በጋና በሚቀጥለው አመት ለምታስተናግደው የቶታል አፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ካይሮ ላይ ሊቢያን የገጠመው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ካይሮ ላይ በግብ የተንበሸበሸ ውጤትን አስመዝግቧል፡፡ ሉሲዎቹ ሊቢያን 8-0 በመርታት ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ከጫፍ ደርሰዋል፡፡
በካይሮ ፔትሮ ስፖርት ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠረቻቸው 6 ግቦችን ጨዋታወን መደምደም ችላለች፡፡ ረሂማ ዘርጋ በ5ተኛው እና 19ኛው ሎዛ አበራ በ16ኛው እና 26ኛው ምርቃት ፈለቀ በ34ኛው ደቂቃ እንዲሁም ብዙአየሁ ታደሰ በ44ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ግቦች ለእረፍት ሉሲዎቹ 6-0 እየመሩ አምርተዋል፡፡ ከእረፈት መልስ ረሂማ ቤትልሄም ከፍያለው የግብ ልዩነቱን ወደ 7 ስታሰፋ ረሂማ በ59ኛው ደቂቃ ሃትሪክ የሰራችበትን ግብ አስቆጥራለች፡፡ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በኢትዮጵያ 8-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ዛሬ ሃትሪክ የሰራችው ረሂማ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመጨረሻ ግዜ የነጥብ ጨዋታ ሲያደርግም በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን ከመረብ ማዋህዷ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያም ከ14 ዓመት በፊት ማላዊን እንዲሁም ከ6 ዓመት በፊት ኬንያን 5-0 ያሸነፈችበት ውጤት በትልቅነት ተመዝግቦ የቆየ ቢሆንም የዛሬውን ድል ሪከርዱን ያሻሻለ ነው።
ከድሉ በኃላ የቡድኑ አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠችው አስተያየት 80 በመቶ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የሚያስፈልገውን ውጤት እንደያዙ ገልፃለች፡፡
የኢትዮጵያ እና ሊቢያ መልስ ጨዋታ በመጪው ማክሰኞ አዲስ አበባ ላይ ይካሄዳል፡፡ ሉሲዎቹ ሐሙስ ጠዋት አዲስ አበባ እንደሚደርሱ ታውቋል፡፡