የአሰልጣኞቻችን የእግርኳስ አስተሳሰብ ፣ የስልጠና ሀሳብ ፣ የስራ ህይወት እና የውጤታማነት መንገድ ዙርያ ትኩረት የሚያደርገው ” የአሰልጣኞች ገጽ ” አምዳችን የዛሬ ተረኛ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ናቸው።
የመድሃኒአለም ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር በነበሩበት ወቅት የአደይ አበባ ቡድንን በመያዝ የአሰልጣኝነት ስራን የጀመሩት ሰውነት ቢሻው በቀጣይ በህዝብ ማመላለሻ ኮርፖሬሽንን ከሶስተኛ ዲቪዚዮን ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ከመለሱ በኋላ ለትምህርት ወደ ጀርመን አምርተዋል። ከአሰልጣኝነት ትምህርቱ በኋላ ጭነት ማመላለሻ ድርጅት (ጭማድ) ፣ መብራት ኃይል ፣ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ ጉምሩክ፣ ሙገር፣ ኒያላ፣ እርሻ ሰብል እንዲሁም በድጋሚ ፣ ኒያላን ካሰለጠኑ በኋላ ወደ የመን አምርተዋል። ከየመን መልስ ደግሞ በ2003 በክለብ አሰልጣኝነት ህይወታቸው የመጨረሻ የሆነው ትራንስ ኢትዮጵያን አሰልጥነዋል።
አሰልጣኝ ሰውነት ከክለብ እግርኳስ ይልቅ በብሔራዊ ቡድን ስራ የሚታወቁ ሲሆን በ1978 የወጣት ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ፣ በ1989 የታዳጊ ወጣት ብሔራዊ ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ፣ በ1993 ዓ.ም የታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ፣ በ1994 የዋናው ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ፣ በ1997 በድጋሚ የብሄራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ፣ በ1998 ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እና የዋናው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል። ቀጥሎም በ2002 መጨረሻ የቶም ሴንትፌይት ምክትል ሆነው ዘደ ብሔራዊ ቡድን የተመለሱ ሲሆን ከ3 ወራት በኋላ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ተሹመው እስከ ጥር 14 ቀን 2006 ድረስ ቆይተዋል። በቆይታቸውም 3 የሴካፋ ዋንጫ ፣ 1 የሴካፋ ከ20 አመት በታች ዋንጫ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እና የቻን ተሳትፎን አሳክተዋል።
አሰልጣኙ ከ30 አመት በላይ የዘለቀው የአሰልጣኝነት ህይወታቸው ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል። የዛሬው የክፍል አንድ መሰናዷችንም የብሔራዊ ቡድን ስኬታማ ጉዟቸው እና ከዋልያዎቹ በኋላ ስላለው ህይወታቸው ያተኩራል። ለቃለ ምልልሱ እንዲያመችም ከ”አንቱ” ይልቅ “አንተ” በሚለው ተጠቅመናል።
በሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም
ለዚህኛው ትውልድ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎን ያሳካህ አሰልጣኝ በመሆንህ ምን የተለየ ነገር ይሰማሀል?
★ እኔ ምንም የተለየ ነገር አይሰማኝም፡፡ የምኮራበት፣ የምንቀባረርበትና የምዘንጥበት ምክንያትም የለም፡፡ እንዲያውም እኔ ይበልጥ ደስ ይለኝ የነበረው ኢትዮጵያ በየሁለት አመቱ ለአፍሪካ ዋንጫና በየአራት አመቱ ደግሞ ለአለም ዋንጫ ተወዳዳሪ ብትሆን ነበረ፡፡ ለዛ የሚያበቃ አቅሙና ተጫዋቾች ቢኖሩም ተጫዋቾችን በዚያ ደረጃ እንዲደርሱ አድርጎ አለመስራቱ እና ያንን እንደሚችሉም አለማሳወቁ ነው ትልቁ ችግር፡፡ በአገራችን እግርኳስ በጠንካራ መልኩ የሚታይ ግብዓት እየኖረን ነው፤ ገንዘብ ብዙ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ በማይደረግበት ሁኔታ ውስጥ እንኳ አገሮች በአፍሪካና በአለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ተፎካካሪ የሚሆኑበት ጊዜያት አሉ፡፡ በእግርኳሳችን ያለው የገንዘብ ሁኔታ ጠንካራ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ህዝባችን በተለይም ወጣቱ እግርኳስን ይወዳል፡፡ ይህን አይነት ህዝብና አቅም ባለበት አገር ላይ “ብሄራዊ ቡድኑ ከረጅም አመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ አለፈ!’ ተብሎ ይህን ያህል እንደብርቅ መታየት አልነበረበትም፡፡ በየጊዜው የእግርኳስ እድገት ለውጥ ማየት ነበረብን፡፡ ሁሉም ሰው ትኩረቱን ኳሳችን ሊያድግ በሚችልበት አሰራር ላይ ቢያደርግና ቀደም ብዬ በጠቀስኩት መሰረት አዘወትረን <የሚቻል> መሆኑን እየተናገርን፣ ስራውን ደግሞ በሚችሉ ሰዎች እያሰራን ብንሄድ በየጊዜው በአፍሪካና አለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ መሳተፍና ከዚያም የተሻለ ቦታ መገኘት እንችላለን፡፡ በዚህ መልኩ ስለማስብ የመኩራራት ስሜት የሚያድርብኝ ሰው አይደለሁም፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ከተሳተፍን 31 አመታትን አስቆጥረን ነበር፡፡ በ2005 ዓ.ም ግን ለአፍሪካ ዋንጫ አለፍን፤በአለም ዋንጫ ማጣሪያም እስከ መጨረሻው የጥሎ ማለፍ ደረጃ ደረስን ፡፡ ሆኖም ከዚያ ጊዜ በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ እጅጉን ቁልቁል እየተንሸራተተ ወደታች ወርዷል፡፡ ለተሳትፎ ረጅም አመት በወሰደበት፣ በአንጻራዊነት “ውጤት” ባመጣው ቡድን እና ከዚያን ጊዜ በኋላ ባሉት አያሌ ዘመናት የሚጠቀሰው አንተ የመራኸው ቡድን ያስመዘገበው “የተሳታፊነት ስኬት” ነው፡፡ ሁኔታውን በትውልዶች መገጣጠም እንደመጣ አጋጣሚ መመልከት እንችላለን? ወይስ በነዚያ ሁለትና ሶስት አመታት ብቻ የታየ የብሄራዊ ቡድናችን “የከፍታ ጊዜ” ሌላ ምክንያት መጥቀስ ይኖርብናል?
★ እንደዚህ አይነቱን ነገር “አጋጣሚ ነው፤ሳይታሰብ የመጣ ነው፤ ሳይጠበቅ ነው፤…… ” ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የሰሞኑን ሁኔታ እናንሳ፡፡ “ወላይታ ዲቻ ሳይጠበቅ ዛማሌክን አሸነፈ፡፡” ሳይጠበቅ! ምን ማለት ነው <ሳይጠበቅ!>?ይሄ በራሱ ገዳይ አባባል ነው፤ ራሳችንን እንደማንችል አድርጎ እንደ መፈረጅ እቆጥረዋለሁ፡፡ እንዴት ነው <ሳይታሰብ!>? ቡድኑ አስቦበት ውድድር ውስጥ መሳተፍ ጀመረ፡ ወደ ግብጽ ሄደ፤ ስትራቴጂ ቀርጾ ወደ ሜዳ ገባ፤ ከተጋጣሚው ጋር ተፋለመ፤ ያዋጣኛል ብሎ በሄደበት መንገድ ውጤታማ ሆነ፡፡ በቃ ይሄ ሁሉ ታስቦበት የተደረገ ነው፤ ሳይታሰብ የሚደረግ ነገር የለም፡፡ ወላይታ ዲቻም ባጋጣሚ ሳይሆን ሰርቶበት ነው ለዚህ የደረሰው፡፡ ሆኖም ዲቻን እንደነ ዛማሌክ፣ አልሒላል፣ እንደ ናይጄሪያዎቹና ደቡብ አፍሪካዎቹ ክለቦች ታላላቅና ጠንካራ ለማድረግ ያለው አማራጭ ጠንክሮ መስራት ነው፡፡
እኛም ሳናስበው አይደለም ያንን ያደረግነው፡፡ በእኔ ጊዜ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ሳይታሰብ የተገኙና የተሰባሰቡ አልነበሩም፡፡ ለረጅም ጊዜ አብረው የቆዩና የሴካፋ ዋንጫ ስናነሳ የነበሩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ እኔ ራሴ ኢትዮጵያ ሶስት የሴካፋ ዋንጫዎችን ስታሸንፍ በስልጠናው ላይ ነበርኩ፤ ሁለቱን በምክትልነት አንዱን ደግሞ በዋና አሰልጣኝነት፡፡ ስለዚህ አሰልጣኞችም ሆነን ተጫዋቾች ልምዳችንን እያዳበርን፣ የተሻለ መግባባት እየፈጠርንና ‘ለምንድነው የማናልፈው?’ የሚለው ቁጭት እየቆረቆረን አብረን የሰነበትን ነበርን፡፡ ይህ በመሆኑም ተጫዋቾች አዕምሮ እና ስነልቦና ላይ መሰራት ነበረበት፡፡ ተጫዋቾቻችን በችሎታ ከማንም እንደማያንሱ አምነን ጠንካራ ስራ ለመስራት ተነጋገርን፤ በዲሲፕሊን መመራት እንዳለብን ተማመንን፡፡ ሁሉም እንደ አንድ እንዲንቀሳቀስ አደረግን፤ የራሳችንን መተዳደሪያ ደንብና መመሪያ አወጣን፤ ከዚያ ዝንፍ የሚለውን መቅጣት ጀመርን፡፡ በዚህ አካሄድ እኔ ያባረርኩትን ሰው ማንም አይመልሰውም ነበር፡፡ በዚህ አረዳድ ስራችንን በተለይም ደግሞ የአካል ብቃት ላይ አጠንክረን ሰራን፡፡ እነዚህን ተጫዋቾች የደረሱበት ደረጃና እድሜያቸው ስለማይፈቅድ ስለቅብብሎችና ቅብብሎችን ስለሚቆጣጠሩበት ቴክኒካዊ ስልት ልታስተምር አትችልም፡፡ አዕምሮአዊና አካላዊ ጥንካሬ ካለ፣ በመካከላቸው ያለው መግባባት ጥሩ ፈር ከያዘ፣ እኔ የምነግራቸውን በተግባር የሚተረጉሙ ከሆነ፣ እኔም ተጫዋቾች የሚሉኝን ለማዳመጥ ከተዘጋጀሁና አጠቃላይ መልካም የሚባል የቡድን መንፈስ ከተፈጠረ ውጤት የማይመጣበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡ በዚህ መልኩ አቅደን፣ ለፍተንና ታግለን እንጂ እንዲሁ በአጋጣሚ የመጣ ውጤት አይደለም፡፡ ጠንክሮ ከተሰራ ሁልጊዜም ቢሆን ስኬት ሊገኝ የሚችል ነገር ነው፡፡ ስለዚህ <ባጋጣሚ የመጣ ውጤት> የሚባል ነገር የለም፡፡
ታዲያ ተደክሞበት የመጣውን የውጤታማነት ጅማሮ ሒደቱን ለማስቀጠል ያልተቻለባቸው ምክንያቶች ምንድናቸው?
★ በመጀመሪያ ያ ውጤት እንዴት እንደመጣ ቁጭ ተብሎ መነጋገርና ማጥናት ያስፈልግ ነበር፡፡ በውይይት መልክ “ምን ተሰርቶ ነው እዚህ ጋር የደረስነው? በምን አይነት አሰራርስ ነው ይህን ያመጣችሁት?” ተብሎ ሊጠየቅ ይገባ ነበር፡፡ ሆኖም ይህን ከማድረግ ይልቅ “ብሄራዊ ቡድናችን እዚህ ከደረሰ- ነገማ አለም ዋንጫ ይገባል፡፡” ተብሎ አሰልጣኝ ማባረርና ቡድን ማፈራረስ ተጀመረ፡፡ ያ የእኛ ቡድን “ፍጹም የተዋጣለት ነበረ፡፡” ማለት እኮ አይደለም፡፡ ጉድለትና ብዙ ክፍተቶች ነበሩበት፡፡ ችግሮቹ የመጡባቸውን ምክንያቶች አጢኖ ማጽዳት፣ መፍትሄዎችን እየፈለጉ ደካማ ጎኖችን ማሻሻልና ወደ ስራ መግባት፣ በውድድሮች ላይ የሚታዩትን ጠንካራ ጎኖች ይበልጥ እያሳደጉ መሄድ፣…….እንደዚህ ማድረግ ሲገባን ሳንወያይ፣ እንከኖቻችን እና ጥንካሬያችን ምን እንደሆነ ሳይታወቅ “ሪፖርት አቅርብ፡፡” ተብዬ ተባረርኩ፡፡ ውጤታማነቱ ያልቀጠለበት ትልቁ ችግር በዚህ ምክንያት የመጣ ነው፡፡ በኋላም ቡድኑ ፈረሰና ልጆቹ ተበተኑ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚመረጡ ተጫዋቾች የብሄራዊ ቡድኑን ከባቢ በተለየ መልክ ይመለከቱታል፤ ሁሉም ነገር አዲስ የሚሆንባቸውን ልጆች ይዘህ ውጤታማ ልትሆን አትችልም፡፡ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ አዳዲስ የሆኑትን ልጆች በነባሮቹ ውስጥ እየቀላቀልክ እና እያላመድክ እንዲሁም የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው እያደረክ ስትሄድ ነው የተሻለ ውህደት ልትፈጥር የምትችለው፡፡ በእኛ ጊዜ ግን የተደረገው ይህ አልነበረም፡፡ ችግሩን ቀርፎ በጎውን ነገር ማስቀጠል ሲገባ ጭራሽ የነበረውን ደህና ትስስር ቆረጡት፤ ግንኙነቶችን በሙሉ አጠፉና አሁን ያለው ነገር ተከሰተ፡፡ ይሄ ነው የሆነው ነገር፡፡
በአገሪቱ የተጫዋቾች አንጻራዊ የብቃት ደረጃ ጫፍ ላይ የደረሱትን ተጫዋቾችን ይዞ እንደ ቡድን በአንድ ለማዋቀርና የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሄድክበት መንገድ ምን ያህል አስቸጋሪ ነበር?
★ <የብቃታቸው ጫፍ ላይ የደረሱ> የሚባል ነገር የለም፡፡ እግርኳስ የቡድን ስራ (Collective Work) ነው፡፡ በእርግጥ በክፍፍል እንደየደረጃው የግለሰብ ሚና (individual Role)፣ የተወሰኑ ተጫዋቾች ስብስብ ሀላፊነት (Group Responsibility) እና የቡድን ውህደት(Team Coherence) ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል፡፡ እግርኳስ ግለሰቦች አንድ ላይ በመሰብሰብ እንደ አንድ ሆነው የሚሰሩት ስራ ነው፡፡ አንዱ ጋር ያለው ሌላው ዘንድ የለም፡፡ ሁሌም የተዋጣለት እና ተበጅቶ የበቃ ተጫዋች ወይም ቡድን ስለማይገኝ የማጣጣም ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሒደት ተስማሚ የሆኑ ጥምረቶችን (Proper Partnerships) ለመፍጠር መጣርንም ያሻል፡፡ በተለያዩ የሜዳ ክፍሎች የሚገናኙና የሚጣጣሙ አንድነቶችን መፍጠር ይኖርብሀል፡፡ ለምሳሌ በቡድንህ በጣም ፈጣን የሆነ የፊት መስመር ተሰላፊ ተጫዋች ካለ በረጅሙ የኳስ ቅብብሎችን በትክክለኛ ምጣኔና በአጥቂው ፍጥነት ልክ የሚፈጽምለት ሌላ ተጫዋች ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህ ተጫዋች ተገቢውን አጣማሪ ትመርጥና የውህደት ቅንጅት እንዲኖራቸው ታደርጋለህ፡፡ ብዙም የመሮጥ ፍላጎት የሌላቸው፣ አጫጭር የሚባሉ የኳስ ቅብብሎችን የሚመርጡና ቴክኒካዊ ችሎታቸው ጥሩ የሆኑትን አይተህም እንዲሁ በክህሎታቸው መሰረት ምርጡን እንዲያበረክቱ የተለያዩ ስራዎችን ትሰራለህ፡፡ በአንድ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾችን በሙሉ ሁሉም ብቁ፣ ሁሉም የተዋጣላቸው ናቸው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ እያንዳንዱ ተጫዋች የራሱ የሆነ ግላዊ ችሎታ አለው፤ አሰልጣኙ የሚሰራው ያን የተናጠል አቅም በጥሩ ሁኔታ ለቡድን ሊውል የሚችልበትን መንገድ የሚያስገኘውን ውህደትና ጥምረት መፍጠር ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ቡድን ውስጥ ሁሉም እኩልና የተዋጣለት ሊሆን አይችልም፡፡
ከዚህ ቀደም በአሰልጣኞች ገፅ ላይ የወጡ ጽሁፎችን ሊንኩን ተጭነው ያገኛሉ፡፡ LINK
በጊዜው ብሄራዊ ቡድኑ በጣም ጠንካራ የሚባል የማሸነፍ ስነ ልቦና ነበረው፡፡ በሜዳውና ከሜዳው ውጪ ትልልቅም ይሁን ተመጣጣኝ ተጋጣሚዎችን ሲያገኝ ጨዋታዎችን እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ታግሎ ለማሸነፍ የሚያሳየው ተነሳሽነትና የማሸነፍ ፍላጎት ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህን ስሜት በተጫዋቾቹ ላይ ለማስረጽ ምን ያህል ፈታኝ ነበር?
★ እነዚህ ነገሮች በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ የሚወሰኑ ነበሩ፡፡ ሲጀመር ተጫዋቾቹ በራሳቸው በተለያዩ ፍልስፍናዎች የተያዙ ናቸው፡፡ ግማሹ “ሩጫ አያስፈልግም፡፡” ባይ ነው፤ ሌላው ደግሞ “የአካል ብቃት ስራ ምን ያደርጋል?ሳንደክም ነው መጫወት ያለብን፡፡” ይላል፡፡ “ሮጠንና ለፍተን ካልተጫወትን ምንም ውጤት ልናመጣ አንችልም፡፡” የሚልም አካል አለ፡፡
እንደዚህ የተወሳሰበና በተለያዩ አስተሳሰቦች የተወጣጠረ የተጫዋቾች ስብስብ ነው የሚኖርህ፡፡ እንግዲህ ይህንን ወደ አንድ ለማምጣት መነጋገር እና መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ቡድኑ ወደ አንድ አመለካከት ካልመጣ ውጤታማ ልትሆን አትችልም፡፡ እኔ ስሮጥ አንተ የምትቆም ከሆነ ችግር ነው፤ እንደ ቡድን ሁለታችንም አብረን መሮጥ አልያም መቆም ነው ያለብን፡፡ ሁለታችንም አብረን ጠንካራ መሆን ይኖርብናል፤ አለበለዚያ እኔ ጠንክሬ አንተን እየጎተትኩ አይሆንም፡፡ ሁለታችንም በጥንካሬያችን መጓዝ ይጠበቅብብናል፡፡ በእግርኳስ እያንዳንዱ ተጫዋች ሜዳ ላይ በሚጫወትበት ቦታ በአግባቡ እንዲወጣ የሚሰጠው የራሱ የሆነ ሀላፊነት አለው፤ የቡድን አጋሩም እንዲሁ፡፡ ለምሳሌ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ሁለቱም በተመሳሳይ ጊዜ በግራ ወይም በቀኝ አይቆሙም፤ በግራና በቀኝ እንጂ፡፡ የመስመር ተከላካዮችንም ብናንሳ አንዱ የአንዱ ቦታ ላይ ሄዶ አይደረብም፡፡ ስለዚህ ተጫዋቾች በሚጫወቱበት ቦታ የተሰጣቸውን ሐላፊነት በብቃት መወጣት አለባቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች ወደ አንድ ለማምጣት ቡድኑ በሚታይበት ክፍተት ላይ ጠንክሮ መስራት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የቡድን አንድነት የሚመጣው ደግሞ በአእምሮ ስራ ብቻ አይደለም፡፡ የአካል ብቃት፣ ቴክኒክና ታክቲክ ላይም አንድነት መፍጠር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ታክቲክ ራሱን የቻለ መርህ አለው፡፡ እነዚህን መርሆዎች አስተምረህ በሜዳ ላይ እንዲተገብሩ ማድረግ፣ ተጫዋቾቹ መርሆዎቹን አውቀዋቸውና ተግባራዊ አድርገዋቸው የሚፈጠሩት ስህተቶች ላይ ደግሞ ማስተካከያዎችን እየወሰድክ መሄድ ግድ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ “ቡድኑ ታክቲክ የለውም!” የሚል አስተያየትን እሰማለሁ፡፡ ያ ሰው “ታክቲክ ምንድን ነው?” ተብሎ ቢጠየቅ የሚመልሰውን መልስ አላውቅም፡፡ የእግርኳስ መሰረታውያን (Fundamentals of Football) የሚባሉትን የአካል ብቃት፣ ቴክኒክና ታክቲክ ከስነልቦናና የአመጋገብ ስርዓት ጋር በማጣመር ስታሰራ ነው የአሸናፊነትን መንፈስ መገንባት የሚቻለው፡፡ አለበለዚያ አንድ ቁንጽል ቃል ይዞ “ይሄ አልሆነም!” ብሎ ሰውን መፈረጅ፣ መወንጀል ወይም መተቸት በጣም አስቸጋሪ ነው ፡፡
በ2005ቱ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ አብዛኛዎቹ የመጀመሪያ ተሰላፊዎች በተለይ በማጣሪያ ጨዋታዎች በቦታቸው የተሻለ ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ አጥቂው መስመር ደግሞ ይበልጡን ጥሩ ሆኖ ታይቷል፡፡ 4-4-2ን ያዘወተርከው በየጨዋታው ሁለቱን የጊዜው ምርጥ አጥቂዎች ለመጠቀም ነው? ወይስ በክለቦች አሰልጣኝነት ጊዜህም የምትመርጠው ፎርሜሽን ነበር?
★ እንደሱ አይደለም፡፡ በመጨረሻው የማጥቃት ክልል (Attacking Third) ላይ የሚገኙት የፊት መስመር ተሰላፊዎች እና ከሜዳው ወገብ በላይ ያሉት አማካዮች በሙሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች እንዲሆኑ ስለምፈልግ ነው፡፡ ለምሳሌ አዳነ ግርማ የወጣለት አጥቂ ነው፡፡ እኔ አዳነን ከመስመር እየተነሳ እንዲያጠቃ በክንፍ/መስመር አማካይኝነት የማሰልፍበት ወቅት ነበር፡፡ በመሀል አማካኝነትም ተጠቅሜበታለሁ፡፡ ጌታነህንና ሳላአዲንን ፊት ላይ ካሰለፍኩ በሁለቱ አጥቂዎች ግራና ቀኝ እንዲሁም ከጀርባቸው የማሰልፋቸው ተጫዋቾች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ነበሩ፡፡ ከማጥቃት ባለፈም እንዲከላከሉ አደርግ ነበር፡፡ ስለዚህ በሁለት አጥቂ ብቻ አልነበረም ስጠቀም የነበረው፡፡ ተፈጥሮአዊ የማጥቃት ችሎታ ያላቸውን ተጫዋቾች የተለያዩ ቦታዎች ላይ በማድረግ እጠቀምባቸው ነበር፡፡ ይህን ሳደርግ ግን “እኔ አጥቂ ነኝ፤ ወደኋላ እየተመለስኩ የመከላከል ስራን አልሰራም፡፡” የሚለውን በአዕምሮ ውስጥ የተቀመጠ መጥፎ አመለካከታቸውን በመጀመሪያ ከተጫዋቾቹ አስወግጄ ነው፡፡ “አጥቂ በመሆኔ ክንፍ ላይ የምጫወተው ለምንድነው?” የሚል አስተሳሰብ አግባብነት የለውም፡፡ የመስመር ጨዋታ እኮ የመከላከልና የማጥቃት ሒደት የሚታይበት ነው፡፡ እግርኳስ ደግሞ በጠቅላላው የመከላከል እና የማጥቃት ተግባር ነው፡፡ የጨዋታ መርሁም (Principle of the Game) ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ <ኳስ ስትይዝ አጥቃ፤ኳስ ስታጣ ደግሞ ተከላከል፡፡> ነው የሚለው፡፡
በማጥቃት ሒደት ኳስን የያዘው ተጫዋች ብቻ አይደለም የሚያጠቃው፤ ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች የማጥቃት ተግባር እንዲያከናውን ቡድኑ ባጠቃላይ የማጥቃት ሒደቱ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ በመከላከል ሒደት ደግሞ ተጫዋቾች በሙሉ ተከላካይ ይሆናሉ፡፡ መከላከልን መጀመር ያለብህም ኳሱን ካጣህበት አካባቢ ነው፡፡ ለምሳሌ አጥቂ ሆነህ በተጋጣሚህ ላይ የጎል ሙከራ ካደረግክ በኋላ ተከላካዩ ኳሱን ሲጀምር አንተ የመጀመሪያው ተከላካይ (Immediate Defender) ትሆናለህ፡፡ አበባውና ስዩም ከኋላ እየተነሱ ጎሎችን ያገቡ ነበር፡፡ “የመስመር ተከላካይ ነኝና ከተከላከልኩና ኳስን ወደፊት ከላኩኝ በቂ ነው፡፡” አላሉም፡፡ ይህንን በቲዎሪና በልምምድ በሚገባ ተማምረንና አስረግጠን ተነጋግረን ነው የሰራነው፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የማሸነፍን ጥንካሬ በአዕምሮአቸው ውስጥ ያስቀመጡት፡፡ እንዲሁ በወሬ ሳይሆን ጠንክረን ሰርተን ነው ያ ውጤት የመጣው፡፡
ከብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በኋላ ወደ ክለብ አሰልጣኝነት ያልተመለስክበት ምክንያት ምንድን ነው?
★ ባጭሩ ለመመለስ በቅቶኝ! ነው፡፡ ብዙ አመታት አሰለጠንኩ፤ ሰላሳ አንድ አመታት አካባቢ በዚህ ሙያ ውስጥ ቆየሁ፡፡ ለነዚህ ሁሉ ጊዜያት ያሰለጠንኩበት ምክንያት ውስጤ አንድ አላማ ስለነበረ ነው፡፡ በወጣትነቴ በመምህራን ማሰልጠኛ እያለሁኝ በመብራት ሐይል የC ቡድን ውስጥ እጫወት ነበር፡፡ በወቅቱ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የመሆን ፍላጎቴ ከፍተኛ ነበር፡፡ ነገርግን አስተማሪ ሆኜ ሰቆጣ ሄድኩኝ፡፡ አመቺ የሆነ አከባቢ ባለመሆኑና የመታየት እድል ስለማይኖርህ ለመመረጥ አትችልም፡፡ እንዲሁ ዝም ብለህ የአስተማሪዎችና የተማሪዎች ቡድን በማቋቋም እዚያው እየተጫወትክ ትኖራለህ፡፡ስለዚህም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጫወቱ ጉዳይ ህልም ሆኖ ቀረ፡፡ የአሰልጣኝነት ሙያውን ስጀምር በብሄራዊ ቡድን የመጫወት አላማዬ ስላልተሳካልኝ ‘ለምን አሰልጣኝ ሆኜ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን አላሰለጥንም?’ ከሚል የረጅም ጊዜ እቅድ ነው፡፡ እኔ አዲስ አበባ አድጌ በመምህርነት ወደ ወሎ-ሰቆጣ ከዚያም ወደ ጎጃም-ባህርዳር ነው የተዛወርኩት፡፡ በ1972 ዓ.ም መጨረሻ ወደ አዲስ አበባ መድሀኒአለም ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መጣሁ፡፡ በወቅቱ ከሰቆጣ ተነስተህ፣ በትልቅ ክለብ ሳትጫወትና የአገሬው ሰው ሳያውቅህ “የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን ማሰልጠን አለብኝ፡፡” ብለህ ማሰብ የማበድ ያህል ይቆጠር ነበር፡፡ ምን ማድረግ ነበረብኝ? በዋነኝነት የእግርኳስ ትምህርት መማር፡፡ መሰረታዊውን ነገር አውቀው ነበር፡፡ የዋና ከተማዋ ሰው በእግርኳስ ባያውቀኝ በአስተማሪነት ህይወቴ የቆየሁባቸው የወሎና የጎጃም ህዝብ ግን በጥሩ እግርኳስ ተጫዋችነቴ ያውቀኛል፡፡ ስለዚህ ለማሳያ ወይም ለማስጀመሪያ (Demonstration) ሊሆን የሚችል እውቀት አሰባስቤ ነበር፡፡ ቀጥሎ ሳይንሱን መማር ነበር፡፡ እሱን ለመማር ደግሞ አላቃተኝም፤ ተማርኩ፡፡ ጀርመን ሁለት ጊዜ፣ ግብጽ እና ኬንያ ሄጄ የአሰልጣኝነት ትምህርቶችን ቀሰምኩ፡፡ የፊፋና የካፍ የአሰልጣኝነት የተለያዩ ደረጃ ያላቸውን ኮርሶች ወሰድኩ፤ አሁንም የካፍ ኢንስትራክተር ነኝ፡፡ በቅርቡም የመጨረሻውን ደረጃ Pro Licence ወስጃለሁ፡፡ ያን እውቀት አዳብሬ እዚህ ደረጃ ደረስኩ፡፡ ታዲያ እዚህ ለመድረስ የተጋፈጥኩት ፈተና ከባድ ነበር፡፡ “ይሄ ደግሞ ከየት ነው የመጣው? ለመሆኑ ኳስ በእግሩ ነክቶ ያውቃል?” ተብለህ ይፌዝብሀል፡፡ ሳይንሳዊ እውቀት ካለህ ኳስ ነክተህ ባታውቅስ? አሰልጣኝ እኮ የግድ ኳስ እየመታ በተግባር ማሳየት ላይኖርበት ይችላል፡፡ የሚችለውን ሰው አምጥተህ “ና! እንዲህ አድርግ፡፡” ማለት ነው፡፡ ሆኖም ያ ሁሉ ከፍተኛ ፈተና በህይወቴ ሲመጣ በአዕምሮዬ የነበረው ጥንካሬ እስከመጨረሻው ድረስ በጽናት ለአላማዬ እንድታገልና ለምፈልገው ደረጃ እንድበቃ አደረገኝ፡፡ ሰላሳ አንድ አመት ከሰራውና የምፈልገውን ካሳካው በኋላ ‘በቃኝ!’ አልኩ፡፡ በአለም ዋንጫ ለመሳተፍ ጥቂት የቀረውም ቡድን ለቴሌቪዥን የማስታወቂያ ገቢ ሲባል ከኢትዮጵያ ይልቅ ናይጄሪያ እንዲያልፍ ተፈለጎ በውድድሩ እንዳንሳተፍ በአድልዎ ያገባነውን ጎል ሽረው፤ ተገቢ ያልሆነ ፍጹም ቅጣት ምት ተሰጥቶብን (በደርሶ መልስ ከገቡብን ጎሎች ሶስቱ ከፍ.ቅ.ም. የተገኙ ነበሩ፡፡) ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ እንጂ ናይጄሪያዎች በልጠውን አልነበረም የተሸነፍነው፡፡ ይህንን ካሳካው በኋላ ፊቴን ወደ ታዳጊዎች አዙሬ ያቅሜንና የምችለውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እየሰራው ነው፡፡ በእርግጥ ያልጠየቀኝ ክለብ የለም፡፡ አሁን እየተከፈለ የሚገኘውን በሚሊዮኖች የሚቆጠረውን ብርም አፈፍ አደርገው ነበር ( ሳቅ ብሎ…..)፡፡
ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፈው ቡድን በፊት በነበሩት ጊዜያት ብሄራዊ ቡድኑን አሰልጥነሀል፡፡ በተለይ ደግሞ በ1990ዎቹ አጋማሽ ቡድኑ በሴካፋ ዋንጫዎች ደጋግሞ ባለድል በሆነባቸው ወቅቶች የነበረው ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ቢያልፍ ኖሮ ይሄን ውሳኔህን ተግባራዊ ታደርገው ነበር?
★ እኔ አሁንም ቢሆን ብሄራዊ ቡድን ማሰልጠን አቅቶኝ አይደለም፡፡ እንዲያውም አሁን የበለጠ ባለ ልምድ በመሆኔ ሚስጥሮቹን አውቄያቸዋለሁ፡፡ አንድን ቡድን ውጤት አስገኝተህ ማቆም በቂ ሊሆን አይችልም፡፡ አንጻራዊ ውጤታማነት ስላሳየሁ አይደለም እኔ ያቆምኩት፡፡ የምትሰራበት ከባቢና የሚያሰሩህ ነገሮች ጥሩ አይደሉም፡፡ እንደ ባለሙያ ከሚያውቅ ሰው ጋር ነው ልትነጋገር የምትችለው፤ ከማያውቅ ጋርማ እንዴት ልትግባባ ትችላለህ? የምትነግረው ነገር የሚገባው ሰው ስታገኝ ለስራህ የተሻለ ድባብ ይፈጥርልሀል፡፡ ከሴካፋ ዋንጫዎች በተጨማሪ በታዳጊ ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር አራተኛ የወጣውን ቡድን አሰልጥኛለሁ፡፡ ያኔም እኛ ስም ስለሌለን ለአለም ዋንጫ እንዳናልፍ ከፍተኛ ግፍ ተፈጽሞብን ግብጽና ጋና እንዲያልፉ ተፈልጎ እኛ ከውድድሩ ወጣን፡፡ በ1998ዓ.ም የሴካፋን ዋንጫ ካመጣን በኋላ ወዲያውኑ ዶ/ር አሸብር ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ሀላፊነት ሰጥተውኝ ነበር፡፡ ለውድድሩ ማለፍም እንችል ነበር፡፡ እዚህ በምድቡ ጠንካራ የነበረችውን ሊቢያን አሸነፍን፡፡ በምን ምክንያት እንደሆነ ሳላውቅ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥመኝ የስራ መልቀቂያ አቅርቤ ወደ የመን ሄድኩ፡፡ ከለቀኩ በኋላ ኢትዮጵያ በምድቡ በምትገኘውና በእግርኳስ ታሪኳ ከዛ ቀደም ተጋጣሚ አገራትን አሸንፋ በማታውቀው ሌላኛዋ ቡድን ናሚቢያ ተሸነፈች፡፡ ያ ቡድን ነበር ለአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፈው፡፡ ያኔ እኛ ናሚቢያን አሸንፈን ሌሎቹን ቀሪ ሁለት የሜዳችን ጨዋታዎች ድል ብናደርግ እናልፍ ነበር፡፡ ያ ቢሳካ ደግሞ በውድድሩ ተሳትፎ መደጋገማችን አይቀርም ነበር፡፡ የተሳትፎ ልምዱን እያዳበርን የመሄድ ተመክሮም እንፈጥር ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ሰው ራስ ወዳድ ነው፡፡ እኔ ውጤታማ ስሆን አንተም ያን ውጤት ትመኘዋለህ፡፡ ስለዚህ በሚያስኬደው መንገድ ተጉዘህ እኔን ጠልፈህ የማስወጣት ስራ ትሰራለህ፡፡ እዚህ አገር ላይ ይህን መሰል ነገሮች ናቸው ያሉት፡፡ ውስጥ ውስጡን ሀይለኛ ሽኩቻ ስላለ ስኬታማነትህ በቀና አይታይልህም፡፡ “እሱ ከየትም መጥቶ አሰልጣኝ ሆኖ ለአፍሪካ ዋንጫ ሊያልፍ ነው፡፡” ስንቱ ለረጅም ጊዜ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ተጫውቶ፣ልምድና ስም አትርፎ፣ ክብር ያለውና በየቦታው የሚጨበጨብለት ያላሳካውን እኔ ሳሳካው ችግር ይፈጥራል፡፡ የሀሜት ንግግሮችና ጩኸቱ ይበረክታል፡፡ ጫጫታና ስድቡ ይበዛል፡፡ “አይችልም እኮ!” መባል ይጀመራል፡፡ <አለመቻል> ማለት ምን ማለት ነው? እኔ ሲቪዬን ማሳየት እችላለሁ፡፡ ጀርመንም ስማር አንደኛ ነው የወጣሁት-ሽልማትና የምስክር ወረቀት አለኝ፡፡ ብቁ(Qualified ) ነኝ፡፡ በቀለም ትምህርትም (Academically) ቢሆን ባቅሜ ተምሬያለሁ፡፡ ምኑ ላይ ነው ታዲያ የማልችለው? እንዲህ አይነቱ አስተያየት እንድትበሳጭ ያደርጋል፡፡
ሌላው የወቀሳ አይነት ደግሞ “የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአለም ዋንጫ አላለፈችም፡፡” የሚል ነው፡፡ ሌላ ጫጫታ ” በእግርኳስ ትልቅ አገር መሆን የምትችለውን……!” የት የምታውቀውን የአለም ዋንጫ!!! ከዛ በኋላ አስወጡኝ፡፡ በስብሰባቸው ላይ እንኳ አይጠሩኝም፤ ያለህን እንድታካፍልም እድል አይሰጡህም፡፡ እንዲህ አይነቱ አመራር ባለበት መስራቱ አያስፈልግም፡፡
ጫናዎቹ ናቸው የገፉህ ማለት ነው?
★ በቃ ጫና አለው፤ በቃኝ፡፡ ለሰላሳ አንድ አመታት ያህል ተጓትቻለሁ፡፡ አሁን እኔ የባንክ እዳ የለብኝ፤ ምን የለብኝ፥ምን የለብኝ፤ ግማሽ እንጀራ መብላት አያቅተኝም፡፡ ያስተማርኩበትና መብራት ሐይል የሰራሁበት ጡረታ አለኝ፡፡ 50 ኪሎ ጤፍ የምትገዛ ብር ስላለችኝና የባለቤቴም ስላለች ሽሮ መብላት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ከማንም ጋር ልጓተት አልችልም፤ በቃ፡፡
አንዳንዶች ግን “ጋሽ ሰውነት በቅርብ አመታት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ታሪክ ትልቅ የሚባል ውጤት ካገኘ በኋላ ወደ ክለብ ተመልሶ ያላሰለጠነው ያንን ስኬት በክለብ አሰልጣኝነቱ ሊያሳይ ወይም ሊደግም ስለማይችል በስጋት ይሆናል፡፡” ብለው ይገምታሉ፡፡ ለዚህ አስተያየት የምትሰጠው ምላሽ ምንድን ነው?
★ በእዚህ አገር እግርኳስ ክለብ ላይ ስኬታማ ልትሆን አትችልም፡፤ አዛዡ ብዙ ነው፡፡ በክለቦች ከቴክኒክ ኮሚቴው አወቃቀር ጀምሮ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ የአሁኑን ጊዜ አላውቅም እንጂ በድሮው ዘመን በተለይም በ80ዎቹና በ90ዎቹ የመጀመሪያ አመታት የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሚሆነው ስለ እግርኳስ ምንም አይነት ግንዛቤ የሌለው የጋራዥ ክፍል ሀላፊው ነው፡፡ ከእሱ ጋር በምን መልኩ ነው የምትጣጣመው? ወንድሙን እንድትቀጥርለትና እንድታሰልፍለት ይፈልጋል፡፡ በዘመዳዘመድ ግንኙነቶች ላይ የተመሰረተ ቡድን እንድትገነባለት ይጠብቃል፡፡ ከዚህ አንጻር አንተ የተማርከውና ሳይንሱ የሚለው ሌላ ነው፡፡ አቋምህን እንድትሸረሽር ያደርጋል፤ ፍርሃት ካለብህ “እሺ!” ትልና ወንድሙን ታስገባለታለህ፡፡ ፍርሀት ከሌለብህ ግን እምቢ ትልና በአቋም ስትጸና “ትዕዛዜን አይቀበልም፡፡” ብሎ ይከስህና ትባረራለህ፡፡ በእርግጥ እኔ በክለብ አሰልጣኝነት ውጤታማም አልነበርኩም ፡፡ ኑሮዬን መኖር፣ልጆቼን ማስተማርና የባንክ እዳዬን መክፈል ስለነበረብኝ ተወዳድሬ ላይ ያሉትን እንደ ጊዮርጊስና ቡና ያሉ ቡድኖችን አላሰለጠንኩም፡፡ ብዙውን ጊዜ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ነው የምገባው፡፡ በአሰልጣኝነት መስፈርቶች በጊዜው ከነበሩት አሰልጣኞች አላንስም፡፡ ነገር ግን በመታወቅ (Popularity) እና ኳስን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በመጫወት የሚወራው ወሬ አያግዘኝም፡፡ “እሱ እኮ ተጫውቶ አያውቅም፡፡” የሚለው አስተያየት ዋጋ ይሰጠው ነበር፤ ተቀባይነትም ነበረው፡፡ ቀረብ ብሎ አንተነትህን ከሚመረምር፣ ከሚጠጋህና ከሚያውቅህ ይልቅ በወሬ ደረጃ የሚሰማው ያሸንፈውና አንተን ምንም እንደማታውቅ አድርጎ ይፈርጅሀል፡፡ እኔ በእነዚህ ነገሮች ተጽእኖ ስለነበረብኝ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን እየወረድኩ አሰለጥናለሁ፡፡ ደመወዜን እላይ ካሉት አሰልጣኞች እኩል አደርግና ታችኛው ዲቪዚዮን ውስጥ ባሉ ክለቦች ውስጥ እገባለሁ፡፡ ብዙ ክለቦችን ወደ ላይኛው ሊግ አሳድጌያለሁ፡፡ በላይኛው ሊግ በማሰለጥን ጊዜ ግን ክለቦች ይወርዳሉ፡፡ የተለያዩ ምክንያቶችን መግለጽ እችላለሁ፡፡ የመጀመሪያው፡- ክለቦቹን የምረከበው ግማሽ አመት ላይ ስለሆነ፣ ሁለተኛው ደግሞ ውድድር ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን የምረከበው ቡድን ውስጥ የነበሩ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ለቀው ተመርጦ ያለቀና ለመፎካከር ብቁ ያልሆነ ቡድን ውስጥ ገብቼ ስለምሰራና ያ ቡድን ከሌሎቹ አንጻር መወዳደር ሳይችል ሲቀር ይወርዳል፡፡ ከዛም “ሰውነት ቡድን ያወርዳል፡፡” ተብሎ መነገር ይጀመራል፡፡ የወረዱት ቡድኖቹ እንጂ እኔ አይደለሁም፤ እኔማ ብቃቱ አለኝ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሰልጥኖ ዋንጫ ያላመጣ አሰልጣኝ የለም፡፡ እኔም ቅዱስ ጊዮርጊስን ብይዝ ከረባቴን አስሬ ዋንጫ አመጣለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁሌም በቡድኑ ውስጥ የምታገኘው ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾችን ነው፡፡ እኔ የምረከበው ቡድን ግን የወረደና የፈረሰ ቡድን ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ቡድኖች ውስጥ የምገባው ለመኖር (survive ለማድረግ)፣ ለማወቅ፣ ለመማር፣ ሙያዬን ለማዳበርና ለማሻሻል ነው፡፡ በክለብ ውጤታማ የምትሆነው ብዙ ድጋፎቾን ስታገኝ ነው፡፡ በተረፈ ግን አሰልጣኝ ሆነህ በእርግጠኝነት ውጤት አመጣበታለው ብለህ የምትገባበት ዋስትና የለህም፡፡ ብሄራዊ ቡድን ግን የአገር ሐላፊነት ነው፡፡ከክለብ አሰራር በተለየ ነው የምትጓዘው፡፡
ለብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት “ሰውነት ይመለስ!” ሲባል ምን አይነት ስሜት ይሰማሀል?” “ይመለስ!” ለሚሉት ወገኖችስ ምን የምትላቸው ነገር አለ?
★ ለእኔ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን ከማሰልጠን የበለጠ የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ ሆኖም አሁን ያሉትን ወጣቶች ይዘህ ውጤታማ ለማድረግ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ወጣቶቹ ኳስ ይችላሉ፤ ሆኖም ይህን የወጣት ስብስብ ስኬታማ ለማድረግ በየትኛውም መንገድ አንድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ብሆን ባንድ ጊዜ ውጤት ማምጣት አልችልም፡፡ ተጫዋቾቹ እኔ በምፈልገው ደረጃ መገኘት መቻል አለባቸው፡፡ ይህን ለማድረግ ልጆቹ ይዘውት የሚመጡትን ለእኔ አመቺ ያልሆነም ነገር ማስቆምና የእኔን ፍልስፍና ብቻ ይዘው እንዲሄዱ ማድረግ አለብኝ፡፡ እንደ እድልሆኖ የማምንበት ጥሩ ነገር ካላቸውና እሱን ማስቀጠል ካለብኝም በእነሱ መንገድ እጓዛለሁ፡፡ የተለያዩ መሸጋሽጎችና ለውጦች ለመፍጠር ጠንክሮ መስራትና ተጫዋቾችን ማሳመን ስለሚጠይቅ ብዙ ጊዜ ይወስዳል፡፡ በመሀል ደግሞ ብዙ ውድድሮች አሉ፡፡ በነዚህ ሁሉ መሀል ሽንፈት ከገጠመህ “ይኸው አይችልም እኮ!” ሊመጣ ነው፡፡ ያ የ2005ቱም ቡድን ቢሆን ጊዜ ነበረው፡፡ ተጫዋቾቹ ከሁለት አመት ተኩል በላይ በትውውቅ አሳልፈዋል፡፡ ከዚያ በፊትም ቢሆን ከሴካፋ ውድድሮች ጊዜ ጀምሮ በብሔራዊ ቡድኑ የቆዩ ተጫዋቾችም ነበሩ፡፡ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ስረከብ በመጀመሪያው ቀን የተናገርኩት ‘ልጆች ከእናንተ ውስጥ የሴካፋን ዋንጫ አብረን ያነሳን አለን፤ አሁን የተሰጠን ከዛ ከፍ ያለ ሀላፊነት ነው- ለአፍሪካ ዋንጫና ለአለም ዋንጫ ማለፍ! (በእርግጥ ለአለም ዋንጫው ውድድር ማለፍ የተሰጠን ሐላፊነት ሳይሆን እኛ እራሳችን የጨመርነው ነበር፡፡) ‘ይሄን ሐላፊነት ለመወጣትና ቀድሞ የነበሩብንን ችግሮች ለመቅረፍ የምንሰራ ከሆነ አብረን እንዘልቃለን፡፡ እኔ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ እፈልጋለሁ፡፡ እናንተም ማለፍ ትፈልጋላችሁ፡፡ ስለዚህ ጠንክረን የምንሰራና ለተሻለ ትግል የተዘጋጀን ከሆነ አብረን እንሁን፡፡ በጊዜ ሒደት የማያስማሙ ችግሮች ሲፈጠሩ ተማምነን የምንሻሻል ከሆነና ተጨማሪ እክሎች ላለማምጣት ራሳችንን የምናስገዛ ከሆነ አሁኑኑ እንስማማ፤ ሀብታም ተጫዋች ካለም ይውጣልን-እኛ አሸንፈን ገንዘብ የምንፈልግ ደሀዎች ነን- በየጊዜው መሸለም እንፈልጋለን፤ የተሻለ ነገር ካመጣንም መንግስት ቤት፣ መኪናና ገንዘብ ይሸልመን ይሆናል ፤ ሽልማቱ የህይወታችንን መሰረት ሊቀየር ይችላል፤ በዚህ መልኩ የሚያስብ ካለ ከጎኔ ይቁም- በተቃራኒው የሆነ ደግሞ ይውጣልኝ፡፡’ አልኳቸው፡፡ በጥሞና ያዳምጡኝ ነበር፡፡ ቀጠልኩና ‘ካልሆነ ግን እኔም ይቅርብኝ-ሀላፊነቱን አልቀበል፡፡’ አልኳቸው፡፡ ተጫዋቾቹ ደግሞ ራሳቸውን በማስተዳደር በኩል ጎበዞች ነበሩ፡፡ ቤት የሰሩ፣ ከአንድ በላይ ታክሲ ያላቸውና ፎቅ የጀመሩም ነበሩበት፡፡ ከንግግሩ በኋላ ሁሉም “ካንተ ጎን ነን፤ መተዳደሪያ ህግ እናውጣ፡፡”ብለው ህግ አወጡ፡፡ ከዚያ በኋላማ እግዚአብሄርም ረዳንና ሽልማቱ ይመጣ ጀመር፡፡ ተመልከቱ ተጫዋቾቹ ለዲሲፕሊን ተገዢ ሆነው ሲገኙ የማነቃቂያው ሽልማት ደግሞ ይበልጡን አጠናከራቸው፡፡ እራት ሰዓት ላይ አንዲት ሰከንድ አያዛንፉም፡፡ መኝታ ላይ ሶስት ሰዓት መገኘት ነበረባቸው፤ በሰዓቱ አልጋቸው ላይ ታገኛቸዋለህ፡፡ ዲሲፕሊን ለማስከበር እኔ የማላስፈልግበት ደረጃ ተደረሰ፡፡ በዚህ አይነት የመግባባት መጠን ከሰራህ ነው ውጤት ልታመጣ የምትችለው፡፡ የመጀመሪያ ተሰላፊዎች አውጥቼ ስንወያይ እንኳ አንዳንድ ተጫዋቾች “ኮች በዛሬው ጨዋታ እኔ ልረፍና እገሌ ይግባ፡፡”እስከመባባል የደርሱት እግርኳሱ የራሳቸው እንደሆነ እንዲያውቁ ተደርጎ ስለነበር ነው፡፡ ታዲያ ይሄ ሁሉ ስራ ጊዜ ይፈልጋል፡፡
እኔም ቅዱስ ጊዮርጊስን ብይዝ ከረባቴን አስሬ ዋንጫ አመጣለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁሌም በቡድኑ ውስጥ የምታገኘው ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾችን ነው፡፡ እኔ የምረከበው ቡድን ግን የወረደና የፈረሰ ቡድን ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ቡድኖች ውስጥ የምገባው ለመኖር (survive ለማድረግ)፣ ለማወቅ፣ ለመማር፣ ሙያዬን ለማዳበርና ለማሻሻል ነው፡፡
ነጥቦችን መሰብሰብ በሚያስፈልግ ውድድሮች ላይ ያለ ቡድን የማታሰለጥን በመሆንህ ብዙም ጫና የለብህም፡፡ በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆኖ ከመስራት በኋላ ኑሮ እንዴት ነው? ከባለሙያዎች ጋር ያለህ ግንኙነት፣ ከአካባቢህ ሰዎች የሚሰጥህ አስተያየት እና ሌሎችስ እንዴት እየሄዱልህ ነው?
★ አኗኗሬ አልተቀየረም፤ ቤቴም ያችው የድሮ ቤቴ ናት፡፡ ፎቅ አልሰራሁም፤ ይሄ መኪና በስጦታ ተበርክቶልኛል፡፡ ያው ድሮም ቢሆን ቁርስ፣ ምሳና ራት እበላለሁ፡፡ ጾም ሲሆን እጾማለሁ፡፡ ትርፍ የሚባል ገንዘብ አላስቀመጥኩም፤ አሁን ጫና የለብኝም፤ ያኔ ግን የኑሮም የስራም ጫና ነበረብኝ፡፡ አሁን ብሰራም ባልሰራም መኖር እንደምችል አረጋግጫለሁ፡፡ ልጆቼን አስተምሬ የራሳቸውን መስመር ይዘዋል፤ እኔና ባለቤቴ ነን ያለነው፤ እሷም ጡረታ አላት፤ እኔም የጡረታ ገንዘብ አለኝ፤ በቃ እሱን አጋጭተን ሽሮ መብላታችን ተረጋግጧል፡፡ ከእንግዲህ በኋላ ሀብታም ለመሆን አላስብም፡፡ አንዳንዴ እንደማንኛውም አባት የማስበው ልጆቼ ወደፊት ተቸግረው እንዳይኖሩ ነው፡፡ ‘ያለኝን ንብረት ሸጬ ላከፋፍላቸውና የየራሳቸውን ቤት ይኑራቸው?’ ብዬ አስባለሁ፡፡ ደሀ ሆነው እንዲኖሩ አልፈልግምና የማቅደው ለነሱ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ኑሮዬ ሰላማዊ ነው፤ ከባለቤቴ ጋር አርባ አመት አብረን ቆይተናል፤ ምንም ችግር የለብንም፡፡ ከብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት በኋላ ደግሞ የነበረው ሁኔታ የሚገርም ነው፡፡ ሰው ይወደኛል፤ ያከብረኛል፤ በየሄድኩበት ሰላምታውንና ፍቅሩን ይሰጠኛል፤ ሱቆች ስገባ ዋጋውን ቀንሶ ግማሹን ነው የሚያስከፍለኝ፤ በተለያየ መንገድ አድናቆቱን ይቸረኛል፡፡ አሁን እኔም የበለጠ የህብረተሰቡ ተገዢ ሆኛለሁ፤ ህዝብ አላስቀይምም፤ ህብረተሰቡ በሰጠኝ ፍቅርና ክብር ደረቴን የምነፋ ሳልሆን አንገቴን ደፍቼ ለኢትዮጰያ እግርኳስ ለማገልገል ወደ ታች በመውረድ ወደ ህጻናት ስልጠና ፊቴን አዙሬያለሁ፡፡ አሁን ያለው የአሰልጣኞች የፊርማ ከፍያ አንድ ሚሊየንና ከዛ በላይ ነው፤ ብዙ ክለቦች ይፈልጉኛል፤ ሄጄ መውሰድ እችላለሁ፡፡ ግን ያን ማድረግ ያማል፡፡
ከቀደመው ጊዜ በተሻለ ከፍተኛ ገንዘብ እያስገኘ ወዳለው የክለብ አሰልጣኝነት እንድትመለስ እና እንድትሰራ የሚገፋፋህ አካል የለም?
★ በጣም ብዙ ሰው ነው የሚገፋፋኝ፡፡ ሆኖም እኔ አሁን እየሰራሁ ያለሁት ማንም ያልሞከረውንና ያልጀመረውን፣ በጣም ትልቅ ነገር የታየበትና ህብረተሰቡ የተደሰተበትን ስራ ነው፡፡ ልጆቹ አድገው ኳስ ተጫዋች ባይሆኑ እንኳ ከአልባሌ ቦታ መራቃቸው በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በአሁን ጊዜ የ13 እና የ14 አመት ታዳጊዎች መበላሻ መንገዶችና ስፍራዎች በርክቷል፡፡ ከእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ውስጥ እንዳይገቡ ማድረጉም ከፍተኛ ዋጋ አለው፡፡ ስለዚህ ለወደፊቱ ለአገሪቷ የሚጠቅም ነገር እየሰራው ስለሆነ ደስተኛ ነኝ፡፡
እንዳው አንዳንዴ ጫናው አይናፍቅህም? በስራ መወጠሩ፣ ከሚዲያ አካላት ለሚቀርቡ ትችቶች መልስ መስጠቱ፣ ከውጤት ጋር በተያያዘ የሚፈጠረው ጭንቀት፣ ሌሎችም…….በረጅም ዘመን የስራ ህይወትህ አብረውህ የተጓዙት እነዚህ ሁኔታዎች አይናፍቁህም?
★ ከእነዚህ ውስጥ እኔን በጣም የሚናፍቀኝ ከሚዲያው ጋር የማደርገው ውይይት ነው፡፡ እሱ በጣም ያስደስተኛል፡፡ በምጠየቀው ጥያቄም ሆነ በምሰጠውም ምላሽ እደሰት ነበር፡፡ እሱን በደንብ ናፍቄዋለሁ፤ እንዳው የሚዲያ አካላቶች በየሳምንቱ እየመጡ ቢያናግሩኝ ደስ ይለኛል፡፡ እግርኳስ ላይ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ የሚያውቅ ሰው ለሌላኛው የሚያውቀውን መስጠት አለበት፡፡ በእግርኳሱ ሙያ ዘርፍ ሙሉ የሆነ ሰው የለም፡፡ ሁላችንም ጎዶሎ ነን፤ ግን አንዱ ከሌላው ጋር በሚወያየው ላገር የሚጠቅም ነገር ሊመጣ ይችላል፡፡ ይሄ በደንብ ይናፍቀኛል፡፡ ከዛ ውጪ ያሳለፍኩትን ጫና ድጋሚ አልፈልገውም፡፡ በጣም ከባድ ነው፡፡ አስቡት እስቲ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በሱዳን 5-ለ-3 ተሸንፈን እዚህ 2-ለ-0 የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የገባንበትን ምሽት! ህዝቡን አስቡት፡፡ እኛ ለሊቱን ሙሉ እንቅልፍ አልወሰደንም ነበር፡፡ ህዝቡም እንደኛው ሳይተኛ ነው ያደረው፡፡ ሰዎች ባረፍንበት ሆቴል በእኩለ ለሊት መጥተው “አይዟችሁ!” ሲሉን ነበር ያደርነው፡፡ ይሄን እየሰማህ እንቅልፍ አይወስድህም፡፡ በማግስቱም በህዝብ ታጅበን ነው ወደ ሜዳ የገባነው፡፡ ህዝቡን ስታይና የተቀበልከውን ሐላፊነት ስታስብ ምን ያህል ከባድ ጫና እንዳለው ትረዳለህ፡፡ ውጤት ባታመጣ ደግሞ የሚመጣው ጫና የመጨረሻው ከባድ ይሆናል፡፡ እኔ የስኳር በሽተኛ አይደለሁም፤ ደም ብዛት የለብኝም፡፡ በዚህ ሁሉ ጭንቀት መሀል ምንም አይነት ህመም ባለማትረፌ እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ ስለዚህ ወደዚህ አይነት አለም ውስጥ ተመልሼ መግባት አልፈልግም፡፡ ያሁኑ ስራዬም መጠነኛ ጫና አለው፡፡ የስድስት አመት ልጆች ይጣሉና ይካሰሳሉ፤ እነሱን ስታስታርቅ ነው የምትውለው፡፡ “ኳስ ከለከለኝ፤ ኳሱን ይዞ ሮጠ፤…..” ብዙ ክሶች አሉ፡፡ አንተ እዚህ እያሰለጠንክ አንዳንዶቹ ደግሞ ቁጭ ብለው ያወራሉ፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህን ህጻናት ማሳደግና ለፍሬ የማብቃት ያህል ትልቅ ፈተና የለም፡፡ ሆኖም ግን ይህኛውን ጫና በፍቅር የምታሳልፈው ነው፡፡ ይዞብህ የሚመጣ ሌላ ተጽዕኖ የለም፤ እዛው ሜዳ ውስጥ የሚያልቅ ነው፡፡ ያኛው ጫና ግን ቤትህ ድረስ ይዞት የሚመጣ ችግር አለ፡፡ በሚዲያው አካል ከትችት ያለፈ ስድብ ይቀርብብሀል፤ አያውቅህም ግን ሙልጭ አድርጎ ይሰድብሀል፤ በተልኮ ይሰድብሀል፡፡ “እንዲህ በሉ ተብለን ነው፤ይቅርታ አድርግልን፡፡” ያሉኝ የሚዲያ ሰዎችም አሉ፡፡ ምን ታደርገዋለህ እንግዲህ <እንጀራው> ከሆነ ሰድቦኛል ማለት ነው፡፡ እናም እንዲህ አይነቱ ጫና ሁለተኛ አጠገቤ እንዲደርስ አልፈልግም፡፡ ቀሪ ጊዜዬን ባለኝ ሰላም ማሳለፍ ነው የምፈልገው፡፡