20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ቀጥሎ ሲውል አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ መቐለ ከተማን ከወልዲያ ጋር ያገናኘው ጨዋታ 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
መቐለ ከተማ ወደ ጅማ ተጉዞ ከተሸነፈበት ጨዋታ ምንም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ሲገባ በወልዲያ በኩል ከፋሲል ከተማው ጨዋታ ተሰላፊዎች መካከል የአንድ አመት እገዳ በተላለፈበት ብሩክ ቃልቦሬ ምትክ አሳልፈው መኮንን በመጠቀም ጨዋታውን ጀምሯል። ወልዲያ ከዚህ በተጨማሪም አሰልጣኝ ዘማርያምን በእገዳ ማጣቱንና ምክትል አሰልጣኙ በገዛ ፍቃዳቸው ስራቸውን መልቀቃቸቸውን ተከትሎ ያለ አሰልጣኝ ነበር ወደ ሜዳ የገባው።
በመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እጅግ ደካማ የሚባል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በዚሁ አጋማሽ ምንም አይነት ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ማየት አልተቻለም፡፡ መሀል ሜዳ ላይ የተገደበና ቶሎ ቶሎ የኳስ መነጣጠቆች በነበሩት በዚህ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በአንፃራዊነት ወደ ግብ የሞከሯቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ከቆሙ ኳሶች የተነሱ ነበሩ፡፡ መቐለ ከተማዎች አንጻራዊ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢኖራቸውም የጠሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታ በመጠኑም ነብስ የዘራ ቢመስልም በስታዲየሙ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ጨዋታውን ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ ፈታኝ አድርጎባቸው ነበር፡፡ በ51ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ የመቐለው ግብጠባቂ ፊሊፕ ኦቮኖ ከእጁ ስታመልጠው መስፍን ኪዳኔ አግኝቶ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ተጫዋቾችን ለማጠፍ ሲሞክር የመቐለ ተጫዋቾች ደርሰው ኳሷን እንዳይጠቀም ሊያደርጉ ችለዋል፡፡
በ66ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ጊዜ ውዝግብ በኃላ ከወልዲያ ከተማ ጋር የተለያየውና የቀድሞው ክለቡ የሆነውን መቐለ ከተማን የተቀላቀለው ያሬድ ብርሃኑ በጨዋታው ደካማ እንቅስቃሴ ያሳየው ጋቶች ፓኖምን ተክቶ በመግባት የመጀመሪያ ጨዋታውን ለአዲሱ ክለቡ ማድረግ ችሏል።
በጨዋታው የመጨረሻ 20 ደቂቃዎች መቐለ ከተማዎች ይበልጥ ጫና በመፍጠር በቀጥተኛ አጨዋወት የወልዲያን የተከላካይ ክፍል ሲፈተሹ ተስተውሏል፡፡ እጅግ አሰልቺ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ የተስተናገደው በ77ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከተከላካዮች በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ከቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት ወደ ግብ የላካትና ቤሌንጌ ያዳነበት ኳስ ነበረች፡፡
የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በ90+2ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ ደነቀ በረጅሙ ያሳለፈለትን ኳስ ቢስማርክ ኦፖንግ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የወልዲያ ተከላካዮችን በማምለጥ ያለፈውን ኳስ በወልዲያው ግብጠባቂ አናት ለማሳለፍ የሞከረውና ቤሌንጌ ያዳነበት ኳስ በመቐለዎች በኩል ጨዋታውን መወሰን የምትችል ጥሩ አጋጣሚ ነበረች፡፡
ጨዋታው በአቻ ውጠች መጠናቀቁን ተከትሎ መቐለ ከተማ በ29 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወልዲያ በ20 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።