የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል። የዛሬው ዳሰሳችንም ትኩረቱን በነዚሁ ጨዋታዎች ላይ አድርጓል።
መከላከያ ከ አርባምንጭ ከተማ
በተከታታይ ደረጃ በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች እርስ በእርስ የሚገናኙበት ይህ ጨዋታ በቦታው ለውጦችን የመፍጠር ሀይል እንደሚኖረው ይጠበቃል። በሁለተኛው ዙር መጀመሪያ መጠነኛ መሻሻል አሳይቶ የነበረው መከላከያ ቀስ በቀስ ወደ ነበረበት የተመለሰ ይመስላል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ያስተናገዳቸው ሽንፈቶችም ዛሬ ካላበቁእና ሶስተኛ ሽንፈት ከመጣ ራሱን ይበልጥ ጫና ውስጥ የሚያገኘው ይሆናል። በአንፃሩ በሜዳው ከሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሙሉ ነጥቦችን እየሰበሰበ የሚገኘው አርባምንጭ መጠነኛ እፎይታ አግኝቷል። በ19ኛው ሳምንት ጥሩ አቋም ላይ የሚገኛው ኢትዮጵያ ቡና ላይ ድል የተቀዳጀው አርባምንጭ ከሜዳ ውጪ ያለው ደካማ ሪከርድ ቢያሰጋውም ከተጋጣሚው የተሻለ ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛል።
የመከላከያው ቴዎድሮስ በቀለ አሁንም ከጉዳቱ ያላገገመ ሲሆን ምንይሉ ወንድሙ እና ምንተስኖት ከበደ ከቅጣት ከመመለሳቸው ባለፈ ፍፁም ገ/ማርያምም ለቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታው ዝግጁ እንደሚሆን ተሰምቷል። በአርባምንጭ ከተማ በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና ባይኖርም ተከላካዩን ወርቅይታደስ አበበ ግን በ5 ቢጫ ካርድ ምክንያት ቡድኑን ማገልገል የማይችል ይሆናል።
ጨዋታው መከላከያ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ወስዶ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚሞክርበት እንዲሁም አርባምንጭ ጥንቃቄን መርጦ በመልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል ለመድረስ የሚጥርበት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል። በመሆኑም መከላከያዎች ለፊት አጥቂዎቻቸው የመጨረሻ ኳሶችን ከማድረሳቸው በፊት በተለይ በምንተስኖት አበራ መሪነት መሀል ሜዳ ላይ ክፍተትን ላለመስጠት ከሚሞክረው የአርባምንጭ ከተማ የአማካይ ክፍል ጋር መፋለም የኖርባቸዋል። ወደ መስመር በሚወጣው አንደኛው አጥቂያቸው በመታገዝም ጥቃታቸው የጎን ስፋትን አግኝቶ እስከ ፍፁም ቅጣት ምቱ ክልል ድረስ እንዲዘልቅ የቅብብሎቻቸው ስኬት ወሳኝ ይሆናል። ሆኖም ከቅብብል ስህተቶች መነሻነት የሚያጡዋቸው ኳሶች አደጋቸው ከፍተኛ ነው። በእንደዚህ አይነት አጋጣሚዎችን አርባምንጮች በአማኑኤል ጎበና እና እንዳለ ከበደ አማካይነት ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ድረስ ለመግባት ይጠቀሙባቸዋል። ሁለቱ አማካዮች በረሳቸው ግብ ማስቆጠር ከሚችሉበት ዕድል ባለፈም ወደ መስመር የሚልኳቸው ኳሶችም አደጋ ሊፈጥሩ ይችላሉ። በዚህ በኩል የመስመር አጥቂዎቹ ፀጋዬ አበራ እና ብርሀኑ አዳሙ የማጥቃት ፍጥነት በማጥቃት ሽግግር ወቅት ክፍተት የሚያገኝ ከሆነ ወደፊት ለመሄድ ከሚጥሩት የጦሩ የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚያደረገውን ፍልሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል።
የእርስ በእርስ ግንዝኙነት እውነታዎች
– አርባምንጭ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገበት 2004 ወዲህ ሁለቱ ቡድኖች 13 ጊዜያት ተገናኝተው መከላከያ 3 ጊዜ ፣ አርባምንጭ ደግሞ 4 ጊዜ አሸንፈዋል፡፡ በቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ መከላከያ 9 ፣ አርባምንጭ 11 ጎሎች አስቆጥረዋል፡፡
– አዲስ አበባ ስታድየም ላይ 6 ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ ሁለቱን በማሸነፍ እና በሶስት አጋጣሚዎች አቻ በመለያየት የተሻለ ሪኮርድ ሲይዝ መከላከያ በ2005 ካሳካው ድል ውጪ በሜዳው አርባምንጭ ከተማን አሸንፎ አያውቅም፡፡
– አርባምንጭ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ ከሜዳው ውጪ ድል ያሳካው በታህሳስ ወር 2009 መከላከያን በረታበት ጨዋታ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ባደረጋቸው 18 ጨዋታዎች ድል ማስመዝገብ ተስኖታል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ከሲዳማ እና ሀዋሳ ጋር አቻ ከመለያየት ውጪ በሌሎቹ በሙሉ ሽንፈትን አስተናዷል፡፡
ዳኛ
ጨዋታውን ፌዴራል ዳኛ ሚካኤል አርዓያ ይመራዋል፡፡ ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ ሁለተኛ ፣ በአጠቃላይ 7ኛ ጨዋታውን የሚመራው ሚካኤል ባለፉት 7 ጨዋታዎች 38 ቢጫ ካርዶች መዟል፡፡
Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ
ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ
ሁለተኛው የእለቱ የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ያለውን ቦታ ለማጠናከር ወልዋሎ ዓ.ዩ ደግሞ ከደረጃውን ግርጌ ለመላቀቅ የሚገናኙባት ይሆናል። ወደ ሰንጠረዡ አናት እየሄደበት የነበረው ፍጥነት አርባምንጭ ላይ የተገታበት ኢትዮጵያ ቡና ከፎካካሪዎቹ ላለመራቅ የግድ ከዚህ ጨዋታ ሶስት ነጥብ ማሳካት ይኖርበታል። በሁለተኛው ዙር አንድም ጨዋታ ማሸነፍ የተሳነው ወልዋሎ ዓ.ዩ ደግሞ ወደ ሊጉ በመጣበት አመት ተመልሶ እንዳይወርድ ካሁኑ ከመሰል ጨዋታዎች ነጥቦችን ማግኘት ያስፈልገዋል። የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቡድን ከበላዩ ያሉትን ቡድኖች የእርስ በእርስ ውጤት አይቶ የሚገባ በመሆኑም ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ቡና ሙሉ ስብስብ በመልካም ጤነነት ላይ የሚገኝ ሲሆን የግራ መስመር ተከላካዩ አስናቀ ሞገስ ግን የቀጥታ ቀይ ካርዱ ቅጣት ሁለተኛ ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል። ወልዋሎ ዓ.ዩ ደግሞ አሳሪ አልመሀዲን እና ግብ ጠባቂው ዮሀንስ ሽኩርን በጉዳት ሲያጣ አማካዩ ብርሀኑ አሻሞ ከረጅም ጊዜ ቅጣት በኃላ ወደ ሜዳ ይመለሳል፡፡
ሁለቱም ተጋጣሚዎች ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ አላቸው። የተጠጋጉ አማካዮች እና የቅርብ ርቀት በርካታ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የሚያሳዩዋቸው ባህሪዎች ናቸው። ሆኖም በቅርብ ሳምንታት እንደተመለከትነው በኢትዮጵያ ቡና በመስመር አጥቂነት የሚፈረጁ ተጨዋቾች በተለይ በመከላከል ሂደት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወደ አማካይ ክፍሉ ቀርበው መጫወታቸው ቡድኑ መሀል ክፍል ላይ በቁጥር ተበራክቶ ተጋጣሚው በቀላሉ እንዳያልፍ ያደርጋል። በመሆኑም የወልዋሎ ወደ መሀል የጠበ የአማካዮች እንቅስቃሴ ከፍተኛ የማጥቃት ሀላፊነት ከሚጣልባቸው የመስመር አጥቂዎቹ ሪችሞንድ አዶንግ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ተመጣጣኝ የሆነ እገዛን ማግኘት ይኖርበታል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የኢትዮጵያ ቡና አማካይ ክፍል ከሚያስጥላቸው እና ከወልዋሎ ተከላካይ መስመር ጀርባ የሚጥላቸው ኳሶች ለሳሙኤል ሳኑሚ የተመቹ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከተከላካይ መስመራቸው ጀርባ የሚተውት ሰፊ ክፍተት ቡድናቸው በሚያጠቃበት ወቅት ጥንቃቄን እንዲያደርግ የሚያስገድደው ነው። በተለይ በመሀል አጥቂዎች ቀጥተኛ ሩጫዎች ስህተት ለመስራት ሲቃረብ የሚታየው የቡድኑ የመሀል ተከላካዮች ጥምረት ከሶስቱ የወልዋሎ የፊት አጥቂዎች የሚደርስበትን ተመሳሳይ ፈተና በአግባቡ ማለፍ ይጠበቅበታል።
የእርስ በእርስ ግንዝኙነት እውነታዎች
– ወልዋሎ ዓ.ዩ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ባደገበት በዚህ አመት የመጀመርያ ዙር የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት ጨዋታ በወልዋሎ ዓ.ዩ 1-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።
– ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ የክልል ቡድኖችን ባስተናገደባቸው ስድስት ጨዋታዎች አንዴም ሽንፈት ያልገጠመው ሲሆን ሶስቱን በማሸነፍ በሶስቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። ግብ ሳይቆጠርበት ከሜዳ የወጣው ግን አርባምንጭን እና ወልዲያን ባሸነፈባቸው ጨዋታዎች ብቻ ነበር።
– ወልዋሎ ዓ.ዩ እስካሁን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ካደረጋቸው 4 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ኢትዮ ኤሌክትሪክን ብቻ ነው።
ዳኛ
ይህ ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ የሚመራ ይሆናል፡፡ በውድድር አመቱ 9 ጨዋታዎች የዳኘው በላይ በጨዋታዎቹ 35 ቢጫ እና አንድ ቀይ ካርድ መዟል፡፡