‹‹ ደስታዬን የገለፅኩት ሆን ብዬ አሰልጣኙን ለማበሳጨት አልነበረም ›› የጅማ ከነማው አሰልጣኝ ፋንታዬ አባተ

ዛሬ በምድብ 3 የመጨረሻ ጨዋታ ጅማ ሼር ኢትዮጵያን አሸንፎ የምድቡ መሪ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ነገር ግን ከጨዋታው በተጓዳኝ የተፈጠረው ውዝግብ የበርካቶችን ትኩረት ስቧል፡፡ የውዝግቡ አካል የነበሩት የጅማ ከነማው አሰልጣኝ ፋንታዬ አባተ ስለተፈጠረው ነገርና ሌሎች ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ስለ ጨዋታው

ጨዋታውን አሸንፈን የሌሎቹን ውጤት ሳንመለከት ወደ ሩብ ፍፃሜው ለማለፍ አቅደን ነበር የገባነው፡፡ ነገር ግን ጨዋታው ባሰብነው መልኩ ባለመሄዱ ግብ ማስቆጠር አልቻልንም ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሰአት ይጫወቱ የነበሩት ሰበታ ከነማ እና ሀላባ ከነማ እየመሩ በመሆኑ ውጥረት ውስጥ ገብተንም ነበር፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ተከላካይ በማስወጣትና አጥቂ በመጨመር ውጤቱን ለማግኘት ጥረት አድርገናል፡፡ በመጨረሻ ሰአት ጥረታችን ፍሬ አፍርቶ አሸንፈን ልንወጣ ችለናል፡፡

ስለተፈጠረው ሁኔታ

ውጤቱን እንፈልገው ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሌሎቹ ቡድኖች እየመሩ መሆናቸው ውጥረት ውስጥ ከቶን ነበር፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ግብ ስናስቆጥርም ከፍተኛ የደስታ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ የተሰማኝን የደስታ ስሜት ለመግለፅ ያህል እንጂ ሌላ ነገር አስቤ የፈፀምኩት ነገር የለም፡፡

ሲሳይ (የሼር ኢትዮጵያ አሰልጣኝ) የማከብረው ጓደኛዬ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ፀብ የለብንም፡፡ ሆን ብዬ እሱን ለማበሳጨትና ፀብ ለመፍጠር በሚል ያደረግኩት ነገር የለም፡፡ በእግርኳስ እንዲህ አይነት ነገሮች ይፈጠራሉ፡፡ የተፈጠረው ነገር በዚህ መልኩ ቢታይልኝ ደስ ይለኛል፡፡ አሰልጣኝ ሲሳይ ጅማዎች እንድንለቅላቸው ፈልገው ነበር ብለው የሰጡትን አስተያየትም አልቀበለውም፡፡

የፀጥታ ኃይሎች ይዘውኝ አልሄዱም፡፡ ከተፈጠረው ግርግር በኋላ የቡድናችንን ወጌሻ ይዘውት ሲሄዱ ተከትዬው መሄድ ስለነበረብኝ ነው ከፖሊሶቹ ጋር አብሬያቸው የሄድኩት፡፡

ስለ ድሬዳዋ ህዝብ

የድሬዳዋ ህዝብ ለሚሰጠን ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ እስካሁን በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ሲያበረታቱን ነበር፡፡ ለህዝቡ ያለኝ አክብሮት ከፍ ያለ ነው፡፡

ቀጣይ ተጋጣሚያቸው

ሆሳእና ከነማን በደምብ አላውቃቸውም፡፡ እዚህ ውድድር ላይ ነው የማውቃቸው፡፡ በጣም ጥሩ ቡድን ነው፡፡ ለቡድኑ አክብሮት አለን፡፡ ሁሉንም ነገር ከ90 ደቂቃ በኋላ እናየዋለን፡፡ አሁን ላይ መተንበይ አይቻልም፡፡ ነገር ግን የድሬዳዋ ህዝብ የሚደሰትበትን ምርጥ ጨዋታ እናሳያለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

 


በጅማ ከነማ እና ሼር ኢትዮጵያ ጨዋታ ስለተፈጠረው ውዝግብ ከዚህኛው ዜና በፊት ፖስት የተደረገው ዜና ====>>> ጅማ ከነማ በውዝግብ ታጅቦ ሩብ ፍፀሜውን ተቀላቀለ


 

ያጋሩ