ወላይታ ድቻ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ዛማሌክን ከውድድር ማስወጣቱ ተጫዋቾቹ በሀገሪቱ ክለቦች እይታ ውስጥ እንዲገቡ በር ከፍቷል፡፡ ከጃኮ አራፋት እና በዛብህ መለዮ በመቀጠልም የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ኃይማኖት ወርቁ ሌላው የተፈለገ ተጫዋች ሆኗል፡፡
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሀዋሳ ከተማን ለቆ ወላይታ ድቻን የተቀላቀለው ኃይማኖት በዘንድሮው ወላይታ ድቻ የአፍሪካ ውድድር ጉዞ ላይ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ከሚገኙ ተጫዋቾች አንዱ ሲሆን በሁሉም ጨዋታዎች ላይም መሰለፍ ችሏል፡፡ ይህን ተከትሎም ስሙ ከግብፅ ክለቦች ጋር መያያዝ ጀምሯል፡፡ ተጫዋቹ በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፡፡ “በክለቦቹ ፍላጎት በጣም ደስ ነው ያለኝ፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ መፈለጌ በራሱ በጣም ኩራት ነው፡፡ በቀጣይ የሚኖረኝ የሙከራ ጊዜ ነው፡፡ ከፈጣሪ ጋር አሳካዋለው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ”
አማካዩ ከክለቦቹ ጋር ግንኙነት ከመፍጠሩ ውጪ በየትኛው ክለብ እንደተፈለገ ይፋ ባይደረግም ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ ግን ምስር ኤል ማቃሳ እና ኤንታግ ኤል ሀርቢ የኃይማኖት ፈላጊ መሆናቸውን እና በዚህ ክረምት ለሙከራ ወደ ስፍራው እንደሚያቀና ለማወቅ ችለናል፡፡