የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተከላካይ ሳላዲን በርጊቾ ስሙ ከፖርቱጋል ዝውውር እና ብሄራዊ ቡድን መቀነስ ጋር ተያይዞ የሰሞኑ መነጋገርያ ከሆኑት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሳላዲንን ጨምሮ ናትናኤል ዘለቀን እና ራምኬ ሎክ ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ ልምምድ ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ ቀርተዋል በሚል መቀነሳቸው ይታወሳል፡፡ ሳላዲን ስለ ፖርቱጋል ጉዞ እና የወደፊት የብሄራዊ ቡድ ቆይታው ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጠው አጠር ያለ ምላሽ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
‹‹ በፖርቱጋል ኤምባሲ ታይተዋል የሚለው ወሬ የመጣው በፌስቡክ ላይ ነው፡፡ እኔ ስለ ጉዳዩ የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ በፖርቱጋል ኤምባሲም አልታየሁም፡፡ ፖርቱጋል ኤምባሲ ሳይሆን ስፔን ኤምባሲ ነው ወረቀት ለመፈረም የሄድኩት፡፡ ስለ ዝውውሩ ጉዳይ የሚከታተልልኝም ለሌላ ሰው ነው፡፡ ›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
‹‹ በፖርቱጋል ለሙከራ ነው የምሄደው:: ክለቡ በፖርቱጋል 2ኛ ዲቪዥን የሚገኝ ሲሆን ሲዲ ፌሬንሴ ይባላል፡፡ ለዚህም አሰልጣኙ ፈቃድ ሰጥቶን ነበር፡፡ ጊዮርጊስም ፍቃደኛ ነው፡፡ የቪዛው ጉዳይ ካለቀልን ወደ ፖርቱጋል አምርተን የሙከራ ጊዜ እናሳልፋለን፡፡ ካልተሳካ ግን በጊዮርጊስ ለመቆየት በቃል ደረጃ ከቦርዱ ጋር ተስማምቻለሁ፡፡ ››
ወደ ብሄራዊ ቡደን ስለመመለስ
‹‹ ወደ ፖርቱጋል የምናቀና ከሆነ ወደ ቡድኑ መመለስ አለመመለሳችን የሚታወቀው ከወዳጅነት ጨዋታው በኋላ ነው፡፡ ›› (ኦገስት 28 ኢትዮጵያ የወዳጅነት ጨዋታ ታደርጋለች)
በጉዳዩ ዙርያ የቅዱስ ጊርጊሱ ህዝብ ግንኙነት ኤርሚስ አሸኔ ለሶከር ኢትዮጵያ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ ለናትናኤል እና ሳላዲን ለሙከራ ወደ ፖርቱጋል እንዲሄዱ ፍቃድ ሰጥተናቸዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾቹ የተሸለ እድል ሲያገኙ ትብብር ያደርጋል፡፡ ናትናኤል በቅርቡ ኮንትራት በመፈረሙ ቢዘዋወር ጊዮርጊስ በገንዘብ ረገድ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ሳላዲን ኮንትራቱ ቢናቀቅም የፖርቱጋል ሙከራው ካልተሳካ ከኛ ጋር ለመቀጠል በቃል ደረጃ ተስማምቷል፡፡ ›› ብለዋል፡፡