ባለፉት ሦስት ወራት ያልተረጋጋ የእግርኳስ ጊዜ ያሳለፈው ፍፁም ገብረማርያም ባለፈው ሳምንት ከወልዲያ ጋር በይፋ ከተለያየ በኋላ መከላከያን ተቀላቅሏል። ትላንት በ20ኛው ሳምነት የፕሪምየር ሊግ መከላከያ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ በመጀመርያው ጨዋታው ቡድኑን ለአሸናፊነት ያበቃ ወሳኝ ጎል ያስቆጠረው ፍፁም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
በመጀመርያ ጨዋታው ጎል ስለማስቆጠሩ
አዲስ ቡድን ስትገባ ካንተ የሚጠበቀው ጎል ማስቆጠር ነው። ጎልም ማስቆጠር ችያለው ፤ በዚህ አጋጣሚ በጣም ደስተኛ ነኝ። ወደ ትክክለኛው እንቅስቃሴ ለመመለስ ጥረት እያደረኩ ነው። ከሦስት ወር ቆይታ በኋላ ነው ወደ ሜዳ የተመለስኩት። ፊትነሴም ገና ነው። ከዚህ በኋላ ጠንክሬ እሰራለው። ጅማሬዬ ደግሞ በጎል መታጀቡ ትልቅ ነገር ነው።
ስለ ወልዲያ
ከወልዲያ በለቀቅኩበት ምክንያት ሦስት ወር ትንሽ ጭንቀት ውስጥ ነበርኩ። ይሄም የሆነው በክለቡ አመራሮች ጥፋት ነው። በዚህ አጋጣሚ የወልዲያ ደጋፊዎችን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለው። በቀላሉ ማለቅ የሚችል ነገር በአመራሩ ድክመት የተነሳ እዚህ አድርሶታል።
ስለ ቀጣይ እቅዱ
መከላከያ ላለመውረድ የሚጫወት ቢሆንም ከአሰልጣኝ ጨምሮ የቡድኑ ስብስብ እጅግ በጣም ጠንካራ ነው። ከእኔ ጎል ማስቆጠር ይጠበቃል። ዛሬ ጎል አስቆጥሬአለው፤ በቀጣይም ከቡድን አጋሮቼ ጋር አብረን ጠንክረን እየሰራን። ጎሎች እያስቆጠርኩ ቡድን ከዚህ የተሻለ እናደርሳለን ።