በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመሀል ሜዳ ስፍራ ላይ ከሚጫወቱ ፈጣሪ እና ባለልዩ ተሰጥኦ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው። የወላይታ ድቻው በዛብህ መለዮ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያሳየው እንቅስቃሴ የብዙ ሰዎች አይን ውስጥ ከመግባቱም ባለፈ በወላይታ ድቻ የጥሎ ማለፍ ስኬት እና የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎው ሊጠቀሱ ከሚችሉ የቡድኑ ውጤታማ ተጫዋቾች መሀል አንዱ ነው። በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ዛማሌክ ላይ በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም የክለቡን የመጀመሪያ ድንቅ ግብ ያስቆጠረው ተጨዋቹ ስለ ወላይታ ድቻ የተለየ ጉዞ ፣ በአፍሪካ መድረክ ስለነበረው የእስካሁኑ ቆይታው እና በቀጣይ በግብፅ ክለቦችም ስለተፈለገበት ጉዳይ እና አጠቃላይ በእግር ኳስ ህይወቱ ዙሪያ ሰፋ ያለ ቆይታን ከሶከር ኢትዮጵያው ቴዎድሮስ ታከለ ጋር አድርጎል፡፡
በዛብህ የተወለድው ሆሳዕና ከተማ ውስጥ ሲሆን እድገቱ ደግሞ እስከ 8ኛ ክፍል በተማረበት መርቲ ጀጁ ከተማ ውስጥ ነው። በዚህ ወቅት በፕሮጀክት የመጫወት ዕድል ያላገኘው ተጨዋቹ አንድ አመት ብቻ እዛው መርቲ ጀጁ ውስጥ በሚዘጋጅ የክረምት ውድድር ላይ ተሳትፎ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። 1999 ወደ ተወለደበት ከተማ ሆሳዕና ተመልሶ በትምህርቱ የቀጠለ ሲሆን በመጣበት አመት በፍጥነት እግር ኳስ የመጫወት ፍላጎቱን ማሳካት እንዳልቻለ ይናገራል።
” ለምን እንደሆነ ባላውቅም ወደ ሆሳዕና ስመለስ እንደ አዲስ ሰው በመሆኔ በቀላሉ ከሰዎች ጋር መግባባት ባለመቻሌ ኳስ መጫወት እየፈለኩ አልሆን አለኝ። ለወረዳ እንኳን ለመጫወት አስቤ ሳልጫወት ቀረው። ከሰው ጋር ያለመግባባቴ የፈጠረው በመሆኑ ባዝንም 2000 ላይ በሚገባ ተግባብቼ ፍላጎቴም መጫወት በመሆኑ ለሀዲያ ዞን ተመርጬ በደቡብ ክልል በተደረገ ውድድር ወደ ሀዋሳ በመሄድ ዞኑን ወክዬ መጫወት ቻልኩኝ። በዞኑ ባሳየውት እንቅስቃሴም ለደቡብ ክልል በመመረጥ መጫወት ችያለው። ” ይላል።
ክልሉን ወክሎ አዲስ አበባ ላይ በነበረው ውድድር በተካፈለበት ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ማየት መቻሉ የወደፊት ህልሙን ከሩቅ ለማየት አስችሎታል። ለውድድር ሀዋሳ እያለ ሀዋሳ ከተማን የማየት ዕድሉ የነበረው ቢሆንም አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳን ያሸነፈበትን ጨዋታ መመልከቱ ወደፊት ትልቅ ተጨዋች የመሆን ፍላጎቱን እንዳናረው ይናገራል። በመዲናዋ ባደረገው ቆይታም ጥሩ የውድድር ጊዜን ያሳለፈ ቢሆንም በዛው በቀጥታ ክለቦችን ለመቀላቀል አልቸኮለም። ኦሜድላን ጨምሮ ሌሎች ክለቦችም በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡለትም ለትምህርቱ ትኩረት ይሰጥ ስለነበር እና የ12ተኛ ክፍል ተፈታኝ የነበረ በመሆኑ እሺታውን እልሰጣቸውም። ከዛ ይልቅ ወደ ሆሳዕና ተመልሶ ወልቂጤ ላይ በነበረው የክለቦች ሻምፒዮና ላይ መሳተፍን መርጧል። በዛም አጋጣሚ ከቡድኑ ጋር አሸናፊ በመሆን ጨርሰ። ከዚህ በኃላም ራሱን ከዚህ በላይ ማሻሻል እንደሚችል በማሰብም በተለያዩ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ቀጠ። በዛው አመት ክረምት ላይ በሻሸመኔ ወደ ብሔራዊ ሊግ ለመግባት በክለቦች መሀከል በነበረ ውድድር ላይ ተሳትፎ በግሉ ባሳየው ብቃት ወደ ሙገር ሲሚንቶ ቢ ቡድን መግባት ችሏል። ሆኖም የሙገር ቆይታው እንዳሰበው አልሆነም። ይህ የሆነበትን ምክንያት እና በመቀጠል ስላደረገው የክለብ ጉዞ እንዲህ ይላል ” በሙገር ሶስት አመታትን ለመቆየት ብስማማም ከአንድ አመት በኃላ እናሳድግሀለን ብለው ቃል ገብተውልኝ ነበር። ሆኖም ከኔ በላይ ሲኒየር የሚባሉ ተጨዋቾችን ሁለት አመት ጠብቀው ሲያድጉ እኔን ባሉኝ ሰአት ባለማሳደጋቸው ቀሪ ጊዜ እያለኝ ከአንድ ከዛው ከመጣ ጓደኛዬ ጋር በመሆን ቡድኑን ለቀን ወደ ሆሳዕና ተመለስን። በወቅቱ ሆሳዕና ጥሩ ደረጃ ላይ ነበር። በሄድንበት አመት 2003 ላይ ሆሳዕና ብሔራዊ ሊግ (አንደኛ ሊግ) ገባ። እኔም ሁለት አመት በመፈረም የእግር ኳስ ጉዞዬን ጀምርኩ። ”
በሆሳዕና የሁለቱን አመት ከጨረሰ በኃላ በድጋሚ ውሉን በማራዘምም በድምሩ ሶስት አመታትን ካሳለፈ በኃላ በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጥሪ ቀርቦለት 2006 ላይ ወላይታ ድቻን ተቀላቅሏል። ሆኖም በጊዜው እንደነ ባዬ ገዛኸኝ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ ፣ አሸናፊ ሽብሩ ፣ አላዛር ፋሲካ እና አናጋው ባድግ የመሳሰሉ ተጫዋቾች በያዘው ቡድን ውስጥ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ሰብሮ መግባት ቀላል አልሆነለትም። በሂደት እነዚህ ተጨዋቾች ወደ ሌሎች የሊጉ ክለቦች ሲያመሩ ግን ድቻ አዳዲስ ተጫዋችን ከማስፈረም ይልቅ ለሌሎቹ ዕድል በመስጠት እና ከተችኛው ሊግ ተጫዋችን በማምጣት ነበር ቡድኑን የገነባው። በዛብህም በዚህ ወቅት ሰፊ የመጫወት ዕድል ካገኙ ተጨዋቾች መሀከል አንዱ ሆኗል። ክለቡ በዚህ አኳኃን ቀጥሎ አምና የኢትዮጵያ ዋንጫን በማሸነፍ ዘንድሮ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። ሆኖም ባሳለፍነው ክረምት ድቻ ከወትሮው በተለየ በዝውውር ሂደቱ ላይ ተሳታፊ ነበር። የዘንድሮው የሊግ አጀማመሩ ግን እንደተጠበቀው ባለመሆኑ ከዘጠኝ አመታት ቆይታ በኃላ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን አሰናብቶ ለዘነበ ከበደ ሀላፊነት ሰጥቷል። “አሁን ላይ ቡድናችን ውስጥ ምንም የተለየ ነገር የለም። አንዳንዴ እግር ኳስ ውስጥ ውጣ ውረዶች አሉ። የችሎታ መብዛት እና ማነስ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ” የሚለው በዛብ የመጀመሪያ ዕድል ከሰጠው መሳይ ተፈሪ ስንብት በኃላም ደስተኛ ሆኖ ቡድኑን እያገለገለ እንዳለ እና በቡድኑ ውስጥ ከየትኛውም ክለብ በላይ የመተሳሰብ እና መረዳዳት መንፈስ እንደሰፈነ ይናገራል። ለበዛብህ የቡድኑ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ስኬት በአመዛኙ የሚገናኘውም ከቡድኑ ማንፈስ እና ከዐዕምሮ ዝግጅት ጋር ነው። የሀገሪቱ እግር ኳስም ያጣው የሄንኑ እነደሆነ አፅንኦት ሰጥቶ ያስረዳል።
“ለኛ መነጋገራችን እና መተባበራችን በአጠቃላይ ቡድኑ ውስጥ ያለው መንፈስ ለአሁኑ ውጤት አግዞናል። በዚህም ምክንያት ታሪክ ሰርተናል። በኛ ሀገር እግር ኳስ ይጎለናል ብዬ የማስበውም የዐዕምሮ ጥንካሬ ነው። እንደ ሀገርም ሳይኮሎጂው ላይ ብንሰራ የተሻልን እንሆናለን። አሰልጣኛችን ዘነበ ሁሌ የሚናገረው ነገር አለ ‘እግር ኳስ ምንም ማለት አይደለም። ጭንቅላታችሁን ነፃ ማድረግ አለባችሁ። እጫወታለው ብላችሁ ካሰባችሁ እንደምትችሉ ማወቅ አለባችሁ’ ይላል። ለምሳሌ እኔ በግሌ አሁን 4 ያህል ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን አድርጌያለው። ብዙም የከበደኝ ነገር የለም። ፈርቼም አላውቅም። እኛ ሀገር መሰራት አለበት ብዬ የማስበው ጭንቅላታችን ላይ ነው። ብሔራዊ ቡድናችንም የሚጎለው ይህ ነገር ነው። ለሳይኮሎጂ ትኩረት መሰጠት አለበት። በአብዛኛው ጊዜ በሜዳችን ላይ አጥቅተን ከሜዳ ውጭ ተከላክለን መጫወት አለብን ይባላል። በሜዳ ላይ አጥቅተን ከተጫወትን ከሜዳ ውጪም አጥቅተን ስለመጫወት ማሰብ አለብን። እኛ ከሜዳ ውጭ ከዛማሌክ ስንጫወት አጥቅተን ለመጫወት ነበር ያቀድነው። በሁለቱም ጨዋታ ለመከላከል ወደ ሜዳ አልገባንም። ለዚህ ዋናው ደግሞ አሰልጣኙ ነው። መመሪያ ሚሰጥህ እሱ ነው። አንተ የሌለህን መከላከል ሀይል ተከላከል ብሎ ማስጨነቅ የለበትም። በርግጥ በተሰጠው ሚና ቦታውን ማስከበር የተጫዋቹ ሀላፊነት ነው። ሁሉም ባለው ብቃት የተሰጠውን መወጣት ይቻላል። ከዛ ባለፈ ግን ማድረግ ማይችለውን ኃላፊነት መስጠት ከባድ ይሆናል፡፡ ” ይላል።
ወላይታ ድቻ በካይሮ ከዛማሌክ ጋር በነበረው የመልስ ጨዋታ በመለያ ምቶች አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ሲያልፍ የግብፅ ክለቦችን ትኩረት ከሳቡ ተጨዋቾች መሀል በዛብህ አንዱ መሆን ችሏል። አማካዩ በወቅቱ መነጋገሪያ ስለነበረው ስለዚህ ጉዳይ እና ቀጣይ እቅዶቹ ሀሳቡን ሲሰጥ እንዲህ ብሏል።
“በቅድሚያ እግዚአብሔር ይረዳኛል ብዬ አስባለው። ከግብፅ ክለቦች ጋር ብዙ ተነጋግረናል። አጋጣሚው መቷል። ያው ከተሳካ ተሳካ ካልተሳካም ደግሞ ነገ ሌላ ይመጣል የሚል ተስፋ ነው ያለኝ። አሁን የሰጡኝ የሙከራ እድል ነው። ዘንድሮ በክለቤ ውል ጨራሽ ነኝ። አሁን ላይ ከዛ በላይ ሙሉ ትኩረቴ ያለው ግን የቡድኔን ስኬታማነት በማስቀጠሉ ላይ ነው። ከዚህ ባለፈ ብሔራዊ ቡድን ገብቶ የመጫወት ፍላጎቴ የምንጊዜም ህልሜ ነው። ውስጤ ሁሌም ሚያስበው መለያውን ለብሶ ኢትዮጵያን በመወከል መጫወትን ነው። ከዚህም በላይ ጠንክሬ ሰርቼ ይህን ህልሜን እውን ለማድረግ እስባለው።
በዛብህ መለዮ እዚህ ለመድረሱ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በወላይታ ደቻ አብሮት መጫወት የቻለውን ወንድሙ እንዳለ መለዮ ትልቁን ቦታ ይወስዳል። በዛብህ ስለወንድሙ ሲንምገር “በመጀመሪያ የረዳኝን ፈጣሪ ማመስገን እፈልጋለሁ ሲቀጥል እንደ አባትም እንደ ወንድም ሆኖ እዚህ እንድደርስ የረዳኝ ወንድሜ እንዳለ ነው። እሱ ኳስን ባይጫወት እኔም እዚህ ባልደረስኩ ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ ከራሱ ህይወት ቀንሶ በብዙ ነገሮች አድርጎልኛል።” ይላል። ስለወንድሙ ሲያስብ የማይረሳውን አጋጣሚም በዚህ መልኩ አካፍሎናል
” አንድ ወራጅ ውሀ አለ። እሱ ኳስን ሲጫወት ወደዛ አካባቢ እየሄደ ይሰራ ነበር። እኔ ደግሞ ልጅ ስለነበርኩ ሲሰራ እየተደበኩ አይ ነበር። እሱ ያን ደራሽ ውሀ ተሻግሮ ሲሮጥ እኔም ተደብቄ እየሮጥኩ እሰራ ነበር። እናም ረጅም ርቀት ሮጦ ሲሄድ ሳልደርስበት ቀረሁ። ስፈልገውም አጣውት። ቦታው ጫካ ነው ያስፈራል። በአጋጣሚ ግን እኔ እንደተከተልኩት ሰምቶ ሲመለስ እኔ የለውም። ከዛ ፈልጎ አገኘኝ እና ለምን መጣህ ብሎ ሲጠይቀኝ ‘አንተ ስትሮጥ አይቼ ነው’ አልኩት። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ፍላጎቴን አይቶ ትጥቅ ገዝቶ ሰጠኝ። ከሱ ጋር በስረአት አብሬው እንድሰራ ረዳኝ። ያኔ በቃ እግር ኳስ መጫወት እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ።”
የሽመልስ በቀለ አድናቂ የሆነው እና አሁን ካሉ ተጨዋቾች መሀከል ደግሞ ከታፈሰ ሰለሞን ጋር መጫወትን የሚመኘው በዛብህ በመጨረሻም ወንድሙ እንዳለ መለዮን አመስግኗል።
” ወንድሜን በጣም ማመስገን እፈልጋለው። በመቀጠል በልጅነቴ ብዙ ለረዳኝ ሱልጣን መሀመድ ፣ ሆሳዕና እያለው ያሰለጠነኝ አሰልጣኝ ደረጀ ፣ የአሁኑ የደቡብ ፓሊስ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ፣ የሀምበሪቾው አሰለጣኝ ተረፈ እና ትልቁን ዕድል የሰጠኝ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን እጅግ እጅግ አድርጌ ላመሰግን ፈልጋለው ፡፡ “