በቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ጨዋታ የኮንጎ ሪፐብሊኩ ካራ ብራዛቪልን በአዲስአበባ ስታዲየም ያስተናገደው የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በገባው አዳነ ግርማ ጎል ታግዞ 1-0 ማሸነፍ ችሏል።
ባለሜዳዎቹ ፈረሰኞች ባሳለፍነው ረቡዕ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ አሸናፊነት በተመለሱበት የፋሲል ከተማው ጨዋታ ከተቀሙባቸው የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾች ውስጥ ግብጠባቂው ለአለም ብርሃኑን በሮበርት ኦዶንካራ እንዲሁም ተከላካዩ ደጉ ደበበን በጋዲሳ መብራቴ በመተካት በተመሳሳይ የ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ጨዋታው ሲገቡ ባደረጉት የተጫዋቾች ሽግሽግ አማካዩ ምንተስኖት አዳነ በዛሬው ጨዋታ ከሰልሀዲን በርጌቾ ጋር በመሀል ተከላካይ ስፍራ ላይ ተጣምሯል። እንግዶቹ ካራ ብራዛቪሎች በአንፃሩ በ4-2-3-1 አሰላለፍ ጨዋታውን ሲጀምሩ በተጠባባቂ ወንበር ላይ አምስት ተጫዋቾችን ብቻ መያዛቸው ከጨዋታው መጀመር በፊት አስገራሚ አጋጣሚ ነበር፡፡
በአጠቃላይ በመጀመሪያው 45 በነበረው የጨዋታ እንቅስቅሴ እንግዳዎቹ ካራ ብራዛቪሎች እንደተጠበቀው ፊት ላይ በመጨረሻ አጥቂነት ያሰለፉት ቦማንዬ ሊማ በስተቀር ቀሪዎቹን የቡድኑ ተጫዋቾች ወደራሳቸው የግብ ክልል በማፈግፈግ በተደራጀ ሁኔታ ሲከላከሉ ተስተውሏል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ ይህንን የተጠቀጠቀ የመከላከል አደረጃጀት ሰብሮ ለመግባት ያደረጉት እንቅስቃሴ ደካማነትን ያስመለከተን ነበር። ካራዎች ከአራቱ ተከላካዮች ፊት ያሰለፏቸው ሁለቱ የተከላካይ አማካይነት ባህሪ ያላቸው ስታኒስላስ አኪራና ኤልቪስ ፊላኬምቦ በቅዱስ ጊዮርጊሶቹ በኩል በሜዳው ቁመት መሀል ለመሀል የሚረጉ ጥቃቶች ላይ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑትን ጋዲሳ መብራቴንና አብዱልከሪም ኒኪማን እግርበእግር በመከተል በጨዋታው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ተፅዕኗቸውን እንዳያሳርፉ መገደብ ችለዋል፡፡
በመጀመሪያ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ20ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ አሰፋ ከቀኝ መስመር ያሻማትን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ አቡበከር ሳኒ ቢገጭም ኳሷ ግን ኢላማዋን ሳትጠብቅ ከቀረችበት አጋጣሚ በዘለለ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በዛሬው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከተሰለፉት ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች መካካል በቀኝ በኩል የተሰለፈው በኃይሉ አሰፋ በተቃራኒው ከተሰለፈው አቡበከር ሳኒ በተሻለ ወደ መሀል በአንፃራዊነት እያጠበበ በመጫወት ለቀኝ መስመር ተከላካዩ አብዱልከሪም መሀመድ በቂ የሆነ የመጫወቻ ሜዳ ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ነገርግን አብዱልከሪም እነዚህን ክፍተቶች ተጠቅሞ ወደ ተቃራኒ የማጥቃት ወረዳ ከገባ በኃላ ወደ ውስጥ የሚያሻማቸው ኳሶች በጊዮርጊስ ተጫዋቾች ከተጋጣያቸው አንጻር በተክለ ቁመና አነስተኛ በመሆናቸው በቀላሉ ሲመክን ተስተውሏል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ማጥቃት ላይ አተኩረው ለመጫወት እንደመሞከራቸው የካራ ተጫዋቾች በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ላይ እምብዛም ተነሳሽነት አላሳዩም እንጂ ምንያህል ጊዮርጊስ ተጋላጭ እንደነበረ ካራዎች በሁለት አጋጣሚዎች በጊዮርጊስ የግብ ከልል አቅራቢያ ከቁጥር ብልጫ ጋር ያገኟቸውን ኳሶች በተጫዋቾቻቸው ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ምክንያት ያልተጠቀሙባቸው እድሎች ማሳያዎች ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማሽ በተለይ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ የጨዋታውን ሂደት በመቆጣጠር ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ በተለይም በ52ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ አሰፋ እና ጋዲሳ መብራቴ በአንድ ሁለት ቅብብል ያለፉትን ኳስ በሀይሉ አሰፋ በግቡ ትይዩ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ የላከውን ኳስ የካራው ግብጠባቂ ማሳ ሞሂካሎና የግቡ ቋሚ ተጋግዘው ያዳኑዋት ኳስ በጣም አስቆጭ ሙከራ ነበር፡፡ ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩትን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ መሀል የሚያሻሙዋቸውን ከኳሶች ለመመከት ሁለቱ የተከላካይ አማካዮች በጥልቀት ለሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ቀርበው የአየር ላይ ኳሶቹን ለመሻማት በሚያደርጉት ጥረት የተነሳ ኳሶቹ በካራ ተጫዋቾች ተገጭተው ሲመለሱ ከጎሉ ፊት ለፊት በቅርብ ርቀት አብዱልከሪም ኒኪማና ጋዲሳ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮችን የመሀል ሜዳው መስመር ላይ በማቆም የቀሩትን ተጫዋቾች በሙሉ በካራ ብራዛቪሎች የሜዳ ክልል ወስጥ በነፃነት እንዲያጠቁ በመፍቀድ ይበልጥ ጫና አሳድረው ለመጫወት ሙከራ አድርገዋል ፤ ነገርግን በቁጥር በተቃራኒ የሜዳ ክፍል ላይ በርከት ቢሉም ተመጣጣኝ የሆነ የተጫዋቾች ስርጭት ባለመኖሩ በተመሳሳይ ቦታ ላይ በርከት ያሉ ተጫዋቾች እየተገኙ የማጥቃት ሂደቱ ውጤት አልባ እንዲሆን ተገዷል፡፡
ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም በሚመስል መልኩ በ61ኛው ደቂቃ ላይ ካራ ብራዛቪሎች በመጨረሻ አጥቂነት ጨዋታውን የጀመረውንና የመጀመሪያ የአየር ላይ ኳሶችን በማሸነፍ እንዲሁም የቡድን አጋሮቹን ወደ ጨዋታ በማስገባት በኩል ደካማ የነበረውን ቦማንዬ ሊማን በማስወጣት ሌላኛውን አጥቂ ራሲን ሉዋምባን በመተካት በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ አስቻለው ታመነን በሁለት ቢጫ ምክንያት መጠቀም ያልቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከተጫዋቹ ያገኙት የነበረውን ኳስን በሰንጣቂ ሩጫዎች ከራስ የሜዳ ክፍል አንስቶ ከፊቱ የሚገኙትን ክፍተቶች በመጠቀም ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል በመድረስ ለቡድን አጋሮቹ ኳስን የማቀበል ሂደት በዛሬው ጨዋታ ላይ መመልከት አልቻልንም ፤ በተቃራኒው ምንተስኖትና ሰልሀዲን ክፍተቶችን ለመጠቀም ከማሰብ ይልቅ በቀጥተኛ አጨዋወት ኳሶችን ወደ ፊት በቀጥታ ማሻገርን ሲመርጡ ተስተውሏል ይህም ለረጃጅሞቹ የካራ ተጫዋቾች ጨዋታውን አቅልሎላቸው ነበር፡፡
በተጫዋቾች ጉዳት እየታመሱ የሚገኙት ፈረሰኞቹ በተጠባባቂ ወንበር በብቸኛ የማጥቃት ባህሪ የነበረውን አዳነ ግርማን በጋዲሳ መብራቴ ተክተው በማስገባት ነገሮችን ለመለወጥ ሞክረዋል፡፡ የጋዲሳ መውጣት የቡድኑን የተከላካይ ክፍል ከአጥቂው ክፍል ጋር ለማገናኘት ሲሞክር የነበረውን ተጫዋች ለቡድኑ ከማሳጣቱ በዘለለ የጊዮርጊስን የማጥቃት እንቅስቃሴ ይበልጡኑ ቅርፁን እንዲያጣ አድርጎት ተስተውሏል ፤ በዚህም ቅያሬ በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጫዋቾች ወደ ካራ የግብ ክልል ተጠግተው መደርደር ቢችሉም መሀል ሜዳው ሙሉ ለሙሉ በመሰበሩ የተነሳ በቂ የኳስ አቅርቦት ባለማግኘታቸው ሲባክኑ ተስተውሏል፡፡ ነገርግን በጥልቀት በመከላከል ስራ ላይ ተጠምደው የነበሩት ካራ ብራዛቪሎች በ78ተኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሳኒ ከቀኝ መስመር በረጅሙ ያሻማውን ኳስ የካራው ግብጠባቂ ማሳ ሞሂኮሎ እጅግ ደካማ በሆነ የጊዜ አጠባበቅ ከግብ ክልሉ ወጥቶ የተሳሳተውን ኳስ በሀይሉ ቱሳ ወደግብ የላካትን ኳስ ተቀይሮ የገባው አዳነ ግርማ በግንባር በመግጨት ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ከዚች ግብ መቆጠር በኃላ ጊዮርጊሶች በአዳነ ግርማና አብዱልከሪም ኒኪማ አማካይነት ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በአንፃሩ ካራ ብራዛቪሎች በ87ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ሜሬቪስ ኪቩቱካ በመቀስ ምት የሞከራትን ኳስ ሮበርት ሊያድንበት ችሏል፡፡
ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ጊዮርጊሶች ከ10 ቀናት በኃላ ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ የተሻለ እድልን ይዘው ወደ ኮንጎ የሚጎዝ ይሆናል፡፡