ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር ወደ ድል ተመልሷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው ጅማ አባጅፋር 1-0 በማሸነፍ ከመሪው ደደቢት ጋር ያለውን የነጥበ ልዩነት ወደ አንድ አጥብቧል። 

በጅማ አባጅፋር በኩል በ16ኛው ሳምንት በሀዋሳ ሽንፈት ከደረሰበት ስብስብ መካከል ጋናዊው አሮን አሞሀን በመተካት መላኩ ወልዴ ወደ መጀመርያው አሰላለፍ ተካቶ በ4-4-2 አደራደር ሲቀርቡ በድሬዳዋ በኩልም በተመሳሳይ ካለፈው ጨዋታ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ በበረከት ይስሀቅ ምትክ ዮሴፍ ድንገቱ ለመጀመርያ ጊዜ ለቡድኑ መሰለፍ ችሏል።

በዛሬው እለት የ2018 የፊፋ አለም ዋንጫ ላይ ከሚዳኙ ዳኞች መካከል ስሙ በተካተተው በዓምላክ ተሰማ የተመራው ጨዋታ የመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን የጎል ሙከራዎች አልታዩበትም። ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር እንግዳው ቡድን ድሬዳዋ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ወደ ተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ ላይ ልዩነት መፍጠር ላይ ሲቸገሩና የወሰዱትን ብልጫ ወደ ግብ ማስቆጠር አጋጣሚ መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጅማ አባጅፋሮች በአንፃሩ ከዚህ ቀደም በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የነበራቸው ተነሳሽነት ወርዶ የታየ ሲሆን በመልሶ ማጥቃት ኄኖክ አዱኛ ከሚፈጥራቸው እድሎች ውጪ የተደራጀ እንቅስቃሴ ማድረግ ተስኗቸዋል። በዚህ ሁኔታ ነበር በ31ኛው ደቂቃ ከጅማ የመከላከል ቀጠና በረጅሙ የተላከውን ኳስ ኦኪኪኦላ አፎላቢ የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮችን ትኩረት ማጣት እና የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ወደ ግብነት በመቀየር ባለሜዳዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ይህች ጎል ለናይጄርያዊው አጥቂ 10ኛ የፕሪምየር ሊግ ግብ ሆና በመመዝገብ ለብቻው የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን እንዲመራ አድርጋዋለች።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ጅማዎች የተሻለ መነቃቃት የታየባቸው ቢሆንም ልዩነታቸውን ሊያሰፋ የሚችል የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በየመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ጋናዊው የድሬዳዋ አጥቂ አትራም ኩዋሜ በገጠመው ጉዳት በበረከት ይስሀቅ ተቀይሮ ሲወጣ በጅማ አባ ጅፋር በኩልም ወንድሙ (ሐብታሙ ወልዴ)ን በተቃራኒነት የገጠመው ተከላካዩ መላኩ ወልዴ በእንቅስቃሴ ከቡድን አጋሩ አሚኑ ነስሩ ጋር ተጋጭቶ በደረሰበት ጉዳት በቢንያም ሲራጅ ተቀይሮ ወጥቷል።

በሁለተኛው ግማሽ ድሬዳዋዎች ይበልጥ ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ሲሆን ጅማ አባጅፋሮች ውጤቱን ለማስጠበቅ ባለመ መልኩ አፈግፍገው መጫወትን ከመጫወታቸው በተጨማሪ የድሬዳዋ እንቅስቃሴም ወደ መከላከል እንዲያዘነብሉ ሲገፋቸው ተመልክተናል። ሆኖም እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ድሬዳዋዎች የጠራ የጎል ማስቆጠር አጋጣሚ የመፍጠር ችግራቸው ጎልቶ ሲወጣ ጅማዎች በአንፃሩ መስመር በኩል በፈጣን ሽግግር አደጋ በመፍጠር ረገድ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። 

እምብዛም የጎል ሙከራ ያልተስተናገደበት ጨዋታ በጅማ አባጅፋር 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ጅማዎች ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ ድሬዳዋዎች በወራጅ ቀጠናው ለመቆየት ተገደዋል።

አስተያየቶች

ገብረመድህን ኃይሌ – ጅማ አባ ጅፋር

” ያለፈውን ጨዋታ እንደመሸነፋችን የስነልቦና ችግር በተጫዋቾቼ ላይ ታይቷል። ያ ደግሞ በጨዋታው ብልጫ እንዲወሰድብን ምክንያት ሆኗል። ነገር ግን ኦኪኪ አፎላቢ በግል ጥረቱ የሚደነቅ ነበር። ባስቆጠረው ጎልም ሶስት ነጥብ ይዘን ወጥተናል። ”  

ስምዖን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

” በዛሬው ጨዋታ ሙሉውን 90 ደቂቃ ጥሩ ተጫውተናል። ከሜዳችን ውጪ እንዲህ ጫና ፈጥረን እንደመጫወታችን መሸነፋችን የሚያስቆጭ ነው። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *