ከፍተኛ ሊግ | ሰበታ ከተማ እና ለገጣፎ በድል የመጀመርያውን ዙር አጠናቀዋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ማክሰኞ ተካሂደው ለገጣፎ ለገዳዲ እና ሰበታ ከተማ አሸንፈዋል።

በ15ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ለገጣፎ ላይ ለገጣፎ ለገዳዲ ቡራዩ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፏል። በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ወደ ለገጣፎ የግብ ክልል መቅረብ የቻሉት ቡራዩ ከተማዎች በሚካኤል ደምሴ በ2ኛው ደቂቃ የግብ ሙከራ በማድረግ የለገጣፎን ግብ ክልል መፍተሽ ጀምረዋል። በ8ኛው ደቂቃ አጥቂው ኢሳያስ ታደሰ የተገኘውን ቅጣት ምት ወደ ግብ ቢያሻግረውም የግብ ጠባቂው በግራ እግሩ እንደምንም ጨርፎ የማዕዘን ምት ሲያወጣበት በ28ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አምበሉ አቡበከር ደሳለኝ በግምት ከ18ሜትር የመታው ኳስ የግቡ አግዳሚ መትቶ ወጥቶበታል። በ35ኛው ደቂቃ ላይ  ደባላ ሮባ ያደረገው ሙከራም እንግዶቹ ካደረጓቸው የግብ ሙከራዎች መካከል የሚጠቀሱ ነበሩ።

በባለሜዳው ለገጣፎ በኩል በ13ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ ታደሰ በግንባሩ በመግጨት የመጀመሪያውን ሙከራ ሲያደርጉ በ19ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በቅጣት ምት የተገኘውን ኳስ በሱፍቃድ ወደግብ አክርሮ ሲመታው የቡራዩ ግብ ጠባቂ ይዞት ወደመሬት በሚወድቅበት ቅፅበት ኳስ ከእጁ አፈትልኮ በመውጣቱ  በአቅራቢያው የነበረው መዝገቡ ቶላ አስቆጥሮ ለገጣፎን መሪ ማድረግ ችሏል።


ከእረፍት መልስ ቡራዩ ከተማ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ የነበረው ሲሆን በርካታ ሙከራዎችን ቢያደርግም ፍሬያማ መሆን ሳይችል ቀርቷል።  በሱፍቃድ ተሰማ በ46ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት፣ በ58ኛው ደቂቃ አቡበከር ደሳለኝ ከሳጥን ውጪ መትቶ ወደ ወረጪ የወጣበት እና በ74ኛው ደቂቃ ኢሳያስ ታደሰ ከቅጣት ምት ሞክሮ የግቡን ብረት ጨርፋ የወጣባቸው ኳሶች የሚጠቀሱ ነበሩ። በለገጣፎዎች በኩል ደግሞ እዮብ ታደሰ በ65ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማ ኳስን በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት እና በ83ኛው ደቂቃ ፋሲል አስማማው በረጅሙ የተሻገረትን ኳስ ተቆጣጥሮ የሞከረውና በተመሳሳይ ለጥቂት የወጣበት ኳሶች የግብ ልዩነታቸውን ሊያሰፉባቸው የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።

በ90ኛው ደቂቃ ኢሳይያስ ታደሰ ከዳኛው ጋር በፈጠረው እሰጣገባ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰነበተበት ክስተት የጨዋታው የመጨረሻ ሁነት ነበር።

 

ውጤቱን ተከትሎ ለገጣፎ ለገዳዲ ነጥቡን 26 በማድረስ በ6ኛ ደረጃ የመጀመርያውን ዙር ሲያጠናቅቅ ቡራዩ ከተማ ከመሪዎቹ ጋር ያለውን ልዩነት የሚያጠብበትን እድል ሳይጠቀምበት ቀርቶ በ27 ነጥብ 4ኛ ላይ ለመርጋት ተገዷል።

በ14ኛው ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ወደ ደሴ ያመራው ሰበታ ከተማ 4-2 ማሸነፍ ችሏል። አብይ ቡልቲ ፣ ጌዲዮን ታደሰ፣ እንዳለ ፍቃዱ እና ሐብታሙ ረጋሳ ሰበታ ከሜዳው ውጪ ሶስት ነጥቦች ይዞ የተመለሰባቸውን ጎሎች ማስቆጠር የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው። በውጤቱ መሰረት ሰበታ ከተማ በ27 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ደሴ ከተማ በ11 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *