በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ ዛሬ ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ተካሂደው ጅማ አባ ቡና ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ድል አስመዝግበዋል።
በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ ውድድር እያከናወነ የሚገኘው ጅማ አባ ቡና የቦርድ አመራሩን ከማጣት አንስቶ ከዋና አሰልጣኙ ግርማ ሐብተዮሀንስ ጋር እስከመለያየት መድረሱ የሚታወስ ሲሆን ተጫዋቹ ደሞዝ አልተከፈለንም በሚል ወደ ሚዛን አማን አናመራም በማለት አቋማቸውን ገለፀው ነበር። ሆኖም ችግሩ የማታ ማታ ተፈትቶ በምሽት ወደ ስፍራው ያቀኑት አባ ቡናዎች በሜዳው አንዴ ብቻ ሽንፈትን ያስተናገደው ቤንች ማጂ ቡናን ገጥመው 2-0 ማሸነፍ ችለዋል። ሱራፊል ጌታቸው በ31ኛው ደቂቃ ቀዳሚውን ጎል ሲያስቆጥር ብዙዓየው እንደሻው በ61ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን አክሏል።
ሆሳዕና ላይ ስልጤ ወራቤን ያስተናገደው ሀዲያ ሆስዕና 1-0 አሸንፏል። በመጀመሪያው ሳምንት ሊካሄድ የነበርው ጨዋታ ዛሬ በተስተካካይ ፕሮግራም የተደረገ ሲሆን ለረጅም ደቂቃዎች ያለ ግብ ዘልቆ በ86ኛው ደቂቃ ተዘራ አቡቴ ባስቆጠራት ወሳኝ ጎል ሆሳዕናዎች አሸንፈው ወጥተዋል። ሀዲያ ሆሳዕና የፊታችን ረቡዕ ሚያዝያ 23 ወደ ወልቂጤ አምርቶ የመጀመሪያውን ዙር የመጨረሻውን ጨዋታ ያከናውናል።
በርካታ ጨዋታ በተስተካካይ መርሀግብር እያከናወነ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ ጨዋታዎቹን ተጠቅሞ ወደ አናት መጠጋቱን ቀጥሏል። ዋና አሰልጣኙ በእገዳ ላይ የሚገኘው ነገሌ ከተማን ያስተናገደው ወልቂጤ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ብሩክ በየነ በ6ኛው ፣ ጌታሁን ባፋ በ36ኛው ደቂቃ፣ 55ኛው ደቂቃ መዝገቡ ወልዴ የወልቂጤን ጎሎች ማስቆጠር የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው።
ወልቂጤ ከተማ በቀጣይም በሜዳው ሀዲያ ሆሳዕና (ሚያዝያ 3) እና ድሬዳዋ ፖሊስን (ሚያዝያ 8) የሚስተናግድ ይሆናል።