የቡሩንዲ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ኢትዮጵያን አዲስ አበባ ላይ በቶታል አፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ 2-0 አሸንፏል፡፡ የሁለቱ ሃገራት ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
“ለውጤቱ ሃላፊነቱን እኔ እወስዳለው” አጥናፉ አለሙ
“ውድድሩ ጠንካራ ነው በእርግጥ፡፡ ወጣቶቹ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ለውጤቱ ግን ሃላፊነቱን እኔ እወስዳለው፡፡ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል ሜዳው ውስጥ መሆን ያለበትን፡፡ ማድረግ የምንችለው ነገር ጠንክሮ መስራት ነው፡፡”
ማድረግ ያለባቸውን ነገሮች አድርገዋል፡፡ ልጆቹ በቦታቸው ላይ ማድረግ ያለባቸውን አድርገዋል፡፡ የቡድኑ ጥንካሬ፣ ተጭኖ የመጫወቱ እና የእድሜ ተመጣጣኝነቱ ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሚችሉትን አድርገዋል፡፡ ትላንት ጀምሮ በተወሰነ ደረጃ ከኮሚሽነሩ ቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ላይ ተወያይተናል አንስተናልም፡፡ በልምምድ ሰዓት የምናያቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ይህ ግልፅ ነው በእድሜ ደረጃ ያለው ነገር በጣም የጎላ ነው፡፡ የእኛ በእድሜ ደረጃ ተፈትነው ወይም በዶክተሮች ተመርምረው የመጡ ናቸው፡፡ በአቅም እና ፊዚካል ባሉ ነገሮች ላይ ተበልጠናል፡፡ ይህ ደግሞ ለውጤቱ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ይህ ፈተና ነው፡፡ ፈተናውን ለመወጣት እኩል መሆን አለብህ፡፡ በእግርኳስ በእድሜ አቻ የሆኑ ነገሮችን ትጠብቃለህ፡፡ በአንፃሩ ውጤቱ እንዳየነው ነው፡፡ አፀፋ ሊሆን የሚችለው የተሻለ ሰርቶ መዘጋጀት ነው፡፡”
“የግቡ አገባብ በመጀመሪያ የግብ ጠባቂው ትኩረት ማጣት ነው፡፡ የልምድ ማጣቱ አንዱ ትልቁ ነገር ነው፡፡ ውድድሮችን የማግኘት ነገሮች የሉም፡፡ ይህ ቢኖር መቅረፍ ይቻል ነበር፡፡ ልምምድ ብቻ ሳይሆን በውድድር ሂደት ውስጥ ማየት የሚገባህን ጉደለትህን ማየት ይገባል፡፡”
“በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ወስነን ተሳካልን” ጆስሊን ቢፕፉቡሳ
“ጥሩ ጨዋታ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ለመግጠም አስቸጋሪ ቡድን ነው ምክንያቱም በአንድ እና ሁለት አጫጭር ቅብብል የሚጫወት ቡድን ነው እናም አስቸጋሪ ጨዋታ ነበር፡፡”
“የስታራቴጂ ጉዳይ ሆኖ ተጋጣሚያችን አጫጭር ኳስ የሚጫወት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ የሚመጣ ተጭኖ የሚያጠቃ መሆኑን ስላወቅን እኛ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ወስነን ተሳካልን፡፡”
“በመልሱ ጨዋታ በሚገባ ለመጫወት እንሞክራለን፡፡ በሜዳችን እንደመጫወታችን በሚገባ ኳስ መስርተን እንጫወታለን፡፡ አሁን የተሻለ እድል አለን፡፡ ተመሳሳይ ጨዋታ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ እንደሁኔው ነው የሚወስነው፡፡”
“አዎ ከ20 ዓመት በታች ናቸው፡፡ የሃባሪ ወጣቶች ግዙፍ ናቸው፡፡ የአየር ሁኔታውም ይመቻቸዋል፡፡ ወጣቶቹ በሙሉ ከእድሜያቸው ትንሽ በላይ የሚመስሉ ናቸው፡፡ ከዛ በተጨማሪ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ይሰራሉ፡፡ በአካል ብቃት በታክቲክ እና ቴክኒክ ስንዘጋጅ ነበር፡፡ የቡሩንዲ የክለብ ተጫዋቾች በካምፕ ነው የሚቆዩት ስለዚህም በሚገባ ይመገባሉ፡፡”