የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ወደ ሩብ ፍፃሜ ደረጃ ተሸገግሯል፡፡ በመጨረሻዎቹ የምድብ ጨዋተዎች የተከሰቱትን ውዝግቦች እና ጥያቄ የሚያስነሱ ጨዋታዎችን ተከትሎ የውድድር እነ ስነ-ስርአት ኮሚቴው የስነ ምግባር ጉድለት አሳይተዋል ፣ ከአቅም በታች ተጫውተዋል ያላቸው ላይ ቅጣት አስተላልፏል፡፡
የቅጣት በትሩ ከደረሳቸው መካከል ወደ ሩብ ፍጻሜው ያለፉት የጅማ ከነማው አሰልጣኝ ፋንታዬ አባተ ናቸው፡፡ አሰልጣኙ ከሼር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ ያሳዩት የደስታ አገላለጽ ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጠ ነው በሚል የክለቡን 4 ጨዋታ እንዳይመሩ እገዳ ተለልፎባቸዋል፡፡ 3ሸህ ብር ቅጣትም ተጥሎባቸዋል፡፡
አሰልጣኙ ከውሳኔው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ውሳኔውን እንደሚያከብሩ ተናግረዋል ‹‹ ስህተት ሰርቼ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ደስታዬን በጥልቅ ስሜት መግለፀን ነው የማውቀው፡፡ ቅጣቱ ለቀጣዩ የክለቡ ጉዞ የሚጎዳ ነው፡፡ ክለባችን ያለበትን ሁኔታ ታሳቢ አድርገው ከውድድሩ ፍፃሜ በኋላ ቅጣት ቢጥሉ መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ቅጣቱን አከብራለሁ፡፡ ›› ብለዋል፡፡
ሌላው በስነ ምግባር ጉድለት ቅጣት የተላለፈበት የጅማ አባ ቡናው ተከላካይ ምንያህል ወንድሙ አሰልጣኝ ደረጄ ናቸው፡፡ ተጫዋቹ ከአዲስ አበባ ከነማ ጋር በተደረገው ጨዋ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተወገደ በኋላ ያሳየው አላስፈላጊ ተግባር 4 ሺህ ብር እና የ4 ጨዋታ ቅጣት እከትሎበታል፡፡ በዚሁ ጨዋታ ከዳኛ እና ኮሚሽነሮቹ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተው የነበሩት አሰልጣኝ ደረጄም የ10 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡ አሰልጣኝ ደረጄ ስለ ቅጣቱ ከሚመለከተው አካል ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
ሱሉልታ ከነማ እና ሆሳእና ከነማ አሰልጣኞች ቡድናቸውን ከአቅም በታች አጫውተዋል በሚል ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡ የሆሳእና ከነማው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በወሎ ኮምቦልቻ የተሸነፉት ከአቅም በታች በመጫወት ነው በሚል የ3 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡ አሰልጣኙ ከቅጣት ውሳኔው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት በአስገዳጅ ሁኔታዎች እንጂ ከአቅም በታች በመጫወት እንዳልተሸነፉ አስረድተዋል፡፡
‹‹እኛ ከአቅም በታች ለመጫወት አልነበረም የገባነው፡፡ ከገንዘብ በተጨማሪ የጨዋ ቅጣ ሊተላለፍብኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ቋሚ ተሰላፊዎቻችንን ያላሰለፍነው በጉዳት እና በቅጣት እንዲሁም ወደ ሩብ ፍፃሜው ማለፋችንን በማረጋገጣችን ለቀጣይ ጨዋታ እረፍት ሰጥተናቸው እንደሆነ በማስረዳታችን ነው ቅጣቱ የቀለለው፡፡ ›› ብለዋል፡፡
የሱሉልታ ከነማው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እና የአሰልጣኝ ቡድናቸውም የቅጣት በትር አርፎባቸዋል፡፡ ሱሉልታ ከነማ ከ ባቱ ከነማ ጋር ያደረገው ጨዋታ ከአቅም በታች ነው በሚል አሰልጣኝ ጳውሎስ ፣ ረዳት አሰልጣኙ እና የቡድን መሪው እያንዳንዳቸው የ5 ጨዋታ እና 3ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡
‹‹ ስለ ቅጣቱ ምንም ማለት አልችልም፡፡ እኛ በጨዋታው ላይ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል፡፡ ሜዳ ውስጥ የሚጫወቱት ተጫዋቾች እንጂ አሰልጣኙ አይደለም፡፡ የሆነው ሆኖ ቅጣቱን አከብራለሁ›› ሲሉ አሰልጣኝ ጰውሎስ ለሶከር ኢትዮጵያ የተሰማቸውን ተናግረዋል፡፡
አሰልጣኞቹ የተቀጡትን ገንዘብ የማይከፍሉ ከሆነ ቀጣይ ጨዋታዎችን ላይመሩ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡