ሪፖርት | የፍቅረየሱስ ድንቅ ግብ ለሀዋሳ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አስጨብጣለች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18ኛው ሳምንት መርሃ ግብር ሀዋሳ ከተማ ደደቢትን አስተናግዶ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ ሶስት ነጥብ ጨብጧል፡፡ ሁለቱ ክለቦች ባላቸው ወቅታዊ አቋም ምክንያት ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ የደጋፊው ስሜታዊ ድርጊት እና አወዛጋቢ የሆኑ የዳኝነት ውሳኔዎችን የተመለከትንበት ነበር፡፡

በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ መርጠው የተንቀሳቀሱ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች እንደሁልጊዜው ሁሉ በኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ወስደዋል፡፡ በ5ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ወደ ሳጥን ውስጥ እየገፋ ገብቶ ወደ ግብ የሞከራት ኳስ አቅጣጫዋን ስታ ወደ ውጭ የወጣችው ኳስ በሀዋሳ በኩል ፤ ጌታነህ ከበደ ከርቀት መትቶ ኢላማው ሳይጠብቅ የወጣበት ሙከራ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የሚጠቀሱ የግብ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ከ15ኛው ደቂቃ በኃላ የጨዋታውን መንፈስ የቀየሩ ድርጊቶች በስታዲየሙ ሲስተዋሉ ተመልክተናል፡፡ ዳንኤል ደርቤ ወደ ደደቢት የሜዳ ክፍል ኳስን እየነዳ ሲገባ ብርሀኑ ቦጋለ በእጅ ነክቷል በሚል ሀዋሳዎች የቅጣትምት ቢጠብቁም ረዳት ዳኛው ኃይለራጉኤል ወልዳይ ኳሱን የነካው ዳንኤል ነው በሚል ለደደቢት ቅጣት ምት በመስጠት ጨዋታው ሲቀጥል የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን ውሀ ያዘለ ፕላስቲክ በመወርወር አሰምተዋል፡፡ ከዚህች ድርጊት በኃላም ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅ የሚፈጠሩት አላስፈላጊ ድርጊቶች አመዝነው ታይተዋል፡፡

በ18ኛው ደቂቃ ዳዊት ፍቃዱ ወደ ደደቢት የግብ ክልል እየገፋ ገብቶ በነፃ አቋቋም ለነበረው እስራኤል እሸቱ ሰጥቶት ወጣቱ አጥቂ ሞክሮወደ ውጪ ሲወጣበት በ21ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን መሀል ለመሀል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ዳዊት ፍቃዱ እየገፋ ገብቶ ከግብ ጠባቂው አማራ ክሌመንት ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ክሌመንት አዞንቶ በግሩም ሁኔታ መልሶበታል፡፡ በ40ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘችውን ቅጣት ምት ፍሬው ሰለሞን በቀጥታ መቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበትም በመጀመርያው አጋማሽ በባለሜዳዎቹ በኩል የሚጠቀሱ የግብ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ ደደቢት በተቃራኒው ደካማ የማጥቃት አቀራረብ የነበረው ሲሆን ገና በጊዜ አቤል ያለውን በጉዳት ማጣታቸው ይበልጥ እንዲዳከሙ እና በጠንካራነቱ የሚጠቀስ የግብ አጋጣሚ እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል፡፡

በዝናብ የታጀበው የሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ በሚፈጠሩ ውዝግቦች መቆራረጥ የበዛበት ነበር፡፡ በተለይ የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች በ17ኛው ሳምንት ወደ ወልዲያ አምርተው 1 ለ 1 በተለያዩበት ጨዋታ ክለባችን ላይ ለተፈፀሙ ድርጊቶች ፌድሬሽኑ አፋጣኝ ውሳኔ ሊሰጥ ይገባል የሚል ቅሬታን አሰምተዋል፡፡ በዚህ የጨዋታ አጋማሽ ደደቢቶች በተሻለ መልኩ የተንቀሳቀሱበት ቢሆንም ሀዋሳዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በዚህም አጋማሽ ወስደዋል፡፡

51ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፍሬው ሰለሞን በግል ጥረቱ የሰጠውን ኳስ እስራኤል እሸቱ ቢያገኛትም ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ሙከራ ሲሆን 53ኛው ደቂቃ ላይ እንግዳው ቡድን ደደቢት በሽመክት ጉግሳ አማካኝት የግብ እድል አግኝቶ ዳንኤል ደርቤ ደርሶ አስጥሎታል፡፡ 59ኛው ደቂቃ ላይ ፍቀረየሱስ ከርቀት የመታትን ኳስ አማራ ክሌመንት ተወርውሮ ሲያወጣበት በ63ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ያሸገረውን ኳስ ለጌታነህ ከበደ ሰጥቶት ከግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘው ጌታነህ አገባው ተብሎ ሲጠበቅ ሶሆሆ በግሩም ብቃት አድኖበታል፡፡

በጨዋታው የመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል፡፡ በሁለተኛው ዙር ከተስፋ ቡድን ያደገው ቸርነት አውሽ እና አላዛር ፋሲካን ቀይረው ካስገቡ በኃላም በተሻለ መልኩ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ 68ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት አውሽ እና ፍሬው ሰለሞን በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን በመግባት የተሻገረውን አላዛር ፋሲካ በግልፅ ሁኔታ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ የሀዋሳዎች ተደጋጋሚ ጫና በመጨረሻም ወደ ውጤታማነት ተለውጦ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉዓለም ረጋሳ ያሻገረውን ኳስ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን የደደቢት ተጫዋቾችን በማለፍ አማራ ክሌመንትን ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ አስቶ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ተጨማሪ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ እድሎች ሳይፈጠሩ ሀዋሳ ከተማ መሪኑን በማስጠበቅ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወጥቷል፡፡ በውጤቱ መሰረት መሪው ደደቢት ከተከታዮቹ ያለውን ልዩነት ያስፋት እድሉን ሳይጠቀምበት ሲቀር ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 25 በማድረስ ራሱን ከመሪዎቹ አስጠግቷል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ

ጨዋታው ለኛ ከባድ ነበር፡፡ ያለፈው የወልዲያ ጨዋታ ላይ በርካታ ጉዳቶች ነበሩብን፡፡ ድካም ነበር ፤ ከዛ አንፃር ጫና ነበረው፡፡ በኛ በምንፈልገው አንፃር ተጫውተናል ማለት ይከብደኛል፡፡ ከረፍት መልስ በተወሰነ መልኩ ተጫዋቾች ቀይረን አስገብተናል፡፡ ካለመረጋጋት ያመከናቸው በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ ፤ ሰአቱ እየገፋ በሄደ ቁጥር ደግሞ ተጫዋቾቼ ለግብ ማስቆጠር የነበራቸው ጉጉት ከፍተኛ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን በማሸነፋችን ደስ ብሎኛል፡፡

ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ – ደደቢት

ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ ሁለቱም ኳስ የሚጫወት ቡድን ናቸው፡፡ ነገር ግን ደጋፊው የፈጠረው ተፅእኖ እኛን አዘናግቶናል፡፡ ሀዋሳ በመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ ነበሩ፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ እኛም ጥሩ ነበርን፡፡


በኢንተርኔት መቆራረጥ ምክንያት ሪፖርቱን በወቅቱ ማቅረብ አልቻልንም።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *