ኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የመንን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኤኤፍሲ እስያ ዋንጫ ማሳለፉን ተከትሎ ብሄራዊ ቡድኑ ከካታር ወደ ሳውዲ አረቢያ ባመረበት ወቅት ከየመን መንግስት እውቅና ተሰጥቶታል፡፡
የየመን ብሄራዊ ቡድን ከዶሃ ወደ ሪያድ ማክሰኞ ሲያመራ የየመን ፕሬዝደንት አብደሮቦ ሃዲ ለተጫዋቾች እና የቴክኒክ አባላቱን አቀባበል አድርገዋል፡፡ ፕሬዝደንት ሃዲ ለአሰልጣኝ አብርሃም ያላቸውን አድናቆት በንግግራቸው የገለፁ ሲሆን ለአሰልጣኙም ያላቸውን ከበሬታ እና ምስጋናም አቅርበዋል፡፡
የመን ከምድብ ስድስት ፊሊፒንስን ተከትላ በመጪው አመት የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች ለምታስተናግደው የእስያ ዋንጫ ማለፏ ሲታወስ አሁን ባለችበት ወቅታዊ አለመረጋጋት ምክንያት የሜዳ ላይ ጨዋታዎቿን ዶሃ ላይ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
የየመን እግርኳስ ማህበር የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆኖ የሰራው አሰልጣኝ አብርሃም የየመን ኦሎምፒክ ቡድንን ይዞ በ2013 ለእስያ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ማሳለፍ ችሏል፡፡