የከፍተኛ ሊግ አጫጭር መረጃዎች

የሀምበሪቾ እና ሀላባ ጨዋታ ለሚያዝያ 6 ተቀጥሯል

በ8ኛው ሳምንት ዱራሜ ላይ በመካሄድ ላይ የነበረውና በደጋፊዎች ረብሻ ምክንያት የተቋረጠው የሀምበሪቾ እና የሀላባ ጨዋታ የካቲት 23 በሀዋሳ ይቀጥላል ተብሎ መርሀ ግብር ቢወጣለትም ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሽሎ በወጣው ፕሮግራም ግን የመጫወቻ ቦታው ወደፊት ይገለፃል በሚል መቼ እንደሚደረግ ሳይታወቅ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ትላንት (ሚያዝያ 2) የሁለቱንም የቡድን መሪዎች በመጥራት ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ካነጋገረ በኋላ በይፋ በደብዳቤ ባይገለፅም በስብሰባው በተስማሙት መሰረት ሀዋሳ ላይ ሚያዝያ 6 እንደሚሆን ተነግሯል።  ሀላባ ከተማ 1-0 እየመራ የተቋረጠውን ጨዋታ ሀላባ ከተማ በአሸናፊነት የሚያጠናቅቅ ከሆነ የምድብ ለ መሪ ሆኖ የመጀመርያውኖ ዙር ማጠናቀቅ ይችላል።


የአሰልጣኞች ስንብት 

ኢትዮጵያ መድን

ኢትዮጽያ መድንን ባለፈው አመት አጋማሽ ላይ ማሰልጠን የጀመሩት አሰልጣኝ ደረጀ በላይ ሚያዝያ 2 ቀን 2010 ላይ ከክለቡ ጋር ተለያይተዋል። ለአንድ አመት ኮንትራት ተፈራርመው የነበሩት ሁለቱ ወገኖች በውል ማራዘም ዙሪያ መስማማት ባለመቻላቸው መለያየታቸው ታውቋል። የቀድሞው የክለቡ ኮከብ ሀሰን በሽር በሁለተኛው ዙር መድንን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት የሚመራ ይሆናል።

ደሴ ከተማ

አሰልጣኝ ጌታሁን ገብረጊዮርጊስን ያሰናበተው ደሴ ከተማ ለምክትሉ ቴዎድሮስ ቀነኒ እድል ቢሰጠውም ባለፈው ሳምንት አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ቀነኒንም አሰናብቷል። ቡድኑ ያለ አሰልጣኝ ሰበታ ከተማን በገጠመበት ጨዋታም 4-2 ሽንፈትን አስተናግዷል።

በተያያዘ ዜና ደሴ ከተማ የዋና አሰልጣኝነት እና የምክትል አሰልጣኝነት የቅጥር ማስታወቂያ ማውጣቱን አስታውቋል። በዋና አሰልጣኝነት የB ላይሰንስ እና የ3 ዓመት የስራ ልምድ ያለው እንዲሁም በምክትል አሰልጣኝነት የC ላይሰንስ እና 0 ዓመት የስራ ልምድ ያለው እንደሚፈለግ ተነግሯል።


ነገሌ ቦረና 

በከፍተኛ ሊጉ ደካማ የውድድር ጊዜን እያሳለፈ ያለው ነገሌ ቦረና ከአሰልጣኝ ነፃነት ጋር ሊለያይ እንደሆነ ተሰምቷል። አሰልጣኙ ከተጫዋቾች ጋር ያለመግባባት እና በአመቱ ውስጥ ክለቡ ከሚጠበቅበት በታች ውጤት በማስመዝገቡ ምክንያት ለመለያየት ከጫፍ እንደደረሱ ነው የተገለፀው፡፡ ቡድኑ በአሁኑ ሰዓት አሰልጣኝ ነፃነትን እገዳ የጣለበት ሲሆን በዚህ ሁለት ቀን ውስጥም የመጨረሻ ውሳኔውን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።     


ሻሸመኔ ከተማ 

በዘንድሮ አመት በተፎካካሪነት ከተጠበቁት ቡድኖች አንዱ የሆነው ሻሸመኔ ከተማ ዘንድሮ ከሚጠበቅበት 45 ነጥብ ውስጥ መስብሰብ የቻለው 14 ያህል ብቻ ነው። ክለቡም ለዚህ ምክንያት ናቸው ያላቸው 7 ተጫዋቾች ላይ የስንብት እርምጃ የወሰደ መሆኑ ታውቋል። ቡድኑ ከዚህ ውሳኔ በኋላ በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ላይ የሚገኘው ካፋ ቡናን አስተናግዶ 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ተሻሽሎ የሚቀርብ መሆኑንም ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።


ጭምጭምታ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የግማሽ አመት ግምገማ ላይኖር እንደሚችል ከፌዴሬሽን አካባቢ እየተሰሙ ያለ መረጃዎች ጠቁመዋል። የዚህ ግምገማ አለመኖር ዜና በብዙ ቡድኖች አመራሮች ውስጥ ዘልቆ የገባ ሲሆን ይህ ግምገማ የማይከናወን ከሆነ ውድድሩን እስከማቋረጥ ድረስ ውሳኔ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉና ግምገማው ለሁለተኛ ዙር ውድድር መስተካከል ያለባቸውን አስመልክቶ መስመር ለማስያዝ እቅድ የሚቀመጥበት በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ሀሳቡን በድጋሚ እንዲያጤን እየጠየቁ ይገኛሉ።

ሰበታ ከተማ 

አሰልጣኝ ስዩም ከበደን ያጣው ሰበታ ከተማ በምክትል አሰልጣኝ ታደሠ እየሰለጠነ የሚገኝ ሲሆን በሁለተኛ አጋማሽ ውድድር ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል የዋና አሰልጣኝ ቅጥር ሊፈፅም እንደሚችል ታውቋል። የተለያዩ አሰልጣኞችን በቅጥር እቅድ ውስጥ ማስገባቱም ተነግሯል።           

ኢብሳ በፍቃዱ

የ2010 የከፍተኛ ሊግ ውድድር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን በ8 ጎሎች እየመራ የሚገኘው ኢብሳ በፍቃዱ ባገጠመው ህመም የቀዶ ህክምና በማድረጉ ወደ ቀድሞ አቋሙ ለመመለስ ጊዜ እንደሚፈልግ ገልጿል።

ተዋወቁት

ስም – ብሩክ ኤልያስ

ክለብ – ደቡብ ፖሊስ

ዕድሜ – 19

ትውልድ ቦታ – ሀዋሳ 

ቁመት – 1፡65

ክብደት – 58

የሚጫወትበት ቦታ – የመስመር አጥቂ

” እግር ኳስን በትውልድ ከተማዬ ሀዋሳ ካሳሁን ኩማሎ የተባለ ግለሰብ በሚያሰለጥንበት ፕሮጀክት ታቅፌ ነው የጀመርኩት። ከዛም በቀጥታ ወደ ደቡብ ፖሊስ አመራሁ። ፖሊስን ለመቀላቀል አስቤው አላውቅም ነበር ፤ ነገር ግን ክለቡ ከፕሮጀክታችን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ሲያደርግ ባደረኩት መልካም እንቅስቃሴ በወቅቱ አሰልጣኝ ቾምቤ ገ/ህይወት አማካኝነት ቡድኑን ልቀላቀል ችያለሁ። በደቡብ ፓሊስ እስካሁን ደስተኛ ነኝ ፤ በገባሁባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ጥሩ እየተንቀሳቀስኩ እና ግብ እያስቆጠርኩ ነው። ከቡድኑ ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ የመቀላቀል እቅድም አለኝ።  “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *