በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 15ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አቻ ተለያይቶ አጋማሹን በመሪነት አጠናቅቋል፡፡ ረፋድ 4፡00 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ ደጋፊዎች ሞቅ ያለ ድጋፍ የደመቀ ሆኖ አልፏል፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር ሲስተናገድ በሁለተኛው አጋማሽ አዲስ አበባ ብልጫ ታይቶበታል፡፡ በመጀመሪያው 45 በርካታ የግብ እድሎች ተፈጥረው ሁለቱም ክለቦች ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡ በባህርዳር በኩል በ14ኛው ደቂቃ ሙለቀን ታሪኩ ያሳለፈለትን ኳስ ሳላምላክ ተገኝ አግኝቶ የመታው ኳስ ወደ ውጪ የወጣበት እና በ18ኛው የአዲስ አበባው ሚሊዮን ሰለሞን ያሻገረው ኳስ ግብ ከመሆኑ በፊት የባህርዳሩ ግብ ጠባቂ ምንተስኖት አሎ ያወጠባት በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ከታዩ ሙከራዎች ለግብ እጅግ የቀረቡ ነበሩ፡፡
የጣና ሞገዶቹን በብቸኛ አጥቂነት የመራው ሙሉቀን ከቡድን አጋሮቹ በፍጥነት እርዳታ አለማግኘቱ እና የባህርዳር ተጫዋቾች ይበልጥ ወደ ሓላ መሳባቸው የማጥቃት ሽግግር ላይ ሲፈተኑ ባለሜዳዎቹ አዲስ አበባዎቹ በበኩላቸው በማጥቃት ወረዳው ላይ የሚያገኙትን እድሎች በቀላሉ ሲያበላሹ ተመልክተናል፡፡ በ40ኛው ደቂቃ ፍቃዱ አለሙ የመታው ቅጣት ምት ምንተስኖት በግሩም ሁኔታ ሲያመክንበት ከሁለት ደቂቃ በሃላ ከግቡ አፋፍ በቅርብ ርቀት ወደ ግብነት ከመለወጡ በፊት አሁንም ምንተስኖት በመስመር ላይ ኳስን ይዟል፡፡ አጋማሹ ከመጠናቀቁ በፊት ሁለት የግብ እድሎችን ያመከነው ምንተስኖት በጉዳት በሁለተኛው አጋማሽ በሃይማኖት አዲሱ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ አዲስ አበባዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ሲወስዱ ባህርዳዎች ተዳክመው ታይተዋል፡፡ የባህርዳር አምበል ደረጄ መንግስቱ እምብዛም ወደ ፊት አለመሄዱ እና ይበልጥ የአዲስ አበባን የመሃል ሜዳ ብልጫ መመከት ባለመቻላቸው አጋማሹን ምድብ መሪው እንዲዳከም አድርገውታል፡፡ ሆኖም በዚህ 45 የታዩ የግብ ሙከራዎች አነስተኛ ነበሩ፡፡ ባህርዳሮች በመልሶ ማጥቃት በ56 እና 58ኛው ደቂቃዎች እድሎችን አግኝተው የነበረ ቢሆንም ሙከራዎች ከመደረጋቸው አስቀድሞ የአዲስ አበባ ተከላካዮች ኳስን አውጥተዋል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 8 ደቂቃዎች ሲቀሩ የአዲስ አበባው እንዳለማው ታደሰ በግንባሩ የገጨው ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶበታል፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች አዲስ አበባዎች ግብ ለማግኘት ተጭነው ቢጫወቱም ይህን ነው የሚባል ሙከራ ጨዋታው ሳያስተናግድ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ ምድብ ሀ በ32 ነጥብ መምራቱን ሲቀጥል አዲስ አበባ ከተማ በ30 ነጥብ በግብ ክፍያ በሽሬ ተበልጦ ሶስተኛ ነው፡፡ የጣናው ሞገድ የውድድር አጋማሹን ምድቡን በመምራት አገባደዋል፡፡