የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቶታል አፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ለማሳተፍ የማጣሪያ ጉዞውን ከሊቢያ ጋር በመጪው ረቡዕ ካይሮ ላይ በመጫወት ይጀምራል፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ( 4፡00 ) ጨዋታው ወደሚደረግበት ካይሮ ያመራሉ፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ በአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ መሪነት ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አሰልጣኟ ብሄራዊ ቡድኑ ቅዳሜ ካደረግ ልምምድ በኃላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠችው አስተያየት ስለተጋጣሚ ቡድን መረጃ ማግኘት አለመቻሉን አስረድታለች፡፡ “አላገኘንም! ማግኘት አልቻልንም፡፡ እስካሁን እየፈለግን ነው፡፡ በእኛም በኩል በፌድሬሽኑም በኩል ከ2016 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውጤት ውጪ ምንም ያገኘነው ነገር የለም፡፡ ፎቶ ራሱ አላገኘንም፡፡” ያለችው ሰላም በነበረው አጭር የዝግጅት ግዜ በቡድኗ ላይ መሻሻልን እንዳየች ተናግራለች፡፡ “የነበረው የዝግጅት ግዜ አጭር ነው ግን ለመጀመር በቂ ግዜ ነው ብዬ ነው ማስበው፡፡ አሁን በተዘጋጀንባቸው ግዜያቶች ከዕለት ዕለት የተወሰነ ለውጥ እያሳየ ያለንበት ደርሰናል፡፡ ጨዋታው ደግሞ የበለጠ ችግራችን፣ ድክመታችን ያሳየናል ብዬ አስባለው፡፡ ስለዚህም የመጀመሪያውን ጨዋታ በጉጉት ነው የምንጠብቀው፡፡”
ኢትዮጵያ በ2012 ኤኳቶሪያል ጊኒ ባስተናገደችው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከተሳተፈች በኋላ በቀጣዮቹ ውድድሮች ላይ መሳተፍ አልቻለችም፡፡ በጥንካሬ ይታወቅ የነበረው ቡድንም ቀስ በቀስ ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ርቋል፡፡ “ሁልግዜ የምንወድቀው ጠንካራ ቡድን ስለሌለን ሳይሆን በቂ እውቀት ስለሌለን ነው፡፡ ስለተጋጣሚ ቡድን አናውቅም፣ የወዳጅነት ጨዋታ አድርገን ስለራሳችን አናውቅም፡፡ ድጋሚ ደግሞ ስለተጋጣሚ ቡድን የሚሰጡ አስተያየቶች አሉ፡፡ ተጋጣሚን ማግዘፍ እና የእኛን ቡድን ማቅለል፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች ከዚህ በፊት ተፅእኖ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ምንያህል እንደሰራን የምናውቀው ጨዋታው ላይ ነው፡፡” ስትል አሰልጣኝ ሰላም ስለ ቡድኑ ያለፉት አመታት ችግር ገልፃለች።
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ላለፉት 18 ወራት ከጨዋታ መራቁን ተከትሎ ከፊፋ የሃገራት ደረጃ ውጪ ሆኗል፡፡ ይህም ለመጪው ጨዋታ እንደመነሳሻ እንደሚሆን አሰልጣኝ ሰላም ታስረዳለች፡፡ “እያንዳንዱ ችግሮች ለመፍትሔ ያነሳሳሉ፡፡ ትክክል ነው ያልሰራነውን አናገኝም፡፡ ከደረጃው ወጥተናል፡፡ ይህም ችግር የሚያነሳሳ ነው ብዬ ነው ማስበው፡፡”
ከሉሲዎቹ ስብስብ 7 ተጫዋቾች ከካይሮ ጉዞ ተቀንሰዋል፡፡ ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ፣ ዘለቃ አሰፋ፣ ፀጋነሽ ተሾመ፣ ቡርቱካን ገብረክርስቶስ፣ ሰርካዲስ ጉታ፣ ትዕግስት ዘውዴ እና ሲሳይ ገብረዋህድ ከስብስቡ የተቀነሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ አንጋፋዋ ቡርቱካን በጉዳት ከቡድኑ ውጪ የሆነችው ብሩክታዊት ግርማን ተክታ ወደ ቡድኑ የተቀላቀለችው ከጥቂት ቀናት በፊት ነበር፡፡