በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ላይ ሀዋሳ ከተማን ከደደቢት ያገናኘው ጨዋታ በሀዋሳ አንድ ለምንም አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወቀል ። ሆኖም በጨዋታው መሀል እና ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የሀዋሳ ከነማ ደጋፊዎች ይፈፅሙት የነበረው ያልተገባ ባህሪ በቀጣይ መታረም እንደሚገባው የደደቢት እግርኳስ ክለብ ለሚዲያዎች በላከው ደብዳቤ አሳውቋል ።
“ጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር የታየበትና ሀዋሳ ከነማም ያገኘው ውጤት በመልካም ጨዋታ የታጀበ ነው ። ነገር ግን በክለቡ ደጋፊዎች በጨዋታው ወቅትና ከጨዋታው በኋላ የተንፀባረቀው ባህሪ እና የተፈፀሙ ድርጊቶች ቀድሞ ከነበረው የሀዋሳ ከተማ ጨዋ ደጋፊዎች ባህሪ ጋር ሲተያይ እጅግ አሳዛኝ እና ለወደፊቱም ፈፀሞ መደገም የሌለበት ድርጊት መሆኑን እናምናለን” ይላል ደብዳቤው።
ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በአንዳንድ ሜዳዎች ላይ እየተከሰቱ ላሉ ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጡ ተግባሮች መባባስ እንደ ምክንያት እየቀረበ ያለው በየጨዋታው የሚመደቡ የጨዋታ ኮምሽነሮች የሚያጋጥሙ ክስተቶችን (ችግሮችን) በሪፖርታቸው በጉልህ ሁኔታ አለመግለፃቸው ነው። ይህ መሆኑም በቀጣይ ችግሮች እንዳይደገሙ እንዲሁም ያጠፋው አካል ላይ የእርምት እርምጃ እንዳይወሰድበት እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ የሚገለፅ በመሆኑ ኮምሽነሮች ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል።