናን 2-1 በማሸነፍ እድሉን በሚገባ ተጠቅሞበታል፡፡ ለአዲስ አበባ ከነማ የድል ግቦቹን ሙሃጅብ መኪ እና ክብረት አየለ ሲያስቆጥሩ የጅማ አባ ቡናን ግብ ሚልዮን መንገሻ አስቆጥሯል፡፡ በጨዋታው አስቀድሞ ወደ ሩብ ፍፃሜ ማለፉን ያረጋገጠው ጅማ አባ ቡና አመዛኞቹን ቋሚ ተሰላፊዎቹን ለሩብ ፍፃሜ ጨዋታው አሳርፎ በተጠባባቂ ተጫዋቾች ተጫውቷል፡፡

በጨዋታው የጅማ አባ ቡና ተጫዋች በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድከሜዳ በመሰናበቱ በዳኞቹ እና የጅማ አባ ቡና አሰልጣኝ ደረጄ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ለጥቂት ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዶ ነበር፡፡

ከጨዋታው በኋላ የአዲስ አበባ ከነማው አሰልጣኝ ታደሰ በሰጡት አስተያየት በየጨዋታው ድክመቶቻቸውን እያሩ በመምጣታቸው ለሩብ ፍፃሜ እንደበቁ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ በመጀመርያው ጨዋታ ስለ ባቱ ምንም መረጃ የሌለን በመሆኑ በሰፊ ግብ ተሸንፈናል፡፡ ከዛ በኋላ ባሉት ጨዋታዎች ግን ድክመቶቻችንን እያረምን ነጥቦች መሰብሰብ ችለናል፡፡ ›› ብለዋል፡፡ አሰልጣኙ ስለ ቀጣይ ተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ ከነማም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ ድሬዳዋ ከነማን ተመልክቸዋለው፡፡ ጠንካራ ተጋጣሚ ነው፡፡ ከደጋፊያቸው የሚመጣውን ጫና ተቋቁመን ለማሸነፍ ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡

በግብ ልዩነት የደረጃው አናት ላይ ተቀምጠው ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፉት የጅማ አባ ቡናው አሰልጣኝ ደረጄ በላይ በበኩላቸው ከጨዋታው ይልቅ በእለቱ ዳኞች ላይ ማውራትን መርጠዋል፡፡ ‹‹ ስለ ጨዋታው ብዙም የምለው ነገር የለኝም፡፡ ነገር ግን በዳኛው ውሳኔ ደስተኛ አልነበርንም፡፡ ተጫዋቻችን አጥቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ዳኛው የጨዋታውን ግለት ተመልክቶ ሊያልፈው ይችል ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ ቀጣይ ተጋጣሚያቸውፌዴራል ፖሊስን በጠንካራ አቋም እንደሚገጥሙም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ቀጣይ ተጋጣሚያችን ጠንካራ ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ በርካታ ቋሚ ተሰላፊዎቻችንን አላስገባንም፡፡ ከዛሬው ድባብ ወጥተን ፌዴራል ፖሊስን ለመግጠም እንዘጋጃለን፡፡ ወደ ፊት መጓዛችንን በመቀጠልም የወከልነውን ህዝብ እናኮራለን›› ብለዋል፡፡

Jimma Ababuna

በድሬዳዋ ስታድየም ባቱ ከነማ ሱሉልታ ከነማን 4-3 ቢያሸንፍም ከምድቡ ከመሰናበት አልዳነም፡፡

7 ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ ሱሉልታዎች ከአቅም በታች እየተጫወቱ ነው በሚል የጨዋታው ኮሚሽነሮች በጨዋታው መሃል ለቡድኖቹ ማስጠንቀቅያ መስጠታቸውም ተነግሯል፡፡ ሱሉልታዎች 2-0 እየመሩ አቻ መሆናቸው ፣ ኋላ ላይ በድጋሚ መርተው በድጋሚ ግብ ማስተናገዳቸው ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡

ከድሉ በኋላ ባቱ በ9 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ይዞ ሲያጠናቅቅ ሱሉልታ ከነማ የምድቡ ግርጌ ላይ ሆኖ ውድድሩን ተሰናብቷል፡፡

በሳቢያን ሜዳ ናሽናል ሴሜንት ሻሸመኔ ከነማን 2-0 በማሸነፍ በድል ውድድሩን ተሰናብቷል፡፡ የስምኦን አባይ ቡድን 7 ነጥቦች ይዞ ምድቡን በ4ኝነት ሲያጠናቅቅ ሻሸመኔ ከነማ በ4 ነጥቦች 5ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡

በሩብ ፍፃሜው ድሬዳዋ ከነማ ከ አዲስ አበባ ከነማ እንዲሁም ጅማ አባ ቡና ከ ፌዴራል ፖሊስ ጨዋቸውን ያደርጋሉ፡፡

 

———

ፎቶ – ከምድብ 2 ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀሉት አዲስ አበባ ከነማ (ከላይ) እና ጅማ አባ ቡና (ከታች)

——

የየምድቦቹን የደረጃ ሰንጠረዥ ፣ ውጤቶች ፣ ቀጣይ ጨዋታዎች እና ከፍተኛ ግብ አግቢዎች ደረጃ ለማወቅ ሜኑ ላይ Competitions ላይ ከሚመጡት አማራጮች Ethiopian National League ቀጥሎም Tables ይጫኑ

ያጋሩ