የሴቶች ፕሪምየር ሊግ፡ ደደቢት መሪነቱን ሲያጠናክር መከላከያ ደረጃውን አሻሽሏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ 4 ጨዋታዎች ሲቀጥል ደደቢት መሪነቱን ያጠናከረበትን መከላከያም ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ያደረገበትን ድል አስመዝበዋል፡፡ በክልል ስታድየም የተደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

የአዲስ አበባ ስታድየም ውሎ (በዳንኤል መስፍን)

08:00 በጀመረው የመከላከያ እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ መከላከያ የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብቷል ። መከላከያ የሴቶቹ ዋና አሰልጣኝ የነበረውን ኑረዲን አደምን ወደ ወንዶቹ ም/አሰልጣኝነት ሲቀየር በምትኩ የቀድሞ የወንደቹ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የነበረው ምንያምር ፀጋዬ ወደ ሴቶቹ በመምጣት አሰልጣኝ ሆኗል።  በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ሆኖ በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚን የመከላከያዋ አጥቂዋ መዲና አወል ነፃ ኳስ ባመከነችበት ቅፅበት ከቀኝ መስመር የተሻገረላትን ኳስ በ12 ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥራ መከላከያን ቀዳሚ በማድረግ ችላለች ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ 19ኛው ደቂቃ ላይ ረድኤት አሳሳኸኝ ከመሀል ሜዳ የተጣለላትን ኳስ ብቻዋን ወደፊት በመግፋት የግብ ጠባቂዎን ከግብ ክልል መውጣት በማየት ቺፕ አድረጋ ግሩም ጎል በማስቆጠር ሲዳማ ቡናዎች አቻ መሆን ችለዋል። በጎሉ መቆጠር ጫና ውስጥ የገቡት መከላከያዎች ባልተደራጀ ሁኔታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ራሳቸው ላይ አደጋ እየፈጠረ ሲዳማዎች ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን አጋጣሚ  በተለይ 44 ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ መልኩ ረድየት አስረሳኸኝ ከግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ ጋር ብቻዋን ተገናኝታ ለጥቂት የወጣባት ኳስ ሲዳማዎችን መሪ ማድረግ የሚችል አጋጣሚ ነበር ።

ከእረፍት መልስ 50ኛው ደቂቃ ላይ እመቤት አዲሱ ከ30 ሜትር ርቀት ላይ የመታችው ቅጣት ምት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት 68ኛው ደቂቃ መዲና አወል ከግብ ጠባቂዋ ጋር ብቻዋን ተገናኝታ ያልተጠቀመችው መከላከያዎች ከእረፍት መልስ ጎል ፍለጋ ተጭነው መጫወታቸውን ማሳያ ሲሆን ተቀይራ የገባችው ሄለን ሰይፋ በቅጣት ምት ጎል አስቆጥራ መከላከያ በድጋሚ እንዲመራ አስችላለች፡፡ ከ12 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞበጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው የሲዳማ ቡናዋ አጥቂ ረድኤት አስረሳኸኝ የግል ጥረቷን ተጠቅማ 80ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎል አሰቆጥራ ሲዳማን አቻ ማድረግ ችላለች ። ከሁለት ደቂቃ በኋላ በ82ኛው ደቂቃ መዲና አወል ከሳጥን ውጭ ግሩም ጎል በማስቆጠር ለራሷ ሁለተኛ መከላከያዎችን አሸናፊ የሚሆኑበትን ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በመከላከያ 3 – 2 አሸናፊነት ተጠናቋል ። በዚህም መከላከያ ንግድ ባንክን በመብለጥ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ እንዲያደርግ አግዞታል፡፡

10:00 በቀጠለውና የሊጉ መሪ ደደቢትን ከደረጃው ግርጌ ከሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክን ጋር ባገናኘው በዚህ ጨዋታ ጅማሬ የግብ እድል በመፍጠር በጤናዬ ወመሴ አማካኝነት ኢትዮ ኤሌትሪክ ቀዳሚ የነበረ ቢሆንም ከግራ መስመር ቡርቱካን ገ/ክርስቶስ ያሻገረችውን በ9ኛው ደቂቃ ላይ ትግስት ዘውዴ በግንባሯ በመግጨት ደደቢትን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች ። ፍፁም የደደቢት የበላይነት በታየበት በዚህ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 16ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ የኤሌክትሪክ ግራ መስመር ክፍተትን ተጠቅማ ሰብራ በመግባት ያቀበለቻትን ኳስ ሰናይት ባሩዳ ሁለተኛ ጎል አስቆጠረች ። 28ኛው ደቂቃ ከኤሌትሪክ የግብ ክልል በ30 ሜትር ርቀት ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት ሎዛ አበራ 3ኛ ጎል ስታስቆጥር  በድጋሚ በ34ኛው ደቂቃ ተከላካዮችን በፍጥነቷ ተጠቅማ በማለፍ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል አስቆጥራ 4 – 0 በሆነ ሰፊ ውጤት ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ።

በሁለተኛው አጋማሽ የአራት ተጨዋቾች ቅያሪ በአንዴ በማድረግ ወደ ሜዳ የገቡት ኢትዮ ኤሌትሪኮች ከእረፍት በፊት ከነበረው በተሸለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ለጎል የቀረበ ጠንከራ የጎል ሙከራ ማድረግ ሲቸገሩ ተስተውሏል። 65ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ በጨዋታው ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ጎል ከርቀት መታ በማስቆጠር የጎሉ መጠንን ወደ 5 አስፍታዋለች ። ይህን ጎል ተከትሎም ባሳለፍነው ማክሰኞ ትዮጵያ ሊብያን 7-0 ስትረታ አራት ጎሎች ያስቆጠረችው ሎዛ አበራ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለተኛ ሐት-ትሪኳን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ብሩቱካን ገ/ክርስቶስ 67 ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጋር ብቻዋን ተገናኝታ ቺፕ አድርጌ አስቆጥራለው ብላ ኳሱ ረዝሞ የወጣበት በደደቢት፣ ተቀይራ የገባችው አይናለም ፀጋይ በኤሌክትሪክ በኩል የሚጠቀሱ ሌሎች ሙከራዎች ነበሩ፡፡ ሰማያዊዎቹ በድሉ ተጠቅመው ከመከላከያ በ4 ነጥብ ርቀው ሊጉን እንዲመሩ አስችሏቸዋል፡፡

በሁለቱም የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታዎች ላይ ምንም አይነት የማስጠንቀቂያ ካርድ ሳይታይ መጠናቀቁ አስገራሚ ሆኗል።

የክልል ስታድየሞች ውሎ (በቴዎድሮስ ታከለ)

09፡00 ሀዋሳ ላይ በሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል፡፡ በሁለቱም የጨዋታ አጋማሾች ሀዋሳ ከተማዎች በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ሆነ በግብ መከራው የተሻሉ የነበሩ የሚያገኟቸውን እድሎች በመጠቀሙ ረገድ ደክመው ታይተዋል፡፡ ድሬዳዋ ከተማዎች በአንጻሩ በመልሶ ማጥቃት በመጫወቱ ረገድ ተሽለው ቀርበዋል፡፡  ግብ ለማስቆጠሩ ቀዳሚ የሆኑት ድሬዳዋወች ሲሆኑ ገና በ5ኛው ደቂቃ ላይ ተራማጅ ተስፋዬ የሀዋሳ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች የሰሩት ስህተት ተጠቅማ ለመቅደስ ማስረሻ የሰጠቻትን ኳስ መቅደስ ወደ ግብነት ለውጣዋለች፡፡ ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ የድሬዳዋን የግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲጎበኙ የታዩት ሀዋሳ ከተማዎች ያለቀላቸውን የግብ አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ 16ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን ከግብ ጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ ያመከነችው፣ ለእረፍት  ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው መሳይ ተመስገን በድጋሚ ያመከነችው ግልጽ የግብ ማስቆጠር እድል እንዲሁም ትርሲት መገርሳ ከቅጣት ምት መታ ግብ ጠባቂዋ ፍሬወህኒ ገብሩ እንደምንም ያወጣችው ኳሶች የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ሀዋሳዎች በተለይ ነጻነት መናን ቀይረው ካስገቡ በኋላ በርካታ የግብ አጋጣሚን መፍጠሩ ችለው ነበር፡፡  53ኛው ደቂቃ ላይ ነፃነት ያገኘችሁ የግብ ማግባት አጋጣሚም ሀዋሳን አቻ ለማድረግ የቀረበች ነበረች፡፡ ግብ ለማስቆጠር የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች መጠበቅ ግድ ያላቸው ባለሜዳዎቹ 85ኛው ደቂቃ ላይ ሳራ ኬዲ ከማዕዘን ምት ያሻገረቻትን ኳስ አማካይዋ እታለም አመኑ በግንባሯ ገጭታ ባስቆጠረችው ግብ አቻ መሆን ችለዋል፡፡

ዲላ ላይ በተመሳሳይ 09፡00 ጌዴኦ ዲላ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ለጌዴኦ ዲላ ሳራ ነብሶ ሁለቱንም ጎሎች ስታስቆጥር ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተልሄም ሰማን እና ኪፊያ አብዱራህማን አስቆጥረዋል፡፡

ውጤቶች

ሰንጠረዥ

ከፍተኛ ግብአስቆጣሪዎች