የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን ሁለተኛ የውድድር ዘመን አጋማሽ ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ ጅማሮውን ሲያደርግ 10:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከአዳማ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ አንድ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ የተስተናገደበት ጨዋታ በሁለቱም በኩል ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ጨዋታው ከሳምንታት እረፍት በኋላ የተደረገ መሆኑ እና የአአ ስታድየም ሜዳ እርጥበት ያዘለ መሆን ለተጫዋቾቹ ፈተና ሲሆን ተስተውሏል።
ከእረፍት በፊት በባንክ የሜዳ አጋማሽ አጋድለው የተሻለ የተንቀሳቀሱት እንግዳዎቹ አዳማ ከተማዎች እንደኳስ ቁጥጥር የበላይነታቸው ወደ ሳጥን የገቡባቸው አጋጣሚዎች እጅግ ጥቂት ነበሩ። በ45ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ ጀምሮ በማራኪ የአንድ ሁለት ቅብብል ይዘው የመጡትን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ ከሳጥኑ ጠርዝ ሞክራ አግዳሚው የመለሰባት ኳስም ብቸኛው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። በንግድ ባንክ በኩል በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን በመጠቀም አጥቂዎቹ ረሒማ እና አይናለም የግብ እድል ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት እምብዛም ስኬታማ አልነበረም።
ከእረፍት መልስ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን ከመጀመርያው በባሰ መልኩ የጠራ የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ ሳይታይ ቀርቷል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከርቀት በሚሞከሩና ኢላማቸውን በሳቱ ኳሶች የጎል እድል ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ በ83ኛው ደቂቃ ዙለይካ ጁሀድ ከተሻማ ኳስ የተመለሰውን ኳስ ሞክራ ወደ ውጪ የወጣባት እንዲሁም በግምት ከ20 ሜትር አይናለም የመተመችውና በተከላካዮች የተመለሰው ኳስ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።
ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በነበረበት 2ኛ ደረጃ ሲረጋ አዳማ ከተማ አንድ ደረጃ አሻሽሽሎ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።