በቶታል አፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ሊብያን 15-0 በሆነ የአጠቃላይ ውጤት በማሸነፍ ወደ መጨረሻው የማጣሪያ ዙር አልፏል፡፡ ሉሲዎቹ አዲስ አበባ ላይ ሊቢያን አስናግደው 7-0 በሆነ ውጤት በረቱበት ጨዋታ በተጋጣሚያቸው ላይ ፍፁም የሆነ የበላይነት ሲያሳዩ ሎዛ አበራ አራት ግቦችን አስቆጥራለች፡፡
አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ከሳምንት በፊት ካይሮ ላይ 8-0 ያሸነፈውን ሙሉ ቡድን አንድም ለውጥ ሳታደርግ አጫውታለች፡፡ ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ሊቢያን ተጭነው የተጫወቱት ባለሜዳዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ያለቀላቸውን እድሎችም አምክነዋል፡፡ በ13ኛው ደቂቃ የተከላካይ አማካይ የሆነችው ህይወት ደንጊሶ ከቀኝ መስመር የተሰጠውን ቅጣት ምት በቀጥታ መትታ የሊቢያዋ ግብ ጠባቂ አምል አሊ ረሂም አቋቋም ስህተት ታክሎበት የመጀመርያው ጎል ተቆጥሯል፡፡ ከደቂቃ በኃላ ሎዛ ከግራ መስመር ይዛ ወደ አደጋ ክልሉ የገባችውን ኳስ ሰናይት ቦጋለ ሞክራ የግቡ ቋሚ ሲመልስባት በ21ኛው ደቂቃ የሊብያ ግብ ጠባቂ አማል ረሂም የምርቃት ፈለቀን አደገኛ ኳስ አምክናባታለች። ከሁለት ደቂቃ በኃላ ዙሌካ ጁሃድ ከቀኝ መስመር ጠርዝ ወደ ሳጥኑ ያሻገረችው ኳስም የውስጠኛውን ቋሚ ገጭቶ ተመልሷል፡፡
ሉሲዎቹ ሎዛ ከሳጥኑ ውጪ ባስቆጠረችው ግብ መሪነቱን ወደ ሁለት ሲያሰፉ ግብ አስቆጣሪዋ ሎዛ እና ረሃማ ዘርጋ የመጀመሪያው 45 ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ያገኙትን የግብ ዕድሎች ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡ አጋማሹ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ረሂማ ሶስተኛው ግብ ከምርቃት የተቀበለችውን ኳስ ተጠቅማ በግንባሯ በመግጨት ከመረብ አዋህዳለች፡፡
ከእረፍት መልስ የኢትዮጵያ ጫና የበረታ ሲሆን ሊቢያዎች ኳስን ከግብ ክልላቸው መስርተው ለመውጣት የነበራቸው ፍላጎት በሚቆራረጡ እና የተሳሳቱ መቀባበሎች ምክንያት ሊሳካ አልቻለም፡፡ ካይሮ ላይ ግብ ማስቆጠር የቻለችው ቤተልሄም ከፍያለው ግብ ጠበቂዋ አማል ረሂምን አልፋ በማይታመን መልኩ ባዶ ግብ በ48ኛው ደቂቃ ስትስት በ51ኛው ደቂቃ ሎዛ የግል ብቃቷን ያሳየችበትን ግብ አስቆጥራለች፡፡
እስከ 73ኛው ደቂቃ ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የግብ ልዩነቱን የሚያሰፋባቸው ዕድሎችን አግኝቶ በረሂም ጥረት እና በሉሲዎቹ የአጨራረስ ድክመት ግብ ከመሆን ድነዋል፡፡ በ73ኛው ደቂቃ ሰናይት በግሩም ሁኔታ ከፍፁም ቅጣት ምቱ ጠርዝ ግብ በማስቆጠር መሪነቱን ወደ 5 አስፍታለች፡፡ በ82ኛው ደቂቃ ሎዛ ሃትሪክ የሰራችበትን ግብ ከመረብ ስታዋህድ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ሎዛ የጨዋታው አራተኛ ግቧን አደጋ ክልሉ ውስጥ ያገኘችውን ኳስ ተጠቅማ አስቆጥራለች፡፡
የሊቢያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አንድ የማዕዘን ምት ከማግኘቱ እና ለሁለት ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ከመድረሱ ውጪ በጨዋታው ላይ ለተጋጣሚው የሚመጥን እንቅስቃሴ አላሳየም፡፡
ኢትዮጵያ በድምር ውጤት 15-0 በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ችላለች፡፡ በመጨረሻው ዙር ማጣሪያም ሴኔጋልን ያሸነፈችውን አልጄሪያን የምትገጥም ይሆናል፡፡