በ2018 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ሉሲዎቹ ወደ ግብጽ አምርተው ሊብያን 8-0 በማሸነፍ በኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ታሪክ ትልቁን ድል አስመዝግበዋል፡፡ በጨዋታው ላይ ቡድኑን በአምበልነት የመራችው ረሂማ ዘርጋው ሶስት ጎሎችን አስቆጥራ ሐት-ትሪክ በመስራት ደምቃ የዋለች ሲሆን በሁለት ተከታታይ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ላይ ሐት-ትሪክ በማስመዝገብም ታሪክ መስራት ችላለች፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ጠዋት ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ረሂማ ስለ ጨዋታው ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠችው አስተያየት በጥሩ እንቅስቃሴ ድል ማድረጋቸውን ተናግራለች፡፡ ‹‹ ወደ ስፍራው ስንጓዝ ይህን ጨዋታ አሸንፎ ለመመለስ እንደሆነ አስቀድመን ተናግረናል። በቀጥታ ጨዋታውን በሬዲዮን እንደሰማችሁት ጥሩ ነበርን። የእኛ ጥሩ መሆን ውጤቱንም ጥሩ አድርጎት በሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፈን እንድንመጣ አድርጎናል። ይህ ጨዋታ በቀጣይ በራስ መተማመናችን ላይ ትልቅ እገዛ ያደርግልናል። ’’ ያለችው ረሂማ የጎል ልዩነቱ መስፋት የሊብያን ደካማነት እንደማያመላክት ‹‹ ተጋጣሚ ቡድን ደካማ ቢሆን እንኳን አንተም ጥሩ ካልሆንክ ይሄን ሁሉ ጎል አታስቆጥርም። ›› በማለት ገልጻለች፡፡
ዘንድሮ በጥሩ አቋም ላይ የምትገኘው ረሂማ በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ንግድ ባንክ 6 ጎሎችን አስቆጠራ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክር ውስጥ የምትገኝ ሲሆን በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ሐት-ትሪክ መስራት ችላለች፡፡ የውድድር አመቱን እንደአጀማመሯ ሁሉ በስኬት ለማጠናቀቅም አልማለች፡፡
‹‹አምና በጉልበት ጉዳት ምክንያት ብዙ መጫወት አልቻልኩም ነበር፡፡ 2010 ላይ ግን ከክለቤ ጋር ጥሩ የውድድር ጊዜ በማሳለፍ ዋንጫ ማንሳት ነው አቅዴ። ከዚህ በተጨማሪ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች መሆንም አስባለው ። ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን ጥሩ የውድድር አመት እያሳለፍኩ ነው ። ብሔራዊ ቡድን ማሊያ ሁለተኛ ሐት-ትሪኬን ትላንት ሰርቻለው። በቀጣይም ከፈጣሪ ጋር ጠንክሬ እሰራለው።››
ሉሲዎቹ ከሊብያ ጋር የሚያደርጉትን የመልስ ጨዋታ በመጪው ማክሰኞ የሚያደርጉ ሲሆን በእግር ኳስ ታይቶ የማይታወቅ ተዓምር ካልፈጠረ በቀር ወደ ቀጣዩ ዙር አንድ እግራቸውን አስገብተዋል፡፡ ይህን ዙር ካለፉ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማምራት የሴኔጋል እና አልጄርያን አሸናፊ የሚገጥሙ ይሆናል፡፡ ረሂማም ብሔራዊ ቡድኑ ከሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች መቅረት በኋላ በድጋሚ ለውድድሩ የመቅረብ ተስፋዋን ገልጻለች፡፡ ‹‹ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ አቅደን ነው የተነሳነው። ቡድናችን ውስጥ ትልቅ ህብረት አለ፡፡ የብዙ ተጨዋቾች ህልም የአፍሪካ ዋንጫ መግባት ነው። እኔ በግሌ ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ መጫወት በጣም እፈልጋለው። በዚህ የማጣርያ ጨዋታ ላይ ብቻ መቆም አንፈልግም። ትላንት ራሱ ከጨዋታዉ በፊት ስብሰባ ላይ እርስ በራሳችን ስናወራ የምናስበው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መጫወትን ነው። እናሳካዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለው ።››