ሪፖርት |ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሀከል 09፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የተደረገው የሊጉ 17ኛ ሳምንት ጨዋታ በባፕቲስቴ ፋዬ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ኢትዮጵያ ቡናን አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሳምንቱ መጨረሻ ካደረጓቸው ጨዋታዎች አራት ተጨዋቾችን ቀይረው ገብተዋል። ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ በድል ከተመለሰው ቡድን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ከኃላ ቶማስ ስምረቱን በኤፍሬም ወንደወሰን አማካይ መስመር ላይ አክሊሉ ዋለልኝ እና መስዑድ መሀመድን በአማኑኤል ዮሀንስ እና ኤልያስ ማሞ እንዲሁም መስመር አጥቂ ቦታ ላይ አስቻለው ግርማን በአስራት ቱንጆ ተክቷል። በመከላከያ የ3-1 ሽንፈት ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ የ5 ቢጫ  ቅጣት ያለበት ግርማ በቀለን እና ዘካርያስ ቱጂን በሲሴይ ሀሰን እና ጫላ ድሪባ እንዲሁም አማካዮቹን ሔኖክ ካሳሁን እና ጥላሁን ወልዴን በአዲስ ነጋሽ እና አልሀሰን ካሉሻ ቀይሮ ነበር ጨዋታውን የጀመረው። 

ጨዋታው ተጀምሮ እስከሚያልቅ አብዛኛው ደቂቃዎቹ በተጨዋቾች ጉሽሚያ እና ተደጋግሞ በሚሰማው የአልቢትሩ የፊሽካ ድምፅ እንዲሁም እሱን ተከትለው በሚሰጡ እጅግ በርካታ የቅጣት ምቶች ለተመልካች አሰልቺ ሆኖ የተካሄደ ነበር። ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለመደው የኳስ ቅብብላቸው ላይ በተመሰረተ የመሀል ለመሀል ማጥቃት ጨዋታውን ጀምረው 4ኛው ደቂቃ ላይ በአስራት ቱንጆ እና ሳምሶን ጥላሁን ቅንጅት ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሳጥን መግባት የቻሉበትን አጋጣሚ ደጋግሞ መፍጠር አልቻሉም። 14 እና 21ኛ ደቂቃዎች ያደረጓቸው የአስናቀ ሞገስ ሙከራዎችም ከኤልያስ ማሞ ቅጣት ምት በተሻገሩ ኳሶች የተገኙ ነበሩ። ቡናዎች መሀል ለመሀል ይፈጥሩት የነበረው ጫና በኤሌክትሪኮች የአማካይ ክፍል ሽፋን ባለመሳካቱም በወጣቱ የቀኝ መስመር ተከላካይ ኃይሉ ገብረትንሳይ የማጥቃት ተሳትፎ የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም ያደረጉት ጥረትም ተጨዋቹ በአንድ ለአንድ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ በደረሰበት ግጭት ምክንያት ፍሪያማ አልሆነም። ከዚህ ውጪ የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ቡድን በቀጥታ ለሳሙኤል ሳኑሚ ከሚጣሉ እና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጨዋቾች መሀል ሜዳ ላይ በሚቀሙ ኳሶች መነሻነት ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክሯል። 28ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ ከአዲስ ነጋሽ ከተቀማ ኳስ ያደረገው የረጅም ርቀት ሙከራም ለአብነት ተጠቃሽ ነበር። 

ባልተጠበቀ መልኩ አንድ ነጥብን ለማሳካት ያለመ የጨዋታ ዕቅድን ይዘው የገቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮችም ያደረጓቸው ሙከራዎች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። የቡድኑ ፈጣሪ አማካይ ካሉሻ አልሀሰን ከተከላካይ አማካዩ አዲስ ነጋሽ ጎን ሆኖ እና በመከላከል ስራ ላይ ተጠምዶ መመልከትም ትልቅ ብክነት ነበር። ካሉሻ ማጥቃትን ለማስጀመር ሲሞክርም በርካታ የተጋጣሚ አማካዮችን መጋፈጥ ይጠበቅበት ስለነበረ በቀላሉ ኳሶች ይበላሹበት ነበር።  የኃይሉን የቀኝ መስመር እንቅስቃሴ ለመግታት ወደ ግራ ሲወጣ የሚታየው ዲዲዬ ለብሪ ይህን አላማውን ማሳካት ቢችልም 35ኛው ደቂቃ ላይ በቡና ሳጥን ውስጥ ከፈጠረው ዕድል ውጪ በማጥቃት ተሳፎፍው ውጤታማ አልነበረም። ከሳምሶን ጥላሁን የተቀማን ኳስ ከታፈሰ ተስፋዬ ተቀብሎ ተክሉ ከርቀት ያደረገው የ6ኛ ደቂቃ ሙከራ እና ካሉሻ 25ኛው ደቂቃ ላይ በቀጥታ የመታው የቅጣት ምት በኤሌክትሪክ በኩል የታዩ ሙከራዎች ነበሩ።


ከእረፍት መልስ የጨዋታው ይዘት እምብዛም ሳይቀየር ባሰልቺነቱ ቢቀጥልም የዲዲዬ ለብሪ መውጣት እና በኃይሌ እሸቱ መተካት እንዲሁም የኃይሌ ቦታ አያያዝ ለታፈሰ የቀረበ መሆኑ ለኃይሉ ነፃነትን የሚሰጥ እና የኤሌክትሪኩን የግራ መስመር ተከላካይ ጫላ ድሪባን ጫና ውስጥ የሚከት ነበር። ቡናዎች 59ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ግርማን በዚህ ቦታ ላይ ቀይረው ማስገባታቸውም ቦታውን ለመጠቀም ማሰባቸውን የሚያመላክት ነው። በመሆኑም ቡድኑ 60ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ ከተክሉ ታፈሰ ከተቀማ ኳስ ከርቀት ሞክሮ በግቡ ቋሚ ከተመለሰበት በኃላ ሌላ ዕድል እንዲያገኝ ሆኗል። ሆኖም አስቻለው እና ሳኑሚ በቀኝ መስመር ይዘው የገቡት ኳስ በተከላካዮች ርብርብ ሙከራ ከመሆን ድኗል። በመቀጠል ቁመተ ለግላጋውን አጥቂ ባፕቲስቴ ፋዬን ወደ ሜዳ ያስገቡት ቡናዎች ተጨዋቹን ኢላማ ያደረጉ ኳሶችን ወደ ሳጥን ማድረስ የጀመሩ ሲሆን 76ኛው ደቂቃ ላይ ፋዬ ከሳኑሚ ጋር ተቀባብሎ ሳጥን ውስጥ የገባበት መንገድም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነበር።

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከመጀመሪያው በተሻለ ሁለት አጥቂዎችን ፊት መስመር ላይ ቢያጣምሩም ለተጨዋቾቹ ኳስ የሚያደርሱበት መንገድ ግን ከመጀመሪያው የተለየ አልነበረም። በተወሰኑ አጋጣሚዎች በአጥቂዎቹ ጫና ሲፈጠርበት ለስህተት ሲቃረብ ይታይ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና የመሀል ተከላካዮች ጥምረትም ነፃ ሆኖ ጨዋታውን እንዲያገባድድ ሆኗል። ቡድኑ መሀል ላይ በድንገት የሚገኙ ኳሶችን ለአጥቂዎቹ ለማድረስ ቢሞክርም ጉልበታቸውን ከመጨረስ ውጪ የፈየደው ነገር የለም። በሂደትም እንደ ዲዲዬ ለብሪ ሁሉ ኃይሌም ወደ መስመር በመውጣት በመከላከሉ ላይ ማመዘኑ አልቀረም። መሀል ሜዳ ላይ የሚገኙ ኳሶችን ወደ ግብ ዕድልነት ለመቀየር በግሉ ሲፍጨረጨር የነበረው ካሉሻ አልሀሰን በቡና አማካዮች በቀላሉ ይታፈን ስለነበር በሔኖክ ካሳሁን ተቀይሮ ከወጣ በኃላ የኢትዮ ኤሌክትሪኮች መከላከል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጎልቶ ታይቷል። 

ይህ ሂደት ኢትዮ ኤሌክትሪክን እስከ ጭማሪ ደቂቃዎች ድረስ ቢያዘልቁትም ከመሸነፍ ግን ሳይተርፍ ቀርቷል። በኢትዮጵያ ቡና መለያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ባፕቲስቴ ፋዬ ከማዕዘን ተሻግራ የተጨረፈችን ኳስ በእግሩ ከጎሉ ቅርብ ርቀት ላይ በመምታት ነበር የጨዋታውን ልዩነት የፈጠረችውን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው። ድሉን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው ዙር አሸናፊነቱን ማስቀጠል ሲችል አሁንም በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ በነጥብ ተቀራርበው ከተቀመጡት ክለቦች ጋር ለሻመሚዮንነት መፋለሙን ይቀጥላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *