ብሄራዊ ሊግ ፡ ጅማ ከነማ በውዝግብ ታጅቦ ሩብ ፍፀሜውን ተቀላቀለ

የምድብ 3 ጨዋታዎች የምድብ 4 ጨዋታዎችን ተከትለው ተደርገዋል፡፡ ጅማ ከነማ እና ሀላባ ከነማም ወደ ሩብ ፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በሳቢያን ሜዳ ሼር ኢትዮጵያን የገጠመው ጅማ ከነማ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሃይደሩስ መሃመድ ባስቆጠራት ግብ 1-0 አሸንፏል፡፡ ሼር ኢትዮጵያዎች ከምድቡ መሰናበታቸውን አስቀድመው ቢያረጋግጡም በዚህ ጨዋታ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ በሙሉ ሃይል መጫወታቸው የበርካቶችን ትኩረት ስቧል፡፡

ግቧ ከተቆጠረች በኋላ የጅማ ከነማው አሰልጣኝ ፋንታዬ አባተ ወደ ሼር ኢትዮጵያው አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃም መቀመጫ በመሄድ ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆነ የደስታ አገላለፅ አሳይተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባትም ጨዋታው ለጥቂት ጨዋታዎች ለመቋረጥ ተገዷል፡፡ የጅማ ከነማው ወጌሻ እና ግብ አስቆጣሪው ሃይደሩስም በግርግሩ ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የጅማ ከነማው አሰልጣኝ ፣ ግብ አስቆጣሪው ሃይደሩስ እና የክለቡ ወጌሻ በፀጥታ ሃይሎች ተይዘው በመኪና ተወስደዋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት የሼር ኢትዮጵያው አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃም በተፈጠረው ሁኔታ እንዳዘኑ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ አሰልጣኙ ባሳየው ነገር በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ተጫዋቾቼ መደረግ የሚገባውን ነገር በሙሉ አድርገዋል፡፡ ሁልጊዜም የማስተምራቸው ለማልያቸው ክብር እንዲጫወቱ እና ዲሲፕሊን እንዲኖራቸው ነው፡፡ ቀድመን መሰናበታችንን ብናረጋግጥም ዛሬ ተጫዋቾቼ ያሳዩት ለማልያቸው ያላቸውን ክብር ነው፡፡ እግርኳስ የሚያስፈልገውም ይህ ነው፡፡ ጅማዎች እንድንለቅላቸው ነበር የሚፈልጉት፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ ›› ሲሉ የተሰማቸውን ብስጭት ገልፀዋል፡፡

halaba

ሀላባ ከነማ መቐለ ከነማን 1-0 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜው ያለፈ ቡድን ሆኗል፡፡ አካሉ አበራ ወሳኟን የማሸነፍያ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ድሉን ተከትሎ ሀላባ ከነማ በ11 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበልጦ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡ ከጨዋታው በኋላ የሀላባ ከነማው አሰልጣኝ ተመስገን ይልማ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ለመቐለ ከነማ ያላቸውን አክብሮት ገልፀዋል፡፡ ‹‹ ለመቐለ ከነማ አክብሮት አለኝ፡፡ ጨዋታውን ለመርሃ ግብር ማሟያ ብቻ ቢያደርጉም ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ተጫውተዋል፡፡ ተጫዋቾቼ ያላቸውን አቅም ሁሉ ተጠቅመው ጨዋታውን አሸንፈው ወጥተዋል፡፡ በሩብ ፍፃሜው የምንገጥመው አውስኮድ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ያለው ከባድ ቡድ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለማለፍ የምንችለውን ሁሉ እናገደርጋለን ›› ብለዋል፡፡

ሰበታ ከነማ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲን 2-1 ቢያሸንፍም ሁለቱም ተያይዘው ምድቡን ተሰናብተዋል፡፡

 

የሩብ ፍፃሜ ተጋጣሚዎች የሚከተሉት ናቸው

ድሬዳዋ ከነማ ከ አዲስ አበባ ከነማ

ጅማ አባ ቡና ከ ፌዴራል ፖሊስ

አውስኮድ ከ ሀላባ ከነማ

ጅማ ከነማ ከ ሆሳእና ከነማ

——–

ፎቶ – ከላይ ጅማ ከነማ ፤ ከታች ሀላባ ከነማ

——-

የየምድቦቹን የደረጃ ሰንጠረዥ ፣ ውጤቶች ፣ ቀጣይ ጨዋታዎች እና ከፍተኛ ግብ አግቢዎች ደረጃ ለማወቅ ሜኑ ላይ Competitions ላይ ከሚመጡት አማራጮች Ethiopian National League ቀጥሎም Tables ይጫኑ

ያጋሩ