በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ ጎልተው መውጣት የቻሉ እና ተስፋ የተጣለባቸው ተጫዋቾችን እያስተዋወቅናችሁ እንገኛለን። በዚህ ሳምንት ፅሁፋችንም በመጋቢት ወር በተካሄደው የህዳሴው ግድብ ዋንጫ ላይ ባሳየው ድንቅ አቋም በአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ የሁለተኛው ዙር የኢትዮዽያ ቡና የውድድር ጉዞ ውስጥ የመጀመርያ ተሰላፊነት ዕድል በማግኘት ከመልካም እንቅስቃሴውም ባሻገር ለጎሎች መቆጠር ምክንያት እየሆነ የሚገኘው የመስመር ተከላካይ ኃይሌ ገብረትንሳይን ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ትውልዱ በነገሌ ቦረና የሆነው ኃይሌ ለቤተሰቡ የመጀመርያ ልጅ ሲሆን በልጅነቱ ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጣው። ከቤተሰቦቹ መካከል ኳስን ተጫውቶ ያሳለፈ ባይኖርም እግርኳስን የሚወዱ መሆናቸውን ኃይሌ ይናገራል። ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ መኖርያቸውን ባደረጉበት ጎተራ አካባቢ እግርኳስን መጫወት የጀመረ ሲሆን በሒደት እግርኳስ እህል ውሀው ሆኖ በ2007 ወደ መከላከያ በማምራት የተስፋ ቡድኑን ተቀላቅሏል። ኃይሌ የመጀመርያ ክለቡ መከላከያ ብዙ እንዲሻሻል እንደረዳው ይገልፃል። ” በክለቡ ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። መከላከያ በነበረኝ የሁለት አመት ቆይታ በእግርኳስ ህይወቴ ላይ ብዙ መሻሻልን አሳይቻለው ። ”
በመከላከያ ተስፋ ቡድን የሁለት አመታት ቆይታ ያደረገው ኃይሌ ቀጣይ ጉዞው ወደ ኢትዮጵያ ቡና ነበር። ወጣቱ የመስመር ተከላካይ ወደ ቡና ያመራበትን ሒደት እንዲህ ይገልፀዋል። ” መከላከያ እያለሁ የውድድር አመቱ ሲጠናቀቅ በእረፍት ጊዜዬ ሙገር ሜዳ ከሙገሮች ጋር አብሬ ልምምድ እሰራ ነበር ። በዚህ ወቅት ታዲያ ታላቁ አሰልጣኝ ስዩም አባተ ይመለከተኝ ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሄጄ እንድጫወት እድሉን አመቻችቶልኝ በእርሱ ጥቆማ መሰረት በ2009 የኢትዮጵያ ቡናን ተስፋ ቡድን ልቀላቀል ችያለው። ስዩም ኢትዮጵያ ቡና እንድገባ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ምን ማድረግ እንዳለብኝ ብዙ ነገሮች አሰልጣኝ ይመክረኝ ነበር። አሁን ላለሁበት ደረጃም የእርሱ አስተዋፆኦ የጎላ ነው ብዬ መናገር እችላለው።”
ኃይሌ በኢትዮጵያ ቡና ያሳየው እድገት ፈጣን የሚባል ነው። አንድ የውድድር ዘመን በተስፋ ቡድኑ ካሳለፈ በኋላ ነበር ወደ ዋናው ቡድን ያደገው። በውድድር አመቱ የመጀመርያ አጋማሽ የመሰለፍ እድል ባያገኝም በህዳሴው ግድብ ጨዋታ ላይ ባገኘው እድል ተጠቅሞ ፈረንሳዊው አልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስን ማሳመን ችሏል። ሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ከተጀመረ በኋላ የተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ላይም ሙሉ 90 ደቂቃ ለመጫወት በቅቷል። ሁለት ወሳኝ የመስመር ተጫዋቾቹን ያጣው ኢትዮጵያ ቡናም በቀኝ መስመር ተስፋ የሚጥልበት ተጫዋች ያገኘ ይመስላል።
በተሰጠው እድል ተጠቅሞ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የሚያምነው ኃይሌ በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ መልካም የሚባል ነው። ከዚህ ቀደም የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የነበረ መሆኑ ለማጥቃት ተሳትፎው አስተዋጽኦ እንዳደረገለት ያምናል። ” መከላከያ እያለሁ የምታወቀው በአማካይ ተጨዋችነቴ ነው። አሁን ነው አሰልጣኙ ወደ መስመር ተከላካይነት የለወጠኝ። በዚህም ደስተኛ ነኝ። የአማካይ ስፍራ ተጨዋች መሆኔ ደግሞ ለአሁኑ ሚናዬ ትልቁን እገዛ አድርጎልኛል። ይበልጥ በማጥቃት እገዛው ላይ ሰው ቀንሼ በድሪብል ወደ ፊት እንድሄድ አድርጎኛል ። ” የሚለው ኃይሌ ስለ መስመር ተከላካይነትም እንዲህ ይናገራል።
” የመስመር ተከላካይ ስትሆን ሁለት ነገሮች ይጠበቁብሀል። አንደኛው የመከላከል ቦታውን ከሌሎች ተከላካዮች ጋር በመሆን ማገዝ አለብህ። ሁለተኛው በማጥቃቱ ደግሞ አጥቂዎቹን ማገዝ ይጠበቅብሀል። በዘመናዊ እግርኳስ የመስመር ተከላካዮች ይህንን ሚና ሲወጡ እያየን ነው ። እንዲያውም የመስመር ተከላካዮች ጎሎች ሁሉ እያስቆጠሩ ይገኛሉ። ተከላካይ ስለሆንክ ብቻ ቆመህ መጫወት የለብህም። የተከላካይ ክፍሉን እንዲሁም የአጥቂውን ክፍል ማገዝ አለብህ ብዬ ነው የማስበው። ”
ኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው ዙር መልካም ጉዞ እያደረገ ይገኛል። በትላንትናው እለት መከላከያን 2-0 በመርታትም ደረጃውን ወደ ሁለተኝነት ከፍ አድርጓል። በጨዋታው በተቆጠሩት ሁለቱም ጎሎች ላይ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው ኃይሌ ድንቅ እንቅስቃሴ ከማድረጉ ባሻገር አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ሲገስፁት ተስተውሏል። አሰልጣኙ ምን ብለውት ይሆን? ኃይሌ መልስ አለው። ” (እየሳቀ) ይሉኝ የነበረው ‘ ሁለት ጎል ተቆጥሯል ፤ ከአንተ የምንፈልገውን አገልግሎትም አግኝተናል። አሁን ታክቲካሊ ዲሲፒሊንድ ሆነህ በመከላከሉ ላይ አተኩር። ከዚህ በኋላ ወደ ፊት አትሳብ የቀረውን ስራ የመስመር አጥቂዎቹ ሚና ነው። ‘ የሚል ምክር ነው የሰጡኝ። እንዳየኸውም የታዘዝኩትን ሰርቼ ወጥቻለው። ”
የቡድን አጋሩ የሆነው መስዑድ መሐመድን የሚያደንቀው ኃይሌ “የተለየ ተጫዋች ነው።” ብሎ የሚገልፀው አምበሉ ምክር እንዳልተለየው ገልጿል። ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም ምስጋናውን አቅርቧል። ” በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ መሀል መጫወት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾች ምኞት ነው። በነሱ ፊት ስትጫወት ደስ የሚል ስሜት ነው ያለው። እያደረጉልኝ ያለው ነገር ከሚባለው በላይ ነው። ስሳሳት እየመከሩ፣ ጥሩ ስሆን ከጎኔ በመሆን እያበረታቱኝ ይገኛሉ። በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እፈልጋለው።”