​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች – ክፍል 2 

ከ18ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብሮች ውስጥ ሶስቱ በደረጃ ሰንጠረዡ የታችኛው ክፍል ላይ ለውጥ የሚያስከትሉ ናቸው። የክፍል ሁለት ዳሰሳችንም ይርጋለም ፣ ድሬደዋ እና አዲስ አበባ ላይ የሚከናወኑትን እነዚህን ጨዋታዎች የሚመለከት ይሆናል።

ሲዳማ ቡና ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ይርጋለም ላይ የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ወደ ወራጅ ቀጠናው መግቢያ አፋፍ ላይ ሆነው እርስ በእርስ ይጭምወታሉ። ቀስ በቀስ ወደ አደጋው ዞን እየተጠጋ የመጣው ሲዳማ ቡና በኢትዮጵያ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ በተከታታይ የደረሰበት የ1-0 ሽንፈት በመጀመሪያው ዙር ከሰበሰባቸው 18 ነጥቦች ፈቀቅ እንዳይል አድርገውታል። ወልዋሎ ዓ.ዩም በተመሳሳይ ሁለት ሽንፈቶችን አስተናግዶ መቐለ ከተማን እየመራ የነበረበት ጨዋታም በመቋረጡ ደረጃውን ለማሻሻል አልቻለም። በመሆኑም ይህ ጨዋታ ቡድኖቹ ከአደጋ ወጥተው ወደ መሀለኛው የሰንጠረዡ ክፍል ለመጠጋት የሚጥሩበት እንደሚሆን ይጠበቃል። 

ሲዳማ ቡና ዉስጥ ምንም የጉዳት ዜና የሌለ ቢሆንም ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመራጮቹ ሙጃይድ መሀመድ ፣  ሚካኤል ኃሲሶ እና ዮናታን ፍሰሀን አገልግሎት አያገኝም፡፡ በወልዋሎ ዓ.ዩ በኩል ደግሞ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ በጉዳት ብርሀኑ አሻሞ በቅጣት የማይሰለፉ ሲሆን የተከላካዩ ተስፋዬ ዲባባም የመግባት ጉዳይ አለየለትም። 

ሲዳማ ቡናም ሆነ ወልዋሎ ዓ.ዩ የማጥቃት ሂደታቸው ዋነኛ መዳረሻ አድርገው የሚጠቀሙት የመስመር አጥቂዎቻቸውን ነው። በዚህ መሰረትም የሲዳማዎቹ አብዱለጢፍ መሀመድ እና አዲስ ግደይ እንዲሁም የወልዋሎ ዓ.ዩዎቹ ከድር ሳሊህ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ከተጋጣሚዎቻቸው የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ዋነኛው የጨዋታው ትዕይንት  እንደሚሆን ይጠበቃል። ይሁንና በዚህ ረገድ ቢመሳሰሉም ሁለቱም ለማጥቃት የሚጠቀሙባቸው መንገዶች ግን የተለያዩ ናቸው። ሲዳማ ቡና ወደ ራሱ ሜዳ ቀረት ብሎ የሚያገኛቸውን ኳሶች የሶስትዮሽ ቅርፅ ካለው የአማካይ ክፍሉ በቀጥታ ለአጥቂዎቹ የሚያደርስ ሲሆን በወልዋሎ በኩል በዋለልኝ ገብሬ እና አፈወርቅ ኃይሉ መሪነት በቅርበት ከሚደረጉ ቅብብሎች የመጨረሻዎቹ ዕድሎች እንደሚፈጠሩ ይጠበቃል። በመሆኑም ሲዳማዎች አማካይ ክፍል ላይ የተጋጣሚያቸውን የመሀል ተሰላፊዎች የኳስ ፍሰት ለማቋረጥ ዋነኛ የማጥቃት መሳሪያ የሆኑት የመስመር አጥቂዎቻቸው እገዛ ሊያስፈልጋቸው ሲችል ወልዋሎዎችም ተከላካይ ክፍላቸው ከግብ ርቆ በሚቆይባቸው አጋጣሚዎች ሲዳማዎች በረጅሙ የሚጥሏቸውን ኳሶች ከመነሻቸው ለማክሸፍ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ጫና የማሳደር ግዴት ይኖርባቸዋል። 

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ክለቦቹ በመጀመሪያው የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው በሶስተኛው ሳምንት ዓዲግራት ላይ ተገናኝቸው 0 0 ተለያይተዋል።

– ሲዳማ ቡና ዘንድሮ ሜዳው ላይ ካደረጋቸው 8 ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

– ወልዋሎ ዓ.ዩ ለመጨረሻ ጊዜ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች በሙሉ ሽንፈት ሲገጥመው 12 ግቦች ተቆጥረውበት አንድ ጊዜ ብቻ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ 4ኛ ዳኝነት ወደ ዛምቢያ የሚያቀና መሆኑን ተከትሎ የይርጋለሙን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ፌደራል ዳኛ ሀብታሙ መንግስቱ ሆኗል። አልቢትሩ በሊጉ እስካሁን በዳኛቸው 3 ጨዋታዎች 1 የቀይ እና 18 የማስጠነቀቂያ ካርዶችን አሳይቷል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ



ድሬደዋ ከተማ ከ ወልዲያ

በመጨረሻው የሰንጠረዡ ክፍል የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ መገናኘታቸው ፉክክራቸውን ከፍ እንደሚያደርገው ይታሰባል። ካለፉት ሶስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኘው ድሬደዋ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት አልቻለም። ቡድኑ ወልዋሎ ላይ ካስቆጠራቸው ሁለት ግቦች በኃላም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስኖታል። ከተጋጣሚው የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልዲያ ሀዋሳ ላይ ባለቀ ሰዐት ያስቆጠራት የምንያህል ተሾመ ጎል ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ አደረገችው እንጂ ወደ 12 ዝቅ ሊል ተቃርቦ ነበር። ቡድኑ እንደ ድሬደዋ ሁሉ ከድል ከራቀ ሶስት ጨዋታዎች ተቆጥረዋል። ይህን ተከትሎም ጨዋታው ሁለቱም ክለቦች የመጋቢትን ወር ያለሽንፈት እንዳያገባድዱ የመጨረሻ ዕድል የሚያገኙበት ይሆናል።

የድሬደዋ ከተማዎቹ አህመድ ረሺድ እና ጀማል ጣሰው በጉዳት ምክንያት ለጨዋታው እንደማይደርሱ ሲሰማ ሳምሶን አሰፋ ከረጅም ጊዜ ጉዳቱ እንደሚመለስ ይጠበቃል። የወልዲያዎቹ ሰለሞን ገብረመድህን እና አዳሙ መሀመድ አሁንም በጉዳት ላይ የሚገኙ ተጨዋቾች ሲሆኑ ነጋ በላይ እና ተስፋዬ አለባቸውም የጉዳት ዝርዝሩን ተቀላቅለዋል።

እንደየተጋጣሚው ሁኔታ እና እንደጨዋታው ቦታ አሰላለፉን የሚቀይረው ድሬደዋ ከተማ ጨዋታው በሜዳው እንደመደረጉ ሶስቱን አጥቂዎቹን በፊት መስመር ላይ እንደሚጠቀም ይጠበቃል። አማካይ መስመር ላይ የሚጣመሩት ዮሴፍ ደሙዬ እና ዘላለም ኢሳያስም የቡድኑን የኳስ ቁጥጥር በመምራት ክፍተቶችን ተጠቅመው ለነ አትራም ኩዋሜ ዕድሎችን የመፍጠር ሀላፊነት ይኖርባቸዋል። የብሩክ ቃልቦሬ እና ሀብታሙ ሸዋለም የወልዲያ አማካይ ጥምረትም የሁለቱን የድሬ ተጨዋቾች እንቅስቃሴ በቅርበት የመከታተል ሀላፊነት እንደሚኖረው ይታመናል። በወልዲያ በኩል ከብቸኛው አጥቂ ዐንዷለም ንጉሴ እና ከሁለቱ የተከላካይ አማካዮች መሀል ምንያህል ተሾመ ፣ አሳልፈው መኮንን እና መስፍን ኪዳኔ ቡድናቸው ወደ ማጥቃት የሚያደርገውን ሽግግር በማፋጠን የማጥቃቱ ዋነኛ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይገመታል። መስፍን እና አሳልፈው ከዚህ ባለፈ ለነ ተስፋዬ እገዛ በማድረግ የድሬደዋ የመስመር አጥቂዎች ከአማካይ ክፍላቸው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ለማቋረጥ በሚሞክሩበት የጨዋታ ሂደት ወቅት የድሬደዋ የመስመር ተሰላፊዎች የሚኖራቸው ምላሽ ተጠባቂ ይሆናል።        

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ክለቦቹ እስካሁን ከተገናኙባቸው ሶስት ጨዋታዎች በሁለቱ ያለግብ ሲለያዩ አምና ድሬደዋ ላይ በተደረገው ጨዋታ ወልዲያ 2-0 ማሸነፉ ይታወሳል።

– ድሬደዋ ዘንድሮ ያሸነፋቸው 2ቱ ጨዋታዎች በሜዳው የተደረጉ ሲሆኑ በቀሪዎቹ አንዴ ተሸንፎ 5 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 

– 8 ጊዜ ከሜዳው ወጥቶ በተጫወተባቸው አጋጣሚዎች አንዴም ድል ያልቀናው ወልዲያ 5 ጊዜ ሲሸነፍ በ3 አጋጣሚዎች ደግሞ አንድ ነጥብ ይዞ ተመልሷል።

ዳኛ

– የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በፌደራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ የመሀል ዳኝነት ይደረጋል። ዳንኤል እስካሁን ምንም የቀይ ካርድ ያላሳየ ሲሆን በተሰየመባቸው አራት ጨዋታዎች 18 ጊዜ ተጨዋቾችን በቢጫ ካርድ ገስጿል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ



ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አርባምንጭ ከተማ

በሁለት ነጥቦች ልዩነት ብቻ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ለሚገኙት ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል። እስካሁን በተለያዩ ሳምንታት ያገኛቸውን ድሎችን ተከትሎ በሚያጋጥሙት ሽንፈቶች ምክንያት ካለበት ፈቀቅ ማለት የተሳነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሁንም ድሬደዋን ካሸነፈ በኃላ በሶስት ጨዋታዎች ያገኘው አንድ ነጥብ ብቻ ነው። በቅርብ ጊዜያት ውጤቶቹ ከተጋጣሚው የተሻለ የሆነው አርባምንጭ ከጎንደር እና መቐለ ሽንፈቶቹ በኃላ በእንዳለ ከበደ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ሲዳማን መርታቱ ከወረጅ ቀጠናው መውጫ በር ላይ አቁሞታል። ይህን ጨዋታ ማሸነፍም ከኤሌክትሪክ ጋር በ5 ነጥቦች የሚያራርቀው ሲሆን ቦታውን ለሌላ አዲስ ክለብ አስረክቦ ከቀጠናው የሚወጣ ይሆናል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ከቀናው ደግሞ ተጋጣሚውን ወደ ታች ገፍቶ በአንድ ነጥብ ልዩነትም ቢሆን ከመውረድ ፍራቸው በጥቂቱ ሊተነፍስ የሚችልበት ዕድል ይኖራል።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል ተከላካዩ በረከት ቦጋለ በ5 ቢጫ ካርድ ምክንያት ከጨወታው ውጪ ሲሆን በ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በብሩንዲው ጨዋታ የተሰለፈው ግብ ጠባቂው ፂዮን መርዕድ ክለቡን እንደሚያገለግል ተሰምቷል። ግርማ በቀለን ከ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት መልስ የሚያገኘው ኤሌክትሪክ ለ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከተመረጠው ስንታየው ዋቀጮ ውጪ የሌሎቹን ተጨዋቾች አገልግሎት እንደሚያገኝ ይጠበቃል።

ጨዋታው ለሁለቱም ተጋጣሚዎች ነጥብ ለማግኘት ወሳኝ ከመሆኑ አንፃር የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት እንደሚንፀባረቅበት ይጠበቃል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በተለየ ለዋነኛ ፈጣሪ አማካዩ ካሉሻ አልሀሰን ወደ ተጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል የተጠጋ ሚና በመስጠት የማጥቃት ሂደቱን እንዲያግዝ የሚያደርግበት ሁኔታ ይኖራል። በዚህ ረገድ ተጨዋቹ ከአማኑኤል ጎበና እና ምንተስኖት አበራ ጋር የሚገናኝባቸውን አጋጣሚዎች ተጠባቂ ያደርጋቸዋል። ቡድኑ ዲዲዬ ለብሪንም ከመስመር ይልቅ ከታፈሰ ተስፋዬ ጎን በመሆን ፊት ላይ እንዲያጠቃ ሀላፊነት ሊጥልበት ይችላል። አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ የመሀል አማካዮቹን ለተከላካይ ክፍሉ ቅርብ አድርጎ በዋናነት በመልሶ ማጥቃት ለእንዳለ ከበደ እና ተመስገን ካስትሮ በሚላኩ ኳሶች በሁለቱ መስመሮች እንደሚያጠቃ ይጠበቃል። አርባምንጮች ወደ መሀል ሜዳው ቀርቦ ለመጫወት ሲሞክር ስህተቶች የማያጡት የባለሜዳዎቹን የተከላካይ መስመር ደካማ ጎን ኢላማ በማድረግ በብርሀኑ አዳሙ እና በረከት አዲሱ ጥምረት ፈጣን ጥቃት የመሰንዘር ዕቅድ ይኖራቸዋል። ሆኖም በጨዋታው ቀድሞ ግብ ያስቆጠረ ቡድን ውጤቱን ለማስጠበቅ ወድኃላ ማፈግፈጉ ይሚቀር አይመስልም።

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ክለቦቹ ከእስካሁኑ 13 ግንኙነታቸው ውስጥ 4 ጊዜ አቻ ሲለያዩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 5 ጊዜ እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ 4 ጊዜ ድል ማድረግ ችለዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ኤሌክትሪኮች 17 እንዲሁም አዞዎቹ 13 ግቦችን አስቆጥረዋል።

– አዲስ አበባ ላይ በተደረጉት 6 ጨዋታዎችም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 10 ጎሎችን አስቆጥረው ሶስት ጊዜ ሲያሸንፉ አንድ ጊዜ ብቻ  ውጤት የቀናቸው አዞዎቹ 2 ጊዜ ግቦችን አግኝተዋል።

– ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዘንድሮ በ5 ጨዋታዎች የክልል ቡድኖችን አስተናግዶ አንዴ ብቻ ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በሶስት ጨዋታዎች 8 ግቦች ተቆጥረውበት ተሸንልፏ።

– አዞዎቹ ዘንድሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡናን ለመግጠም ወደ መዲናዋ ብቅ ይሉ ሲሆን በሁለቱ ጨዋታዎች በድምሩ 5 ግቦችን አስተናግደው ተሸንፈዋል።

ዳኛ

– ዘንድሮ አምስት ጨዋታዎችን ዳኝቶ አንዴም የቀይ ካርድ ያላሳየው ፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አልቢትሩ እስካሁን 20 ጊዜ የቢጫ ካርዶችን መምዘዙን የዘንድሮ የዳኝነት ሪከርዱ ያሳያል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *