በየጊዜው እንደአዲስ በሚፈጠሩ ነገሮች የተነሳ በልተረጋጋ ሁኔታ የውድድር አመቱን አጋማሽ ያለፈው የወልድያ እግርኳስ ክለብ በተለያዩ ችግሮች ተወጥሮ ይገኛል። አሁን ደግሞ ያለፉትን ሁለት አመታት በም/አሰልጣኝነት እያገለገለ ይገኝ የነበረው ኃይማኖት ግርማ ከድሬደዋ ከተማ ሽንፈት በኋላ በውጤት መጥፋት ምክንያት በገዛ ፍቃዱ ከቡድኑ ጋር መለያየቱ እርግጥ ሆኗል። አሰልጣኝ ኃይማኖት ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ከቡድኑ ጋር ከተለያየ በኋላ በድርድር መመለሱ ይታወቃል።
ቡድኑ ከፊቱ ለሚጠብቁት ወሳኝ ጨዋታዎች አሁን ላይ ያሉት 10 የሜዳ ላይ ተጨዋቾች እና 3 ግብ ጠባቂዎች ብቻ መሆናቸው ደግሞ ሌላው ችግሩ ሆኗል። ጉዳዩ በዋናነት ዘጠኝ ተጨዋቾች በጉዳት ላይ ከመሆናቸው ጋር ይያያዛል። በሁለተኛው ዙር ይህንን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ክለቡ አሳልፈው መኮንን ፣ መስፍን ኪዳኔ ፣ ሞገስ ተስፋዬን ማስፈረሙ ቢታወስም ከአልሳዲቅ አልማሀዲ እና በላይ አባይነህ ጋር የደረሰበት ስምምነት ከፌዴሬሽኑ በተላለፈበት ውሳኔ ምክንያት ከዳር መድረስ አልቻለም። ዘጠኙ ተጨዋቾች በፍጥነት ከጉዳታቸው አገግመው የማይመለሱ በመሆኑ እና በቅጣት (በ5 ቢጫ እና ቀይ ካርድ) ምክንያት ያጣቸውን ተጨዋቾች ጨምሮ ቅጣት ከተላለፈባቸው ሶስቱ ተጨዋቾች ጋር ያለው ውዝግብ እልባት አለማግኘቱ ቡድኑ በቀጣይ በሚኖሩ ጨዋታዎች በ13 ተጨዋቾች ብቻ ጨዋታዎችን የመጀመር አደጋ እንዲጋረጥበት አድርጓል።
በተያያዘ ዜና ከታደለ ምህረቴ ፣ ያሬድ ብርሀኑ እና ፍፁም ገ/ማርያም ጋር ተያይዞ ወልድያ እግር ኳስ ክለብ ጥሪዬን አልተቀበሉም በማለት ያስተላለፈው የ180 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እና የሁለት አመት ዕገዳ ውሳኔ በፌዴሬሽኑ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ውድቅ ከተደረገ በኃላ ክለቡ ውሳኔውን አሻሽሎ የሁለት አመት እግዱን በማንሳት የገንዘብ መጠኑን ወደ 500 ሺህ ብር ከፍ አድርጎታል። ሆኖም ሦስቱ ተጨዋቾች በድጋሜ ይህን ያህል ገንዘብ አንከፍልም በማለታቸው ጉዳዩ ሳይቋጭ በእንጥልጥል ተይዟል ።