ቅድመ ዳሰሳ | 17ኛ ሳምንት የመጋቢት 20 ጨዋታዎች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ነገ ወልዲያ ፣ ጅማ ፣ አርባምንጭ ፣ ዓዲግራት እና አዲስ አበባ ላይ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። እኛም በቅድመ ዳሰሳ በሚከተለው መልኩ ተመልከተናቸዋል።

ወልዲያ ከ ሀዋሳ ከተማ

የመሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታድየሙ ጨዋታ ሁለት በተለያየ መንገድ ላይ የሚገኙ ክለቦችን ያገናኛል። ወልዲያ ቅጣት በጣለባቸው ተጨዋቾቹ ጉዳይ እና በምትካቸው ሌሎች ተጨዋቾችን ያለመተካቱን ተከትሎ ከሜዳው ውጪ ያለመረጋጋት ይታይበታል። ሜዳ ላይም ወደ ሶዶ እና አዳማ ያደረጋቸውን ጉዞዎች በሽንፈት ደምድሞ ነው ለነገው ጨዋታ የሚቀርበው። ወጣ ገባ የነበረው የውድድር ዘመኑን ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ባሳካቸው ሰባት ነጥቦች እያስተካከለ የመጣው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ በመጀመሪያው ዙር የነበረውን መጥፎ የሜዳ ውጪ ሪከርድ ለመቀየር ወደ ወልዲያ አቅንቷል። ሀዋሳ በወልዲያ ላይ በሁለተኛው ሳምንት ያስመዘገበው የ4-1 ድል እና ሰሞንኛው መልካም አቋሙ ለዚህ ጨዋታ ዝግጅት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግለት ይታሰባል። 

ወልዲያ ሰለሞን ገብረመድህን እና አዳሙ መሀመድን አሁንም በጉዳት የሚያጣ ሲሆን ብሩክ ቃልቦሬ ከቅጣት መልስ ተሰላፊ እንደሚሆን ይጠበቃል። አዲስአለም ተስፋዬን ከቅጣት መልስ የሚያገኘው ሀዋሳ ከተማ የመሀል ተከላካዩ ሲላ መሀመድን በ5 ቢጫ ካርድ ምክንያት ሲያጣ አዲስ ፈራሚው አብዱልከሪም ሀሰን እና ከተስፋ ቡድን በቅርቡ ያደገው ቸርነት አውሽ የወረቀት ጉዳያቸው ባለማለቁ ምክንያት እንደማይደርሱ ተሰምቷል። መሳይ ጳውሎስ ፣ ዮሀንስ ሱጌቦ እና ፀጋአብ ዮሴፍ ደግሞ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን መመረጣቸውን ተከትሎ ለክለባቸው አገልግሎት የማይሰጡ ተጨዋቾች ናቸው።

የተጨዋቾች እጥረት ያለበት ወልዲያ የአዳማውን ጨዋታ በአምስት ተጠባባቂዎች ብቻ አድርጎ ምንም ቅያሪ ሳያደርግ ነበር ያጠናቀቀው። ይህ ሁኔታ ሳይቀረፍ  በነገው ጨዋታም የሚቀጥል ከሆነ በቡድኑ ላይ የሚፈጥረው ችግር ቀላል አይሆንም። ችግሩ በሜዳ ላይ የሚኖረው ቡድን አማራጭ ስትራቴጂዎችን ተጠቅሞ የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥርም ዕክል እንደሚፈጥር ዕሙን ነው። በነገው ጨዋታ ወልዲያ በዋነኝነት ፊት ላይ በሚኖረው የአንዷለም ንጉሴ እንቅስቃሴ ላይ መሰረት ያደረገ አቀራረብን ይዞ እንደሚገባ ይጠበቃል። አዲስ ፈራሚዎቹ መስፍን ኪዳኔ እና አሳልፈው መኮንንም በሁለቱ መስመሮች የሚኖራቸው ሀላፊነት የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን እንደሚወስድ የሚጠበቀው የተጋጣሚያቸው የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴን ለመግታት ከአንዷለም ይልቅ ለመስመር ተከላካዮቹ በሚቀርብ አማካይ ቦታ አያያዝ ላይ የሚተገበር ይሆናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ቡድኑ ኳሶችን በሚነጥቅባቸው አጋጣሚዎች ከሀዋሳ የተከላካይ መስመር ጀርባ በሚኖረው ቦታ ላይ ለመግባት የሚያስችሉ ዕድሎችን ለብቸኛው አጥቂ የመፍጠር ሀላፊነት ይኖርበታል። 

የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን ከውጤቱ መስተካከል ባለፈ በአጨዋወቱም እየተሻሻለ መጥቷል። ጨዋታው የሚደረግበት ሜዳም ከቡድኑ ባህሪ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑ ተጠቃሚ ያደርገዋል። አምናም ምንም እንኳን ማሸነፍ ባይችሉም በወልዲያ አዲስ ሜዳ ላይ የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር የቻሉት ሀዋሳዎች ነበሩ። ሀዋሳ የሜዳ ጥራት በሚፈልገው ከኳስ ቁጥጥር ተኮር ጨዋታው ባለፈ የመልሶ ማጥቃት አጋጣምዎችን ካገኘ መጠቀም የሚያስችል አቅም እንዳለው ጅማን በሙሉአለም ረጋሳ ድንቅ ጎል የረታበት ያሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታ አሳይቶን አልፏል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ የመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ተሳትፎ በሚጨምርበት ወቅት የተሻለ ውጤታማነትም ይኖረዋል። በነገው ጨዋታም ሀዋሳ ከተማ በዋነኝነት በመሀል ሜዳ በሚደረጉ ቅብብሎች መነሻነት የመስመር አጥቂዎቹን ተሳትፎ አክሎበት ወደ ወልዲያ የግብ ክልል ለመግባት እንደሚጥር ይጠበቃል። የወልዲያ የመከላከል ሽግግር በፍጥነት የማይታገዝ ከሆነ ደግሞ ከፊት አጥቂው እስራኤል እሸቱ ውጪም ዘግይተው ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን የሚደርሱ የሀዋሳ አማካዮችም አደጋ የሚፈጥሩበት ዕድል ሰፊ ነው። 

እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ እስካሁን በሊጉ 5 ጊዜ ተገናኝተዋል። አንድም ጊዜ አቻ ባልተለያዩበት ታሪካቸው ወልድያ 7 ጎሎችን በማስቆጠር 2 ጊዜ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ 10 ግቦችን በማስቆጠር 3 ጊዜ ባለድል ሆነዋል። 

– ወልዲያ ላይ በተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች ወልዲያ አሸንፏል።

– ወልዲያ አላሙዲን ስታድየም ላይ ባደረጋቸው ያለፉት 9 ተከታታይ ጨዋታዎች አልተሸነፈም።

– ሀዋሳ ከተማ ከሜዳው ውጪ ለመጨረሻ ጊዜ ካሸነፈ ነገ አንድ አመት ይደፍናል። ለመጨረሻ ጊዜ ከሜዳው ውጪ ያሸነፈው መጋቢት 20 ቀን 2009 መከላከያን (3-0) ነበር። ነገ ልክ በአንደኛ አመቱ መጥፎ ሪከርዱን ይፍቅ ይሆን?

ዳኛ

በመጀመሪያው ዙር አርባምንጭ ከተማ ከደደቢት እንዲሁም ድሬደዋ ከተማ ከወልዋሎ ዓ.ዩ ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች መዳኘት የቻለው ፌደራል ዳኛ አክሊሉ ድጋፌ ለዚህ ጨዋታ ተመድቧል። አልቢትሩ በሁለቱ ጨዋታዎች ሰባት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን አሳይቷል። 


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ጅማ አባ ጅፋር ከ ድሬደዋ ከተማ

ሁለተኛውን ዙር ሀዋሳ ላይ በደረሰበት የ1-0 ሽንፈት የጀመረው ጅማ አባ ጅፋር በሜዳው ካለው ጥንካሬ አንፃር ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ አሳክቶ በጥቂቱ የተንሻራተተበትን ደረጃውን ለማሻሻል  ያልማል። እዚህ ላይ ቡድኑ በሜዳው ያለው ብርታት ለመጨረሻ ጊዜ ጅማ ላይ ላስተናግደው ጥሩ አቋም ላይ ለሚገኘው ወላይታ ድቻም ያልተመለሰ መሆኑን ማስታወስ ይገባል። ወልዋሎ ዓ.ዩን ካሸነፈበት ጨዋታ በኃላ ዳግም ወደ ነበረበት ፈዛዛ የውድድር አመት እየተመለሰ እንዳይሆን የሚያሰጋው ድሬደዋ ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ አሳክቶ ወደ ጅማ አምርቷል። ድሬድዋ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንደ አዲስ አበባው ጨዋታ ሁሉ ሜዳው ላይም ነጥብ ማስጣሉ ግን እንደ አንድ ጥሩ ጎን የሚነሳለት ነው። 

ከጅማ አባ ጅፋር በጉዳት ይህ ጨዋታ የሚያመልጠው እንዳለ ደባልቄ ብቻ ሲሆን በድሬደዋ ከተማ በኩል በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ላይ መጠነኛ ጉዳት ገጥሞት የነበረው ዘነበ ከበደ እና በዛ ጨዋታ ላይ ያልተሰለፈው ኢማኑኤል ላሪያ  ወደ ጅማ የተጓዙ ሲሆን ሳምሶን አሰፋ ግን አሁንም ጉዳት ላይ ይገኛል። 

በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በሙሉ ሀይላቸው ሲያጠቁ የሚታዩት አባ ጅፋሮች ከሽንፈት መልስ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን ተጭነው መጫወታቸው የሚቀር አይመስልም። ፊት ላይ ተመስገን ገብረኪዳን እና ኦኪኪ አፎላቢ ከድሬደዋ የተከላካይ መስመር ጋር ከሚያደርጉት ፍሊሚያ በተጨማሪ ዮናስ ገረመው እና አሮን አሞሀ በማጥቃት ወቅት የሚኖራቸው ፍጥነት እና የኳስ ቅብብል ስኬትም ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ በኄኖክ አዱኛ አማካይነት በቀኝ መስመር በኩል የሚከፍተው ተደጋጋሚ ጥቃት አህመድ ረሺድ ከሚሰለፍበት የድሬደዋ የግራ መስመር የመከላከል ክፍል ጋር የሚገናኝባቸው አጋጣሚዎች ተጠባቂዎች ናቸው። 

ድሬደዋ ከተማ ለማጥቃት ቦታ እየሰጠ በመጣው አጨዋወቱ አሁን ደግሞ ሶስት የፊት መስመር ተጨዋቾችን መጠቀም ጀምሯል። ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ ወደ ሜዳ የተመለሰውን ሀብታሙ ወልዴን እና አዲስ ፈራሚው በረከት ይስሀቅን ከአትራም ኩዋሜ ጋር ያጣመረው ቡድን በዚህ ጨዋታ ላይ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹ ብቃት በእጅጉ ያስፈልገዋል። በተለይም ዘላለም ኢሳያስ እና ዮሴፍ ዳሙዬ መሀል ሜዳ ላይ የሚኖራቸው ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተከላካይ አማካያቸውን ከጥቃት በመከላከሉ በኩልም ሆነ ፊት ላይ ላለው የሶስትዮሽ ጥምረት ኳሶችን ለማድረስ እስፈላጊ ያደርገዋል። ይህን ሀላፊነት ለመወጣት ደግሞ ተጨዋቾቹ ከአባ ጅፍፋሮቹ ይሁን እንዳሻው እና አሚኑ ነስሩ ጋር የሚገናኙባቸው የሜዳ ክፍሎች ላይ ተሽለው መገኘት ይጠበቅባቸዋል። 

ዳኛ

ጨዋታው በዚህ አመት በርከት ያሉ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን እየዳኛ ለሚገኘው ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታው ይሆናል። በአምላክ በመጀመሪያው ዙር ሶስት ጨዋታዎችን ዳኝቶ ስድስት ቢጫ ካርዶችን አሳይቷል። 


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


አርባምንጭ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

ወንድሜህ ዘሪሁን አርባምንጭን ከተሰናበተ በኃላ ሲዳማን በተቀላቀለበት ሳምንት ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ መገናኘታቸው ትኩረትን ስቧል። በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የተቀመጠው አርባምንጭ ከተማ የመጀመሪያውን ዙር በፋሲል ከተማ ተረቶ የደመደመ ሲሆን ሁለተኛውን ዙርም መቐለ ላይ በደረሰበት ሰፊ ሽንፈት ጀምሮታል። ቡድኑ በሁለቱ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ሳይችል እጅ ከመስጠቱ በፊት አሳይቶት የነበረውን መነቃቃት መልሶ ለማግኘት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ወዳሸነፈበት ሜዳው መመለሱ ተጠቃሚ ያደርገዋል። እንደተጋጣሚው ሁሉ ሁለተኛውን የውድድር አጋማሽ በሽንፈት የጀመረው ሲዳማ ቡና ከ12ኛው ሳምንት በኃላ ዳግም ወደ ድል መመለስ የከበደው ይመስላል። በዚህ ጨዋታም ከሜዳው ውጪ የአመቱን የመጀመሪያ ድል ለማግኘት እና ከወዲሁ የወራጅ ቀጠና ስጋትን ለመሸሽ እንደሚፋለም ይጠበቃል።     

አርባምንጭ ከተማ ወደ መቐለ ሳይጓዙ ቀርተው የነበሩትን ፀጋዬ አበራን ከጉዳት አንድነት አዳነ ከቅጣት መልስ እንደሚጠቀም ይጠበቃል። ሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ በጉዳት እንዲሁም ተከላካዩ አበበ ጥላሁን በ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ  ባዬ ገዛኸኝ ከቅጣት የሚመለስ ይሆናል።  ከዚህ ውጪ የአርባምንጮቹ  እስራኤል ሻጎሌን እና ፂሆን መርዕድ እንዲሁም  የሲዳማ ቡናዎቹ  ዮናታን ፍሰሀ ፣ ሚካኤል ሀሲሳ እና ሙጃይድ መሀመድ ለ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን መመረጣቸውን ተከትሎ ቡድኖቻቸውን የማይገለገሉ ይሆናል።    

አርባምንጭ ከተማ በቡድን መዋቅሩ ውስጥ በርካታ ሊያሻሽላቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን የመቐለው ጨዋታ አሳይቶን አልፏል። በተለይ ቡድኑ ከተጋጣሚው ፈጣን ጥቃት ሲሰነዘርበት የኃላ መስመር ተሰላፊዎቹ የሚኖራቸውን የቦታ አያያዝ በሚገባ ማጤን ይጠበቅበታል። በነገው ጨዋታ ይህ ደካማ ጎኑ በሲዳማ ቡና በቀላሉ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል በመሆኑም የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች በማጥቃት ላይ የሚደረግ ተሳትፎ የሲዳማን የመስመር ተከላካዮችን ፍጥነት ከግምት ያስገባ እንዲሆን ይጠበቃል። ጨዋታው ለአርባምንጭ የተሻለ የመሀል ሜዳ ነፃነት ሊሰጥ የሚችል በመሆኑ አማካይ ክፍል ላይ ያለው የምንተስኖት አበራ እና አማኑኤል ጎበና ጥምረት በኳስ ቁጥጥር ሂደት ውስጥ ከሌላኛው አማካይ አለለኝ አዘነ ጋር የተሻለ መናበብን በማሳየት ለፊት አጥቂዎቹ የጠሩ እና የበዙ ዕድሎችን መፍጠር ይጠበቅበታል። 

ፈጣን የመስመር አጥቂዎችን ለያዘ እንደ ሲዳማ ቡና አይነት ላለ ቡድን የነገው ጨዋታ ግብ ለማግኘት የተመቸ ይመስላል። ቡድኑ አዲስ ግደይ እና አብዱለጢፍ መሀመድን በመጠቀም ሰፊ ክፍተት ሲፈጥሩ በሚታዩት የአርባምንጭ የመስመር እና የመሀል ተከላካዮች መሀል በመግባት ሳጥን ውስጥ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የሚችልበት አማራጭ በነገው ጨዋታ ይጠበቃል። ይህን ለማድረግ ደግሞ እንደ ትርታዬ ደመቀ እና ፍፁም ተፈሪ ያሉ አማካዮች በቁጥር ተበራክቶ ከሚገጥማቸው የአርባምንጭ የአማካይ ክፍል የሚነጥቋቸውን ኳሶች ተጋጣሚያቸው የመከላከል ቅርፁን ከመያዙ በፊት ለመስመር አጥቂዎቻቸው ቀጥተኛ ሩጫ በተመቸ አኳኃን ማሳለፍ ግድ የሚላቸው ይሆናል። 

እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ከለቦቹ በሊጉ ታሪካቸው 13 ጊዜ ሲገናኙ ሁለት ሁለት ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል። ቀሪዎቹ 9 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተደመደሙ ነበሩ። ግብ በማስቆጠሩም በኩል ተቀራራቢ ሲሆኑ አርባምንጭ 8 እንዲሁም ሲዳማ 7 ጊዜ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችለዋል።

– አርባምንጭ ላይ ከተደረጉ 6ቱ ጨዋታዎችም ግማሹ የአቻ ውጤት የተመዘገበባቸው ሲሆን በሜዳው ሁለቴ ድል የቀናው አርባምንጭ ስድስት ግቤችን አንዴ ያሸነፈው ሲዳማ ደግሞ ሶስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ዳኛ

የአመቱን ስምንተኛ ጨዋታውን የሚዳኛው ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ይህንን ጨዋታ የሚመራው ይሆናል። አልቢትሩ እስካሁን በሰባት ጨዋታዎች 28 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን እና 2 የቀይ ካርዶችን መዟል። 


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ መቐለ ከተማ

በመጀመሪያው ዙር ሁለቱም ቡድኖች ለሊጉ አዲስ ሆነው በተገናኙበት የትግራይ ደርቢ ያለግብ ቢለያዩም አሁን ላይ  በደረጃ ሰንጠረዡ በመሀላቸው አስር ቡድኖች ይገኛሉ። ወልዋሎ ዓ.ዩ ለመጨረሻ ጊዜ ሜዳው ላይ ባደረገው ጨዋታ ሀዋሳን ሲረታ በጥሩ ሁኔታ አመቱን ወደጀመረበት መንፈስ ይመለሳል ተብሎ ቢጠበቅም ከዛ በመቀጠል ግብ ባላስቆጠረባቸው ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ገጥሞት በወራጅ ቀጣናው አፋፍ ላይ እንዲገኝ ሆኗል። ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ መሰብሰብም ቡድኑ ራሱን ካሁን ከአደጋ ክልል እንዲያርቅ እድል የሚሰጠው ነው። ሆኖም ተጋጣሚው መቐለ ከተማ በቀላሉ ይህ እንዲሆን የሚፈቅድ አይመስልም። ከሶስት ተከታታይ ድሎች በኃላ በመከላከያ ተሸንፈው የመጀመሪያውን ዙር ያገባደዱት መቐለዎች አርባምንጭ ላይ ባዘነቧቸው አራት ጎሎች ሁለተኛ ደረጃን ተቆናጠው ነው ወልዋሎን የሚገጥሙት። ድሉ ለቡድኑ የሚፈጥርለት መነሳሳትም ለዓዲግራቱ ጨዋታ ተነሳሽነቱን ከፍ እንደሚያደርግለት ይጠበቃል። 

ወልዋሎ  ለ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የተመረጠውን ግብ ጠባቂ በረከት አማረ  ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም ተጨዋቹ በገጠመው የአፍንጫ ህመም ምክንያት ሳይሳካለት ቀርቷል። በመቐለ ከተማ በኩል ደግሞ አሌክስ ተሰማ ፣ ጋቶች ፓኖም እና ሀብታሙ ተከስተ ጉዳት ላይ መሆናቸውን ሰምተናል። 

በዋነኝነት የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በማግኘት ላይ ተመስርቶ የተገንባው የወልዋሎ ቡድን በተጋጣሚዎቹ ተገማች የሆነ ይመስላል። ቡድኑ በጣሙን ተቀራርበው በሚጫወቱ የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎች ሲኖሩት የሜዳውን ስፋት የተሻለ የመጠቀም አዝማሚያ የሚያሳየው ኳስ ወደ መስመር አጥቂዎቹ ጋር ሲደርስ ብቻ ነው። በነገው ጨዋታም በዚሁ ቦታ ላይ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ እና ከድር ሳሊህ ከመቐለ የመስመር ተከላካዮች ጋር ሲገናኙ የሚኖራቸው ውሳኔ አሰጣጥ ቡድኑ ለሚፈጥራቸው የግብ ዕድሎች ዋነኛ መነሻ እንደሚሆን ይታመናል። በወልዋሎ የግብ ሙከራዎች ላይ በሙሉ በዋና ተዋናይነት ሲሳተፍ የሚታየው ታታሪው የመስመር አጥቂ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ወደ ኃላ ወደ መሀል ተመልሶ በሚጫወትባቸው አጋጣሚዎች ለጠባቡ አማካይ ክፍል ተጨማሪ ይቅብብል አማራጬችን ሲያስገኝ ይታያል። ወልዋሎዎች ነገም ተጨዋቹ በመቐለው የቀኝ መስመር አማካይ ያሬድ ከበደ አቅጣጫ በመጠኑ ወደኃላ  እየተሳበ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ የህን ጥቅም ለማግኘት እንደሚያስቡ ይጠበቃል።  በሌላ በኩል የአማካይ ክፍሉ የአፈወርቅ ኃይሉ እና ዋለልኝ ገብሬ ጥምረት መሀል የሚኖረው ርቀት እንደጨዋታው ሂደት የማይመጠን ከሆነ ጠንካራ የሆነው የመቐለ ከተማ የተከላካይ አማካይ ጥምረትን በቀላሉ ለማለፍ እንደሚቸገር መናገር ይቻላል።            

መቐለ ከተማ ለውጤቱ ዋነኛ ተጠቃሽ ከሆነው የመከላከል አደረጃጀቱ በተጨማሪ በግራ መስመር ያደላ የማጥቃት ስርዐቱም ክፍተቶችን ሲያገኝ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የሚችል ስብስብ ነው። ይህ የቡድኑ ጠንካራ ጎን የበርካታ ተጨዋቾች ተሳትፎ ሳይደረግበት በተጋጣሚ የሜዳ ክልል ውስጥ በተወሰኑ ተጨዋቾች መሀከል በፍጥነት ላይ ተመስርቶ በሚደረግ ቅብብል ግቦችን ሊያስገኝለት እንደሚችል የአርባምንጩ ጨዋታ ያሳየ ነበር። በነገውም ጨዋታ ወልዋሎ የተከላካይ መስመሩን ወደ መሀል ሜዳ አስጠግቶ የሚጫወት እንደመሆኑ መጠን የመቐለ የተከላካይ አማካዮች ኳስ መቀማት የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ለቡድኑ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ይዘው መምጣት የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው። አማካዮቹ የቀሟቸውን ኳሶች ወደ ፊት ለማሳለፍ እጅግ ጠባብ ከሆነው የወልዋሎ የመሀል ሜዳ አቀራረብ ፈተና ሊገጥመው ቢችልም ይህን ማለፍ ከተቻለ ግን በተለይ ኳስ በአማኑኤል ገብረሚካኤል እግር ስር ስትገባ ለመቐለዎች ነገሮች ምቹ ይሆንላቸዋል። አማኑኤል በማጥቃት ሽግግር ወቅት ከወልዋሎው የቀኝ መስመር ተከላካይ እንየው ካሳሁን ጋር አንድ ለአንድ የሚገናኝባቸው እንዲሁም ከኑሁ ፋሴይኒ ጋር ቦታ በሚቀያየርባቸው ወቅቶች ቢስማርክ ኦፖንግ በወልዋሎ ሳጥን ውስጥ የሚኖረው ቦታ አያያዝ ዕድሎች ወደ ግብነት ለመቀየር ወሳኝነት ይኖረዋል። 

ዳኛ

ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ የዓዲግራቱን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እንደምመራው ይጠበቃል። እስካሁን አንድ ጊዜ የቀይ ካርድ ያሳየው እና 17 ጊዜ በቢጫ ካርድ ተጨዋቼችን የገሰፀው አልቢትሩ እስካሁን ስድስት ጨዋታዎችን መዳኘት ችሏል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ፋሲል ከተማ

የነገው የአዲስ አበባ ስታድየም ብቸኛ ጨዋታ 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኝ ይሆናል። ከድል ከራቀ ስድስት የሊግ ሳምንታትን ያሳለፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለተኛውን ዙር ወደ ድሬደዋ አምርቶ አንድ ነጥብ ይዞ በመመለስ ነበር የጀመረው። ቡድኑ 6ኛ ደረጃ ላይ ይቀመጥ እንጂ አሁንም ከመሪው ደደቢት ጋር የአምስት ነጥብ ልዩነት ብቻ ያለው በመሆኑ በዋንጫው ፉክክር ውስጥ እንደሚገኝ ግልፅ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጨረሻ ጊዜ አዲስ አበባ ላይ ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ቢያገባድድም ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ አሳክቶ ደረጃውን ለማሻሻል የጎንደሩን ድል ለመድገም እንደሚፋለም ይጠበቃል። ከተጋጣሚው በተለየ በመዲናዋ በሳምንቱ አጋማሽ ውጤት የቀናው ፋሲል ከተማ በአርባምንጭ እና ወልዋሎ ላይ ያሳካቸው ሁለት ድሎች እስከ 11ኛው ሳምንት አንዴም ያልገጠመውን ከዛ በኃላ ግን ሶስቴ ከደረሰበት ሽንፈት መልሶ ለመራቅ ጥሩ መንደርደሪያ ሆኖታል። ለአፄዎቹ በነጥብ በተጠጋጋው የሰንጠረዡ አናት ፉክክር ውስጥ ይበልጥ ከፍ ለማለት ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ትልቅ ቦታ ይኖረዋል።

የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሳላዲን ሰይድ እና ናትናኤል ዘለቀ እንዲሁም የፋሲል ከተማው አይናለም ኃይለ በዚህ ጨዋታ ላይ የማይኖሩ ሲሆን የአፄዎቹ አጥቂ ራምኬል ሎክ ከቅጣት መልስ ሊሰለፍ እንደሚችል ሰምተናል። ከዚህ ውጪ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሮበርት ፣ አስቻለው ታመነ እና አበባው ቡታቆም ለጨዋታው መድረሳቸው እርግጥ አልሆነም።

ከድል የራቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደወትሮው ሁሉ ነገም ሙሉ ትኩረቱን አጥቅቶ በመጫወት ላይ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ቡድኑ በመሀል ሜዳ ቅብብሎች ላይ ተመስርቶ ክፍተቶችን ማግኘት ሲቸግረው የሚጠቀምባቸው ቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶችም አማራ ማሌን ከነ ያሬድ ባየህ ጋር የሚያገናኙበት አጋጣሚዎች ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው። ተጋጣሚው ፋሲል ከተማ ከኃላ የነበረበትን ችግር ያቃለለ እንደመሆኑም መጠን በአብዱልከሪም ኒኪማ የሚመራው የአማካይ ክፍል ጫና ከሚያሳድርበት የአፄዎቹ የመሀል ክፍል ቦታ ላይ በቀላሉ የመቀባበያ አማራጮችን የሚያገኝ አይመስልም። በመሆኑም ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው የሚከላከሉ ቡድኖች ሲገጥሙት እንደሚያደርውገው ሁሉ እምነቱን ይበልጥ ከመስመር ተሰላፊዎቹ ወደ ውስጥ በሚላኩ ኳሶች ላይ እንደሚጥል ይታሰባል። በሁለቱም አማራጮች ውጤታማ ለመሆን ግን ቡድኑ ከኳስ ውጪ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በፋሲል የመከላከል ዞን ውስጥ እድሎችን ለመጠቀም የሚያስችል ክፍተትን ለማግኘት መታተር የሚጠበቅበት ይሆናል።

ፋሲል ከተማ ከያሬድ ባየህ መመለስ በኃላ ከኃላ መስመሩ ላይ መረጋጋት ይታይበት እንጂ የቀደሞው ፈጣን የማጥቃት ስርዐቱ ጉልበቱን ያጣ ይመስላል። ቡድኑ ከሜዳ ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የተጋጣሚን ቅብብል ለማፈን ብዙውን የሜዳ ክፍል አካለው በሚጫወቱት አማካዮቹ ጥረት በመነሳት ለመስመር አጥቂዎቹ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ይፈጥራል። ሆኖም አሁን ላይ ለነዚህ አጥቂዎች የሚደርሱ ኳሶች ይቅብብል ስኬት መውረድ እና የአጥቂዎቹ ቦታ አያያዝ ውጤታማነቱን ቀንሶት ታይቷል። አፄዎቹ ከዚህ አጨዋወት ግቦችን ለማግኘት የቅዱስ ጊዮርጊስን የተከላካይ መስመር በሜዳው ስፋት የሚለጥጥ የመስመር አጥቂዎች ቦታ አያያዝ እንዲሁም ከአማካይ ክፍሉ ደግሞ ፈጣን እና ጥሩ እይታ የታከለባቸው ኳሶችን ይፈልጋሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ የያስር ሙገርዋ እና ኤፍሬም አለሙ የአማካይ ቦታ እንዲሁም የአብዱርሀማን ሙባረክ እና ኤርሚያስ ኃይሉ የመስመር እንቅስቃሴ ወሳኝ ይሆናል።

እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከተማ እስካሁን 4 ጊዜ ተገናኝተዋል። ከዚህ ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 ጊዜ ያሸነፈ  ሲሆን አንዱ ድል በፎርፌ የተመዘገበ ነበር። ፋሲሎች ደግሞ አንዴ ሲያሸንፉ በቀረው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው ወቅት ከተቆጠሩ 9 ግቦች ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ የ5ቱ ፋሲል ከተማ ደግሞ የ4ቱ ባለቤቶች ናቸው።

– ክለቦቹ አዲስ አበባ ላይ አንድ ጊዜ ተገናኝተው 2-2 ተለያይተዋል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው ፋሲልን ነበር። (ጥር 9)

– ፋሲሎች ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ ባደረጓቸው 5 ጨዋታዎች የተሸነፉት በአንዱ ብቻ ነው።

– ቅስዱ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ጅማ አባጅፋርን ካሸነፈ በኃላ በአዲስ አበባ ስታድየም ባደረጋቸው 3 ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ዳኛ

ጥሩ እድገት እያሳዩ ከመጡ ዳኞች መሀከል የሚጠቀሰው እንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በ16ኛው ሳምንት ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡና ካደረጉት ጨዋታ መልስ ይህን ጨዋታ የሚመራ ይሆናል። ቴዎድሮስ እስካሁን በ7 ጨዋታዎች 26 የቢጫ ካርዶች እና 2 የቀይ ካርዶችን መዟል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *