ኒጀር ለምታስተናግደው የቶታል አፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ቅዳሜ መደረግ ጀምረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ምበመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ቡሩንዲን ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ታስተናግዳለች፡፡
የማጣሪያ ድልድሉ ካፍ ይፋ ካደረገ በኃላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩትን አጥናፉ አለሙን የ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አድርጎ ሹሟል፡፡ ሆኖም ሹመቱ ግዜውን ያልጠበቀ በመሆኑ የብሄራዊ ቡድን የዝግጅት ግዜ አጭር እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በአንፃሩ ቡሩንዲ በተሻለ ተጋጣሚዋን ባወቀችበት ቅፅበት ዝግጅቷን ጀምራለች፡፡
የቡሩንዲ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ሐሙስ ምሽት አዲስ አበባ የደረሰ ሲሆን አርብ እና ቅዳሜ ለጨዋታው ልምምድ ሰርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ ዝግጅቱን በኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ አከናውኗል፡፡
የቡሩንዲው አሰልጣኝ ጆስሊን ቢፕፉቡሳ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ጨዋታውን አሸንፈው ለመመለስ እንዳሰቡ ገልፀዋል፡፡ “የመጣነው ለማሸነፍ ነው፡፡ አሸንፈን እንመለሳለን ብለን እንጠብቃለን፡፡ ስለኢትዮጵያ ቡድን ብዙ መረጃ የለንም፤ በርግጥ ብዙ ለማወቅ አልሞከርንም ስለዚህም ብዙ መረጃ የለንም፡፡”
ጨዋታውን ሶማሊያዊያን ዳኞችን እንዲመሩት ካፍ መርጧቸዋል፡፡ የመሃል አርቢትር ኑር ሙሃዲን መሃመድ፣ ረዳቶቹ አብዲ መሃመድ ኑር እና ሁሴን ማኦ ሀሰን ጨዋታውን ይመራሉ፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤአ. በ2001 እንዲሁም ቡሩንዲ በ1995 ለዓለም ወጣቶች ዋንጫ አልፈዋል፡፡ ሆኖም በቅርብ አመታት ውስጥ ለአፍሪካ የታዳጊዎች ውድድር ሲያልፉ አይታይም፡፡ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ለመልሱ ጨዋታ የሚጠቅመውን ውጤት ዛሬ በሜዳው ማስመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡